-ለ65 ከፍተኛ የሰራዊት አመራሮች ሹመት ተሰጥቷል
አዲስ አበባ፡- ለሰራዊቱ ከመንግስት የሚፈለገው ሙሉ ለሙሉ መሟላቱንና ሰላምን በማስከበር ሀላፊነቱንም እንደሚወጣ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትርና የጦር ሀይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዶክተር አብይ አህመድ አስታወቁ። 65 ለሚሆኑ የሰራዊቱ ከፍተኛ አመራሮችም በፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ትናንት ሹመት ተሰጥቷል።
ለሰራዊቱ ከፍተኛ አመራሮች በታላቁ ቤተ መንግስት ትናንት ሹመት ሲሰጥ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባስተላለፉት መልዕክት ከመንግስት ለሰራዊቱ የሚፈለገው የደመወዝ፣ የዩኒፎርም፣ የአበልና ሌሎች ሁኔታዎች ሙሉ ለሙሉ መሟላታቸውን ገልጸዋል። ሰራዊቱ የአገሩን ስላም እንደሚያስከበርም ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመከላከያ ሰራዊቱ ከማንኛውም ፓርቲ፣ ብሄር፣ ሃይማኖትና ሌሎች ሁኔታዎች ገለልተኛ በመሆን በህገ መንግስቱ የተሰጠውን ተልዕኮ መሰረት አድርጎ ማገልገል አለበት።
ጄኔራል መኮንኖች ለራሳችሁና ለአገራችሁ ዘብ መቆም አለባችሁ ሲሉ አሳስበው ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎችም ህግን አክበረው መንቀሳቀስ ግዴታቸው ነው ሲሉ አመልክተዋል።
የኢፊዴሪ ፕሬዚዳንት አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ፤ ለተሿሚ ጄኔራል መኮንኖች ባስተላለፉት መመሪያ፤ ሹመቱ የተሰጠው ትናንት በአስቸጋሪ ሁኔታ የአገርና የህዝብ ሉዓላዊነትና ሰላም እንዲከበር ለፈጸማችሁት ተጋድሎ ነው።
በቀጣይም ዓመታትም ኢትዮጵያ ሰላሟ ተጠብቆ፣ ዜጎች ተፈቃቅረው ወደ ልማትና ዕድገት እንዲሄዱ ሰላምን በማስከበር ሀላፊነታችሁን በአግባቡ እንደትወጡ የተሰጠ አደራ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያን ከሚፈለገው ከፍታ ላይ ለማድረስ ሰላም ወሳኝ ነው ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ፤ ይህም ሀላፊነት ለመከላከያና ለጸጥታ ሀይሉ የተሰጠ መሆኑም ጠቅሰዋል። ሰላም ዓለም አቀፋዊ ነው ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ ሰራዊት በአፍሪካ ሰላምን በማስፈን የአገሪቱ አምባሳደር ሆኗል።
የዛሬ ተሿሚዎችና ሰራዊቱ እውቀትና ክህሎታችሁን በማሳደግና በተቋሙ መልካም አስተዳደር በማስፈን ሀላፊነታችሁን ተወጡ ሲሉም ጥሪያቸውን አቅርበዋል። አገሪቱ ታፍራና ተከብራ እንድትኖር ሰራዊቱ በዱር በገደሉ መስዋዕትነት በመክፈል ላደረገው አስተዋጽኦም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የኢፌዴሪ ጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል አደም መሃመድ በበኩላቸው ሰራዊቱ ህዝባዊነትን በመላበስ ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲና አመለካከት ገለልተኛ በመሆን ህዝብን በእኩልነት እያገለገለና የአገርን ለዓላዊነትን እያሰከበረ ነው።
በአገራዊና ዓለም አቀፋዊ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች የማይበገር እንዲሆንና የተሰጡትን ሀላፊነቶች በብቃት ለመወጣትም ማሻሻያዎች እያደረገ መሆኑንም አንስተዋል። የአገር ሉዓላዊነትንና ሰላምን እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰላም በማስከበር ያተረፈውን መልካም ሥም ለማስቀጠል ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።
በዕለቱ ለስድስት ከፍተኛ አመራሮች የሌተናል ጄነራልነት፣ ለ19 የሜጀር ጄነራልነት እንዲሁም ለቀሪዎቹ የብርጋዴር ጄነራልነት በአጠቃላይ ለ65 ከፍተኛ አመራሮች ሹመት ተሰጥቷል።
አዲስ ዘመን ጥር 10/2012
አጎናፍር ገዛኸኝ