አዲስ አበባ፡- የአንበጣ መንጋን የመከላከል ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ያመለከተው ግብርና ሚኒስቴር አልፎ አልፎ የሚያመልጠውን መንጋ ለመቆጣጠር ህብረተሰቡ ከጥቆማ ጀምሮ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል።
በግብርና ሚኒስቴር የዕፅዋት ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዘብዲዎስ ፍላፖ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል እንደተናገሩት፤ በአራት አውሮፕላኖች በመታገዝ ከጎረቤት አገራት በንፋስ እየታገዘ ከየመን፣ ከሱማሌ ላንድና ከፑንት ላንድ እንዲሁም ከሶማሊያ ወደ ኢትዮጵያ የሚገባውን አንበጣ ለመከላከል አሁንም ጠንካራ ሥራ በመሰራት ላይ ይገኛል።
በአምስት በሮች መንጋው የሚገባ መሆኑን ጠቁመው፤ በአገር ውስጥም በጋ መኸርና በልግ ላይ አረንጓዴ ተክሎች በስፋት የሚኖሩ በመሆናቸው አንበጣ የመብዛት እድል አለው የሚሉት አቶ ዘብዲዎስ፤ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ መኖሩም ተፅዕኖ እየፈጠረ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
አራት አውሮፕላኖችን ስትራቴጂክ በሆነ ስፍራ ዋነኛ መግቢያዎችን በመለየት የፀረ ተባይ መርጨት ሥራ በመከናወን ላይ መሆኑን ተናግረዋል። ሁለት ጠንካራ አውሮፕላኖችን በመጠቀም አንደኛውን ከድሬዳዋ እስከ ደጋሃቡር ያለው አካባቢ በመሸፈን፤ ከሶማሌ ላንድ የሚገባውን አይሻ ደወሌ አካባቢ ሊሰፍር የሚችለውን አንበጣ ከውጭ ገብቶ እንዳረፈ ማታ ያደረበት ቦታ ጥቆማ ስለሚካሄድ ሳይነሳ በጠዋት ርጭት በማካሄድ የመከላከል ሥራው እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በቀብሪደሃር በኩል በሽላቦ የሚገባውን ከጎዴ ቀላፎ አውሮፕላን እየተነሳ የሚከላከል መሆኑን ጠቁመው፤ ሆኖም ከእነዚህ አውሮፕላኖች አቅም በላይ ባይሆንም አንዳንዴ ሾልኮ የሚገባ መንጋ ሊኖር እንደሚችል ተናግረዋል።
አውሮፕላኖች ለርጭት ተነስተው ከሰሩ በኋላ ሌላኛው መንጋ ቢመጣ ፀረ ተባይና ነዳጅ እስከሚሞላ በተወሰነ መልኩ መንጋው የማለፍ ዕድል ሊያጋጥም እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
አሁን ወደ ባሌ ቦረና ጉጂ የደረሰው አንበጣ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ የነበረው ሰፊ መንጋ አረንጓዴ ነገር በብዛት ሲያገኝ ሁለት ሶስት ቦታ የሚበታተንበት አጋጣሚ በመኖሩ መሆኑን ጠቁመው፤ ያመለጠ የአንበጣ መንጋን ለመከላከል ህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 11/2012
ምህረት ሞገስ