አዲስ አበባ፡- ዘመናዊ የእንስሳት መኖ አቅርቦት ከሁለት በመቶ የማይበልጥ በመሆኑ በእንስሳት ምርታማነት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደሩን የእንስሳት መድኃኒትና መኖ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ።
በባለስልጣኑ የመኖ ምዝገባና ፍቃድ ዳይሬክተር አቶ ሞቲ ቸሩ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ዘመናዊ የእንስሳት መኖ አቅርቦት ከሁለት በመቶ አይበልጥም። ይህም አገሪቱ ያላትን ከፍተኛ የእንስሳት ሀብት ምርታማ እንዳይሆን አድርጎታል።
እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ዘመናዊ የእንስሳት አቅርቦት ካለመኖሩ በተጨማሪ የግጦሽ መሬት ታርሞና ተኮትኩቶ ከመርዛማ ነገር ተለይቶ ባለመቅረቡ በእንስሳት ሀብቱ ምርታማነት ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው። ከፍተኛ ቁጥር ያለው የአገሪቱ የእንስሳት ሃብት ለሚፈለገው ዓላማ ተለይቶ ለስርዓተ ምግብ ባለመቅረቡ የእንስሳት ሀብት በሚፈለገውና ባለው ሀብት መጠን ጥቅም እያስገኘ አይደለም።
የእንስሳት ሀብቱን ዘመናዊ ለማድረግም የእንስሳት ስርዓት ምግብ አሰራር ማስተካከል ይገባል የሚሉት አቶ ሞቲ፣ በዓመት ከ130ሺ ቶን የማይበልጠውን ዘመናዊ የእንስሳት መኖ አቅርቦት መቀየር ይገባል ብለዋል። በከተማ አካባቢ ያለውን አቅርቦት ብቻ ሳይሆን በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ዘመናዊ የእንስሳት መኖ ማቅረብ እንደሚገባና የግብርና ሚኒስቴር ኤክስቴንሽንም ይህን ተግባራዊ ማድረግ እንዳለበትም ተናግረዋል።
አቶ ሞቲ፤ እንስሳትን የሚያረባው ህዝብ ስለ ዘመናዊ መኖ አጠቃቀም ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆኑን ጠቁመው ግንዛቤውን ማሳደግ እንደሚገባም አብራርተዋል፡፡ የእንስሳት አረባቡ ቁጥር ላይ የተመሰረተ ሰለሆነ ቁጥሩን በማስተካከል የመኖ አቅርቦቱን መጨመር ያስፈልጋል ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የመኖ ኢንዱስትሪውን በማሳደግ ከፍተኛ የሆነውን የመኖ ዋጋ መቀነስ እንደሚገባ የጠቆሙት አቶ ሞቲ፤ መሰረታዊ የመኖ ንጥረ ነገር ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ ታክሱንም መቀነስ እንደሚገባ ጠቁመዋል። በአጠቃላይ የመኖ አቅርቦቱን በማስተካከል ምርትን በማሳደግ ገበያን ማዕከል ያደረገ፣ የንግድ እሳቤ ያለው አካሄድ መከተል ያስፈልጋል ሲሉም መክረዋል።
የኢትዮጵያ የእንስሳት ምርታማነትን ከስሩ ለመቀየር ስርዓቱን ከመሰረቱ ማስተካከል ይገባል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ የመኖን ምርታማነት፣ ጥራትና ውጤታማነት ለማሻሻል የክልል ግብርና ቢሮዎችና ግብርና ሚኒስቴር ኃላፊነት ወስደው መስራት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል። ለመኖ አቅርቦት ተስማሚ በሆኑ ቦታዎች የመኖ ግብዓት ማዕከላትን ማቋቋም ስርጭትና አቅርቦትን ማሳለጥም ይገባል ብለዋል።
በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች በግልና በመንግስት የመኖ ልማትን በግብርና በኤክስቴንሽንም በማስፋት፣ ፖሊሲ በማዘጋጀት እና በመኖ ምርት እንዲሳተፉ በማድረግ ለውጥ እንዲመጣ ማድረግም እንደሚገባ አቶ ሞቲ ጠቅሰዋል፡፡ በመኖ ልማት ባለሃብቶች፣ አርሶና አርብቶ አደሮች እንደ ሁኔታ ማሳተፍ እንደሚገባና የቢራ፣ የስኳርና ሌሎች ተረፈ ምርቶች ለእንስሳት መኖ የሚቀርብበትን ስርዓት መቀየስ ለምርታማነቱ ማደግ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ጠቁመዋል፡፡
ዝናብ አጠር አካባቢዎች ለእንስሳት መኖ የሚሆን ስልት በመንደፍ አቅርቦቱን ማስተካከል። ባለሃብቶች በእንስሳት መኖ ማምረት ኢንቨስትመንት እንዲሳተፉ ማድረግ፤ የደረቅና ፈሳሽ መኖ ዲፖዎችን በማዘጋጀት የመኖ አቅርቦትን ማሳደግም እንደሚገባም አቶ ሞቲ አመልክተዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 10/2012
አጎናፍር ገዛኸኝ