አዲስ አበባ፡- በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚደረጉ ውይይቶች እስከ ጥር መጨረሻ ድረስ እንዲቀጥሉ ከስምምነት የተደረሰ ሲሆን ኢትዮጵያም በቀጣይ ውይይቶች በህዳሴው ግድብ ሙሌትና ውሃ አለቃቀቅ ዙሪያ የሚደረጉ ውይይቶች የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መልኩ እንዲጠናቀቁ መስራቷን እንደምትቀጥል ተገለጸ፡፡
ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን የህዳሴውን ግድብ ሙሌትና ውሃ አለቃቀቅ አስመልክተው በዋሺንግተን ባደረጉት ውይይት እስከ አሁን የተደረጉትን የቴክኒክ ውይይቶች ጨምሮ እስከ ያዝነው ጥር መጨረሻ ድረስ ጉዳዩ በጥልቀት እንዲመከርበትና ውጤቱም እንዲቀርብ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነብያት ጌታቸው ትናንት በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስረዱት የኢትዮጵያ፣ የግብጽና የሱዳን የውጭ ጉዳይና የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች እ.አ.አ ከጥር 13 እስከ 15 / 2020 በዋሺንግተን ባደረጉት ውይይት እስከ አሁን የተደረጉትን የቴክኒክ ውይይቶች ጨምሮ ጉዳዩ በጥልቀጥ እንዲመከርበትና እ.አ.አ. እስከ ጥር 28 /2020 ውጤቱ እንዲቀርብ ተስማምተዋል።
በቀጣዮቹ የቴክኒክ ውይይቶች የውሃ አለቃቀቅ ሥርዓት፣ ከመጀመሪያው ዙር ሙሌት በኋላ የሚኖር የሙሌት ሂደት፣ በግድቡ ዙሪያ የሚኖር ዘላቂ ትብብር እና በድርቅና በተራዘመ ድርቅ ወቅት የሚኖር ትብብር እልባት እንደሚያገኙ ስምምነቱ ማመላከቱን ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።
የሦስትዮሽ ስምምነቱ በግድቡ ሙሌትና ውሃ አለቃቀቅ ላይ የሚደረገውን ውይይት በስምምነት ለመቋጨት የሚረዳ የድርጊት መርሃ ግብር እንደተቀመጠለት የጠቀሱት አቶ ነብያት ኢትዮጵያም ቀጣዮቹ ውይይቶች የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መግባባት እንዲጠናቀቁ መስራቷን ትቀጥላለች ብለዋል።
ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይም መግለጫ ሰጥተዋል።ከነዚህም ውስጥ 33ኛው የአፍሪካ መሪዎች ስብሰባ ‹‹ግጭትና ጦርነትን በማስቆም ለአፍሪካ ልማት ምቹ ሁኔታን መፍጠር›› በሚል መልዕክት እ.አ.አ ከየካቲት 9 እስከ 10 በአዲስ አበባ እንደሚከበርም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር የምታደርገው ዲፕሎማሲ ጥብቅ አፍሪካዊ መሠረት የያዘ እንደሆነም በመግለጫቸው ተናግረዋል።በኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ጉልህ ሥፍራ ከሚይዙ ጉዳዮች አንዱና ዋነኛው ኢትዮጵያ በፀረ- አፓርታይድ ትግል ውስጥ የተጫወተችው ሚና ተጠቃሽ እንደሆነ ጠቅሰው፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መስራች ሀገር እንደመሆኗ በአፍሪካ ተሰሚነትና ተጽዕኖ ፈጣሪነት ላይ ያተኮረ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ ስታደርግ እንደቆየችም አስታውሰዋል።
የኢትዮ ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት 50ኛ ዓመት የወርቅ እዮቤልዩ በዓልን በቤጂንግና በአዲስ አበባ ከተሞች ለማክበርም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።ሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩት እ.አ.አ በ1970 እንደሆነና ሁሉን አቀፍ ትብብራቸውም እየተጠናከረ መምጣቱን ጠቅሰዋል፡፡
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የምትከተለውን ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ አጠናክራ እንደምትቀጥል የገለጹት ቃል አቀባዩ ሰሞኑን በተለያዩ የአፍሪካና የአረብ ሀገራት የሚገኙ ዜጎች የሚደርስባቸውን ጥቃት ለማስቆም ከየሀገራቱ ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ንግግር እንደተደረገ አመልክተዋል።በዚህም መልካም ውጤት እንደተገኘ ጠቅሰው በቅርብ ቀናትም 238 የሚሆኑ ዜጎች ከሊባኖስ ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን አስረድተዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 9/2012
ኢያሱ መሰለ