- በመሠረታዊ የምግብ ሸቀጦች ላይ የተጨመረ ታክስ የለም
አዲስ አበባ፡- ኤክሳይዝ ታክሱ የተሽከርካሪን ዋጋ እንደሚቀንስና በመሠረታዊ ሸቀጦች ላይም የተጨመረ ኤክሳይዝ ታክስ አለመኖሩን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፣ በቅርቡ ለተወካዮች ምክር ቤት ተሻሽሎ የቀረበው የኤክሳይዝ ታክስ ማሻሻያ አዋጅ የተሽከርካሪን ዋጋ የሚቀንስ እንጂ የሚጨምር አይደለም።
በተሻሻለው አዋጅ ከ1300 ሲሲ በታች ያሉ የአዳዲስ ተሽከርካሪዎች ኤክሳይዝ ታክስ ከ35 በመቶ ወደ አምስት በመቶ ዝቅ እንዲል ተደርጓል ይህም ከጠቅላላው ዋጋ 83 በመቶ (ከ200 እስከ 250 ሺ ለአንድ መኪና) የሚቀንስ ነው። እነዚህም ለንግድም ሆነ ለግል አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉ በመሆኑ የአዳዲስ መኪናዎችን ዋጋ እስካሁን ከነበረው የበለጠ ርካሽና ከአሮጌው ጋርም ተቀራራቢ ያደርጋቸዋል።
ኤክሳይዝ ታክስ ለሀገር ውስጥም ለውጪም በተመሳሳይ የሚሰራ ቢሆንም የሀገር ውስጥ አምራቾች በጉምሩክ በኩል የሚቀረጠው 65 በመቶ የሚደርስ ግብር የማይመለከታቸው በመሆኑ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ገልጸዋል። የሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርትንም በተመለከተ በማህበር ለሚደራጁት አዳዲስ ተሽከርካሪዎች ምንም ዓይነት ቀረጥ ሳይከፍሉ እንዲያስገቡ የሚፈቅድ ሕግ ስላለ ከኤክሳይዝ ታክሱ ጋር በተያያዘ የሚፈጠር ተጽእኖ እንደማይኖር ተናግረዋል።
ፖሊሲው የተዘጋጀው በአንዳንድ አካላት እየተነገረ እንዳለው መንግሥት ብዙ ገቢ የመሰብሰብ እቅድ ኖሮት አይደለም ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው በአሁኑ ወቅት ወደሀገር ውስጥ እየገቡ ያሉት ተሽከርካሪዎች ከስምንት እስከ አስር ዓመት ጥቅም ላይ የዋሉ ናቸው።
በመሆኑም በቅናሽ ወደ ሀገር ቢገቡም ለነዳጅና ለጥገና የሚጠይቁት ወጪ ከመግዣው በላይ እየሆነ ነው። በተጨማሪም ዘርፉ በሀገር ውስጥ አምራቾች በኩል የሥራ ዕድል መፍጠር ባለመቻሉ ኢንዱስትሪው ተቀዛቅዞ ቆይቷል።
በመሆኑም ያሉትን ለማበረታታትና አዳዲስ ባለሀብቶችም ወደገበያው እንዲቀላቀሉ በኤሌክትሪክ የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪ ለማምረት የሚመጡትንም ባለ ሀብቶች የሚያበረታታ ይሆናል።
ዶክተር እዮብ ጨምረው እንደተናገሩት መሠረታዊ የምግብ ሸቀጦችን በተመለከተም በስኳር፤ በጨውና ዘይት ምርቶች ላይ ምንም የተጨመረ አዲስ ታክስ የለም። ይልቁን ‹‹በስኳር ላይ ዋጋ ተጨምሯል›› የሚል ወሬ የሚያስወሩት ልዩ ጥቅምና ፍላጎት ያላቸው አንዳንድ አካላት ናቸው። በተጨማሪ በአዋጁ ዝግጅት ወቅት ስኳርና ጨው ለጤና የሚጎዱ በመሆኑ ኤክሳይዝ ታክሰ እንዲጣልባቸው የተነሳም ሀሳብ ነበር። ነገር
ግን ስኳርና ጨው ላይ ምጣኔውን የመቀነስ ሥራ በመሰራቱ ከዚህ በፊት ስኳር ላይ ይጣል ከነበረው 33 በመቶ የኤክሳይዝ ታክስ ከማምረቻ ወደ ሽያጭ ሲሸጋገር 27 በመቶ ሆኖ የነበረ ሲሆን አሁን ግን ከዚያም ቀንሶ ሃያ በመቶ እንዲሆን ተደርጓል። ይህም የስኳር አምራቹን የሚያበረታታና ከውጭ የሚገባውም በቅናሽ ዋጋ ለተጠቃሚው እንዲደርስ የሚያስችል ነው። በዘይት በኩል ለምግብነት ቢውሉ ለጤና ጎጂ የሆኑትና ለኢንዱስትሪ ግብአት የሚውሉና ሃምሳ በመቶና ከዚያ በላይ የስብ መጠን ያላቸው ምርቶች ላይ ነው ኤክሳይዝ ታክስ የተጣለው፡፡
በተመሳሳይ በጨውም ላይ የተጣለ አዲስ ኤክሳይዝ ታክስ የለም። ይሄ እንዳለ ሆኖ የገበያ መዋቅሩ ላይ ችግር በመኖሩ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪን መከላከል ስለሚያስፈልግ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደሥራ እየተገባ መሆኑን ገልጸዋል።
ቢራን በተመለከተ አሁን ለመጣል የተቀመጠው ኤክሳይዝ ታክስ ከፍተኛ ሆኖ ሳይሆን እስካሁን ማምረቻ ላይ ይጣል የነበረው ታክስ ግልጽነት ያልነበረውና በዚህም ለብልሹ አሠራርና ለሙስና የተጋለጠ በመሆኑ በሕጉ በተቀመጠው መሠረት ሃምሳ በመቶ ሳይሆን እስከ 17 በመቶ ብቻ ሲከፈል ነበር።
የአሁኑ ግን አርባ በመቶ በሽያጭ ብቻ የሚያስከፍል ነው። ወጣቱን ከሱሰኝነት ለመታደግ ብዙ መጨመር እንደሚያስፈልግ በአዋጁ ዝግጅት ወቅት የተነሳ ቢሆንም ቢራ አምራቾች በርካታ የሥራ ዕድል የፈጠሩ በመሆኑና አርሶ አደሩንም ስለሚመለከት ወደፊት እየታየ የሚስተካከል እንደሚሆን አስገንዝበዋል። በተመሳሳይም በሲጋራ ላይ መጠነኛ ጭማሪ መደረጉንም ዶ/ር እዮብ በመግለጫው ላይ አስታውሰዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 9/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ