የትምህርት ዋናው ዓላማው ሰዎችን በእውቀት፣ በመረጃና በክህሎት በማበልጸግ ውሳኔያቸው ሁሉ እውቀትንና መረጃን መሰረት ያደረገ እና በምክንያት የሚያምን ማኅበረሰብን መፍጠር ነው። ትምህርት በሀገራችን ኢትዮጵያ ከተጀመረ በጣም ቆየት ያለ ቢሆንም የዘመናዊ መደበኛ ትምህርት ግን በአፄ ሚኒሊክ አማካኝነት በ1898 ዓ.ም እንደተጀመረና በ1950 ዓ.ም ደግሞ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መመስረቱን ከታሪክ እንረዳለን፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በአንድን ሀገር እድገት፣ ልማት፣ ስልጣኔ፣ ስነልቦናዊ አስተሳሰብ፣ እንዲሁም ማህበረሰባዊ እና ባህላዊ ወዘተ እሴቶች ላይ ያላቸው ተጽዕኖ ቀላል አለመሆኑ ይታወቃል። ሀገር ተረካቢ የሆነና ሃገሩንና ወገኑን የሚወድ፣ ብቁ እና ጤናማ የሆነ እንዲሁም በእውቀት የታነጸ ዜጋ ማፍራት ከቤተሰብ ቀጥሎ በአጠቃላይ የትምህርት ተቋማት ተቀዳሚ ድርሻ መሆን ይገባዋል።
ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተማረ የሰው ኃይልን በስፋትና በብቃት ለገበያ ከማቅረብ በሻገር ችግር ፈቺ የሆኑ ምርምሮችን በስፋት በማውጣት ኅብረሰተቡ ላይ ተጋርጠው የሚገኙትን ችግሮች የመፍታትም ግዴታ አለባቸው፡፡
በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ውስብስብ ችግሮች ባሉባቸውና በእነዚህም ችግሮች የህብረተሰቡ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ በሚስተጓጎልባቸው ሀገራት ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ችግር ፈቺ የሆኑ ምርምሮች በብዛትና በጥራት እየወጡ ለህብረተሰቡ መድህን ሊሆኑ ይገባል።የከፍተና ትምህርት ተቋማቱ ስኬትም በዋናነት መለካት ያለበት ከዚህ አንጻር መሆን ይገባዋል።
በኢትዮጵያ ውስጥ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በዓይነትም ሆነ በብዛት እየተበራከቱ ቢመጡም የተማረ የሰው ኃይልን ለገበያ ከማቅረብ በሻገር የኅብረተሰቡን ችግሮች መሰረት ያደረጉ ጥናትና ምርምሮችን ሲያደርጉና ማህበረሰቡን ሲታደጉ አይታዩም።
አብዛኞቹ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሲቋቋሙ ችግር ፈቺ የሆኑ ምርምሮችን በማድረግ የህብረተሰቡን ችግሮች ለመፍታት ዓላማ ይዘው ቢሆንም የተሳካላቸው ግን ጥቂቶቹ ናቸው።በዚህ ረገድ ተጠቃሽ የሆነውና የህብረተሰቡን ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉ ጥናትና ምርምሮችን በማውጣት የሚታወቀው የጅማ ዩኒቨርሲቲ ነው።ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም የተማሪዎችን የቤተመጽሃፍት አጠቃቀም የሚያሻሽልና መጽሃፍትን በመፈለግ ይጠፋ የነበረውን ጊዜ የሚያድን
በኤሌክትሮኒክስ የታገዘ የቤተመጽሃፍ አጠቃቀም ተግባዊ አድርጎ በተማሪዎች ዘንድ እፎይታን ፈጥሯል።በተመሳሳይም ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የሚሰራበትን የቾክና የሰሌዳ የትምህርት አሰጣጥ ዘዴን በኤሌክትሮኒክስ በመተካት በወጪም ሆነ በትምህርት አሰጣጡ ዘመናዊነት ጉልህ የሚባል ቴክኖሎጂን በምርምር ለትምህርቱ ዘርፍ አበርክቷል፡፡
ሰሞኑን ደግሞ በሆስፒታሎች አገልግሎት አሰጣጥ ሲጉላላ ለኖረው ታካሚ እፎይታን የሚሰጥ በአሻራ የተደገፈ የህክምና አገልግሎት በምርምር አውጥቶ እንካችሁ ብሏል።በተለይም ይህ የምርምር ውጤት በካርድ መጥፋትና መሰወር እንዲሁም በፍለጋ ይጠፋ የነበረውን ጊዜና እንግልት የሚቀንስ ከመሆኑም ባሻገር ብዙ ዕሮሮ የሚሰማበትን የህክምናው ዘርፍ ለማዘመን አይን ገላጭ የሚሆን ነው።
በርካታ ውስብስብ ችግሮች ባሉባትና ህብረተሰቡም የእነዚህ ችግሮች ገፈት ቀማሽ በሆነበት ሀገር የጅማ ዩኒቨርሲቲን አይነት ችግር ፈቺ የሆኑ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንዲበዙ ያስፈልጋል።አንዲትም ሀገር ያሏት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ብቃት የሚለካውም በሚያመርቱት የሰው ኃይል ብዛት ብቻ ሳይሆን ለህብረተሰቡ በሚያበረክቱት አስተዋጽኦም ጭምር በመሆኑ ዩኒቨርሲቲዎቻችን ፊታቸውን ችግር ፈቺ ወደ ሆኑ ጥናትና ምርምሮች በመመለስ ረግድ ጅማ ዩኒቨርሲቲን መንገድ መከተል ግድ ይላቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 9/2012