መሀል አዲስ አበባ ተወልዶ ያደገው ዮሴፍ ኃይለማርያም ብርታትና ጥንካሬን የወረሰው ከቤተሰቦቹ መሆኑን ይናገራል። ዮሴፍ በልጅነቱ ከሌሎች ወንድሞቹ የሚለየው በእግሩ ላይ በሚስተዋለው ጉዳት ነበር። ይሁን እንጂ በዚህ ስሜት ውስጥ ሆኖ እንዳያድግ ሰበብ የሆኑ በርካታ ምክንያቶች ነበሩት።
ወላጅ አባቱ በልጃቸው ላይ የእግር ጉዳት እንዳለ ቢያውቁም በዚህ ሰበብ ከሌሎች እህትና ወንድሞቹ ተለይቶ ወደኋላ እንዲቀር ፍላጎታቸው አልነበረም። በወቅቱ ታላላቆቹ ሊከውኑት የሚገባውን ሥራ ለእሱ ቀድመው በመስጠት የተለየ ኃላፊነት እንዲሰማው ያደርጉ ነበር። የዮሴፍ አባት ልጃቸው ጋዜጠኛ እንዲሆንም ምኞታቸውን ሲገልጹለት ቆይተዋል። በዱላ ተመርኩዞ መሄዱን ያውቁታልና በሬዲዮ ስቱዲዮ ተገኝቶ ድምፁን መስማት ምኞታቸው ነበር።
ዮሴፍ የልጅነት ዕድሜው ለከባድ ኃላፊነት የሚያበቃው አልነበረም። ርቆ መሄድና ሮጦ መድረስን ውዴታ በተመላበት ግዴታ ይፈጽመው ነበር። አባት ልጃቸው ‹‹አካል ጉዳተኛ›› ነው በሚል ልማድ ተቀምጦ እንዲቆዝም አይሹም። በተለየ ትኩረት እንዲታይም ፍላጎታቸው አልነበረም። ከሌሎች ልጆቻቸው በበለጠ በሥራ እንዲሳተፍ፣ልቆ እንዲታይና በተሸናፊነት ስሜት ዝቅ እንዳይል የሚችሉትን ሁሉ ያደርጋሉ።
እኩዮቹ አይፈጽሙትም የሚባለውን ጉዳይ ለእሱ ማሳለፋቸውም ሌሎች ጭምር ውጤቱን እንዲያዩትና ‹‹ይቻላል›› የሚለውን ሀቅ እንዲያረጋግጡ አስችሏል። የፊደልን ሀሁ ያልቆጠሩት ወላጅ እናቱም ቢሆኑ ከአይዞህ ባይነታቸው ባሻገር የልጃቸውን መከፋት አይሹም። ከወንድሞቹ ጋር ሩጫ ሲወዳደር እሱ እንዲቀድም የመፈለጋቸው ዋንኛ ምስጢርም ሽንፈት እንዳሰይማውና አካል ጉዳተኛ መሆኑን እንዳያስብ ለማድረግ ነበር።
በዚህ ዓይነቱ እውነታ ውስጥ ያደገው ዮሴፍ ታዲያ እያደር የቤተሰቡ መታወቂያ ጭምር መሆኑ አልቀረም።
ያለ እሱ የሰፈር ኳስ ጨዋታ የማይደምቅ፣ያለ እሱ ንግግር የትምህርት ቤቱ ስነጽሑፍ ጆሮ የማይስብ ሆነ። በዕድሜው ከፍ ሲል ደግሞ በታዋቂ ጋዜጦችና ሬዲዮ ጣቢያዎች በመሳተፍ የውስጥ ስሜቱን መተንፈስ ቻለ። የልጅነት ፍላጎቱንና የአባቱን ህልምም እውን ማድረግ ጀመረ።
አብሮት ያደገው የመተማመን ስሜት ወጣትነቱ ላይ ሲደርሰ አልተለየውም። በልጅነቱ ከእናት አባቱ በወሰደው የ‹‹ይቻላል›› ብርታት ተመርቶ በትዳር ጎጆ ለመውጣት ከቤቱ የመጀመሪያው ሆነ። ዛሬ ዮሴፍ በልጅነቱ የጀመረውን ስነጽሑፍ አዳብሮ ጋዜጠኛ መሆን ችሏል።
‹‹አሁን ሸክሜ ሁሉ ለአካል ጉዳተኞች ሆኗል›› የሚለው ጋዜጠኛ ዮሴፍ መረጃና ግንዛቤ ስለአካል ጉዳተኞች የሚለውን ማህበር በፕሬዚዳንትነት ይመራል። በአሁኑ ጊዜም በአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ተቀጥሮ ኤፍኤም 96 ነጥብ 3 ላይ በሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅነት በመሥራት ላይ ይገኛል። እሱ እንደሚለውም የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ የተለየ ትኩረት በመስጠት ማንነታቸውን ማንጸባረቅ ተቀዳሚ ዓላማው ሆኗል።
ዘንድሮ በተከበረው ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን ላይ ትኩረት እንዲሰጣቸው ከተደረጉ ነጥቦች መሀከልም አካል ጉዳተኞችን ወደ አመራር ኃላፊነት ማምጣት የሚለው አንደኛው ነው። እንደ ዮሴፍ ዕምነትም የምዕተ ዓመቱ ዋንኛ ግብ በዚህ ጉዳይ ላይ ማተኮሩ ለአካል ጉዳተኛው ተስፋ የሚሰጥ ጅማሬ ይሆናል።
ይሁን እንጂ ዮሴፍ ከዕቅዱ ተስፋ ሰጪነት ባሻገር ስጋት የመኖሩ እውነታ አይቀሬ መሆኑንም ይናገራል። ለዚህ የሚያስቀምጠው ምክንያት ደግሞ እስከዛሬ በአካል ጉዳተኞች ላይ የተቀረጸውን በጎ ያልሆነ አመለካከትን ነው። አካል ጉዳተኞች ‹‹አይችሉም›› በሚል መገለላቸው ያስከተለባቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያው ጫና ቀላል አይደለም።
በዕቅድ ሂደቱም የኖረውን አመለካከት መቅረፍ ካልተቻለ የተነደፈው ዓላማ ግቡን ይመታል የሚል ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ይቸግራል። ይህን ለውጥ በሚፈለገው መንገድ ለማስረጽ ደግሞ አካል ጉዳተኛውን ጨምሮ በጉዳዩ ላይ ‹‹ያገባናል›› የሚሉ የመንግሥት አካላት በአመለካከት ሊቀየሩ ይገባል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶሾሎጂ ትምህርት ክፍል መምህር ዳዊት የቆየሰው እንደሚሉት ደግሞ በ2030 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተግባራዊ የሚሆነው የልማት ግብ ሁሉን አቀፍ እንደመሆኑ የአካል ጉዳተኛውን ጉዳይ የሚያጎሉ አራት ነጥቦች ተካተውበታል።
በተለይ በግብ 8 ላይ የተጠቀሰው አካል ጉዳተኞች በሥራ ስምሪት ላይ ያላቸውን ተሳትፎ የሚረጋግጥ ነው። በተመሳሳይ በግብ 27 ላይ የሰፈረው ሃሳብም ይህንኑ ዕቅድ አጠናክሮ የሚያስቀጥል ስለመሆኑ ሰፍሯል።
አቶ ዳዊት እንደሚሉት በ2030 ተግባራዊ እንዲሆን የተነደፈው የልማት አጀንዳ ‹‹ማንም ወደ ኋላ እንዳይቀር በሚል መሪ ሃሳብ ጠብቆ የታሰረ ቃልኪዳን ነው። በዚህም እንደሌሎች የዓለማችን ክፍሎች ሁሉ በሀገራችን ያሉ አካል ጉዳተኞች የዕቅዱ ተጠቃሚና የዓላማው ግብ ይሆኑ ዘንድ ጥረቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል።
ወይዘሮ ሰሚራ ሱልጣን በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የሴቶች ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ አባል ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት መንግሥት ለአካል ጉዳተኞች የተለየ ትኩረት በመስጠት እየሠራ ይገኛል። የመንግሥት መስሪያ ቤቶችን ዕቅድና አፈጻጸም በመገምገም ሂደትም ተቋማት በአካልጉዳተኞች ላይ ባከናወኑት ተግባራት ወቅታዊ ሪፖርት እንዲያቀርቡ እየተደረገ ነው።
‹‹የሚወጡ ህጎችና አዋጆች እንዲተገበሩ ጥረቱ ይቀጥላል›› ያሉት ወይዘሮ ሰሚራ ያም ሆኖ ግን በርካታ ሥራዎች የሚቀሩ በመሆናቸው ከ2030 የልማት ግቦች ጋር ተያይዞ ምክርቤቱ በተሟላ ሁኔታ ሥራዎችን ለማከናወን ዝግጁነቱን እንደሚያረጋግጥ ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 9/2012
መልካምስራ አፈወርቅ