- የክልሉ መንግስት ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም
አዲስ አበባ፡- በትግራይ የሕንጣሎ ወረዳ ነዋሪዎች በአዲሱ የአስተዳደር መዋቅር ሒዋነ ከምትባለው ወረዳ ጋር እንዲቀላቀሉ መደረጋቸውን ተቃውመዋል፡፡ ‹‹በአቅራቢያችን መተዳደር እንፈልጋለን›› በማለትም ከመቀሌ ከተማ ወደሳምረ በሚወስደው ደንጎላት በሚባል አካባቢ መንገድ ዘግተው የክልሉ መንግስትን ምላሽ በመጠባበቅ አራተኛ ቀናቸውን ደፍነዋል፡፡
ለመንገዱ መዘጋት ምክንያቱ የ‹‹ወረዳችን ይመለስልን›› ጥያቄ በማቅረብ ከህብረተሰቡ በተወከሉ ነዋሪዎች አማካኝነት ላለፉት ስድስት ወራት ያክል ወደክልል አስተዳደር ተመላልሰው ቢጠይቁም ምላሽ ባለማግኘታቸው ምክንያት የተነሳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ያናገራቸው የአካባቢው ነዋሪ አቶ መሀሪ ገብረ፤ ‹‹ህብረተሰቡ ሌላ ሃሳብ የለውም፣ ዓላማው ወደክልሉ ቢሮ በመመላለስ ላነሳው ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ነው›› ብለዋል፡፡
በተቃውሞው ሕብረተሰቡ ራሱ ሁኔታውን እንደሚከታተልና መንገድ ቢዘጋም የጸጥታ ችግር እንደሌለም ጠቁመዋል፡፡ መንገድ መዘጋቱ በአካባቢው ላይ ተጽእኖ አይኖረውም ወይ? በማለት ላነሳነው ጥያቄም፤ ይኖረዋል ይህን ያደረግነው ግን
ምላሽ ስላልተገኘ ነው፣ ግን የተቸገሩና ወሳኝ ጉዳዮች አይገደቡም ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አራተኛ ቀኑን የደፈነው ከሕንጣሎ ከተማ ወደ ሳምረ የሚወስደው መንገድ ምንም አይነት እንቅስቃሴ እንደሌለውም ምንጮቻችን አረጋግጠውልናል፡፡
የዞንና የወረዳ አስተዳዳሪዎች በአካል ተገኝተው ህብረተሰቡን ማነጋገራቸውን የጠቆሙት ምንጮች፤ ህብረተሰቡ የዞንና የወረዳ አስተዳዳሪዎች እንደማይፈልግና ከክልል አስተዳደር አካላት በአካል ተገኝተው እንዲያናግሯቸው እንደሚፈልጉም ተናግረዋል፡፡
‹‹ሕንጣሎ ድሮ የነበረ ወረዳችን ነው፡፡ ሕንጣሎ ወጅራት ተብሎ ወደ አንድ ተደርጎ ነበር›› ሲሉ አስታውሰው፤ በአዲስ አሰራር ሕንጣሎ እና ወጅራት ተብሎ በሁለት ተከፍሏል። በዚሁ መሰረት ሕንጣሎና አካባቢው ያሉ ቀበሌዎችን ይዞ ሕንጣሎ ወረዳ ወይም ደግሞ የአምስት ኪሎ ሜትር ልዩነት ባላት ደንጎላ ላይ ሊሆንልን ይገባል ብለዋል፡፡
ከሕንጣሎ እስከ ሒዋነ እስከ 35 ኪሎ ሜትር ርቀት ስላለው የሚፈልጉትን አገልግሎት ለማግኘት ስለሚቸገሩና ሕንጣሎ ወደሒዋነ መቀላቀሉ ተገቢ ባለመሆኑ እንዲስተካከል ጠይቀዋል፡፡
ሕንጣሎ ወረዳ ተመልሷል በሚል ስያሜውን ይዞ በህንጣሎ ያሉትን እንደ ደንጎላት ሳምረ ያሉ ቀበሌዎችን ይዘው ወደሒዋነ ከተማ መቀላቀሉ ትክክል አይደለም ብለዋል፡፡ ወረዳው ሕንጣሎና በእዛ አካባቢ ያሉ ቀበሌዎች እንዲይዝም ጠይቀዋል፡፡
በአደረጃጀቱ ላይ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ህዝቡን እንዳላነጋገሩ የጠቆሙት ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የአካባቢው ነዋሪ፤ ከዚህ ይልቅ ከአንዳንድ የቀበሌው አመራሮች ጋር ብቻ ተነጋግረው መወሰናቸው ለቅሬታው መፈጠር ምክንያት መሆኑን ነግረውናል፡፡
የክልሉ መንግስት ሕዝቡ በአቅራቢያው እንዲተዳደር በሚል ባወጣው የከተማ አወቃቀር የስምንቱ ቀበሌ ወኪሎች ተውጣጥተው ከወረዳ እስከ ክልል ድረስ ጥያቄውን ቢያቀርቡም ምላሽ እንዳላገኙ ገልጸዋል፡፡
በጉዳዩ ምላሽ ለማግኘት ወደ ትግራይ ክልል ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊያ ካሳ ጋር ደጋግመን ብንደውልም ምላሽ አላገኘንም፡፡ ምክትል ቢሮ ኃላፊው አቶ ሐዱሽ ካሱን በስልክ አግኝተናቸው በነዋሪዎቹ ቅሬታና ተቃውሞ ምላሽ እንዲሰጡ ጠይቀናቸው ጉዳዩን እንደማያውቁት አሳውቀውናል፡፡ ጉዳዩን አጣርተው ሊነግሩን መልሰን እንድንደውል የገለጹልን ቢሆንም፤ ለህትመት እስከገባንበት ጊዜ ድረስ ደጋግመን ብንደውልም ስልካቸውን ሊያነሱልን አልቻሉም፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 10/2012
ዘላለም ግዛው