አዲስ አበባ፡- ነገ እና ከነገ በስቲያ የሚከበረውን የጥምቀት በዓል በደማቅ ሥነ ሥርዓት ለማክበር የጎንደር ከተማ ዝግጅቷን አጠናቃለች።የጥምቀት በዓል በየዓመቱ በጎንደር ከተማ በድምቀት የሚከበር ቢሆንም በዚህ ዓመት ጥምቀት በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በመመዝገቡ ጎንደር በልዩ ዝግጅት እንደምታከብር ነው የተገለጸው።
በጎንደር ከተማ አስተዳደር የባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አስቻለው ወርቁ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ የሥርዓተ ጥምቀቱን ሙሉ ዝግጅት ለማክበር ዝግጅት ተጠናቋል፤ ገንዳዎች ውሃ ተሞልተዋል።ከአራት ሺህ በላይ ሰዎችን የሚይዝ የመመልከቻ ሰገነት ተዘጋጅቷል።
ሰባት የጥምቀት ፀበል መርጫ ፓምፖች ተዘጋጅተዋል። በበዓሉ ላይ ፓትርያርኩን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና የሃይማኖት አባቶች ይገኛሉ።የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባና የክልል ፕሬዚዳንቶች ይገኛሉ።
ዘንድሮ በጎንደር የሚከበረው የጥምቀት በዓል ‹‹ሕይወት በቤተ መንግሥት›› የሚል ዝግጅት እንዳለው አቶ አስቻለው ተናግረዋል።ዝግጅቱም በነገሥታቱ ዘመን የነበረውን አከባበር የሚያሳይ ነው።የጥበቃ ሥነ ሥርዓቱን፣ አዋጅ ሲነገር እና ግብር ሲቀርብ የሚያሳዩ ትዕይንቶች ተዘጋጅተዋል።ለዚህም ከተለያዩ የኪነ ጥበብና የባህል ቡድኖች ከ200 በላይ ወጣቶች ዝግጅት አጠናቀዋል።በጥር 11 ዕለት ምሽት የንጉሥ እራት ይዘጋጃል።
ከውጭ ለሚመጡ እንግዶች በጎንደር ከተማ ውስጥ ያሉ የተለያዩ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች፣ የተፈጥሮ መስህቦች ለማስጎብኘትም ዝግጅት ተደርጓል።ከበዓሉ ቀደም ብሎም ብዙ የውጭና የአገር ውስጥ ጎብኝዎች ወደ ከተማዋ ገብተዋል።
በጎንደር ከተማ የሚገኙ ሆቴሎችም ከስድስት ወር በፊት ዝግጅት እንዳደረጉ ነው አቶ አስቻለው የተናገሩት።ከጥር 10 እስከ 13 ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቱ ቢከበርም ከጥር 3 ጀምሮ የባህል ሳምንቶች ተደርገዋል።በባህል ሳምንቱ ውስጥም የተለያዩ ባህላዊ ትዕይንቶች ቀርበዋል። በቴዎድሮስ አደባባይና በመስቀል አደባባይ ባህላዊ ዓውደ ርዕዮች ተደርገዋል።ጥር 6 ቀን የዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ 201ኛ ዓመት የትውልድ ቀን ከባህል ፌስቲቫሉ ጋር ተከብሯል።
እንደ አቶ አስቻለው ገለጻ፤ ዛሬ ጥር 9 ቀን ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽት 11 ሰዓት ድረስ ሙሉ ዝግጅት አለ።በአደባባዮች፣ በጎዳናዎችና በአዳራሽ ውስጥ የባህል ባንዶች በባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች የታገዙ ዝግጅቶችን ያቀርባሉ።
አዲስ ዘመን ጥር 9/2012
ዋለልኝ አየለ