አዲስ አበባ፡- ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግና 900 ሚሊዮን ብር የሚፈጅ የማህበረሰብ በጎ አድራጎት አገልግሎት ፕሮግራም ማሰናዳቱን የሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስትሩ ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ ላይ በሚኒስቴር መስሪያቤቱ የተጠሪ ተቋማትና ስትራቴጂክ አጋርነት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር ጄነራል ዳይሬክተር ወይዘሮ አስማ ረዲ እንዳሉት 900 ሚሊዮን ብር የሚፈጅ የማህበረሰብ አገልግሎት ያሰናዳ ሲሆን በመጀመሪያ ዙርም 10ሺህ ወጣቶች ተጠቃሚ ይሆናሉ ።
እንደ ወይዘሮ አስማ አባባል የበጎ ፍቃድ አገልግሎትን ለመስጠት የሚመጡ ወጣቶች ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲሁም በቴክኒክ ሙያ ተመርቀው ሥራ ያላገኙ ወጣቶች በሙሉ ፍላጎት ካላቸው መመዝገብ ይችላሉ።
የብሔራዊ በጎ ፍቃድ የማህበረሰብ አገልግሎት ዋነኛ አላማም ወጣቶችን በማብቃት የሀገር እና የሕዝብ ፍቅርን፣ ምክንያታዊነትን፣ የሕይወት መምራት ክሕሎትን፣ አገራዊ አንድነትን፣ ብሔራዊ መግባባትን እና ጥልቅ ማሕበራዊ ትስስርን ለማጎልበት ያለመ መሆኑን ወይዘሮ አስማ ተናግረዋል።
እንደ ዳይሬክተሯ አባባል በዚህ የመጀመሪያው ዙር በሆነውና 10ሺ ሥራ ፈላጊዎችን በሚያሳትፈው እና ቀጣይነት ባለው በዚሁ ፕሮግራም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ተመርቀው ሥራ በመፈለግ ላይ ያሉ ወጣቶች የሚሳተፉ ይሆናል፡፡
ወይዘሮ አስማ ወጣቶቹ ለ3 ወር ስልጠና ይሰጣቸውና በቀጣይ አንድ ዓመት ውስጥ ማህበረሰቡን የሚያገለግሉ ሲሆን ለ10ሺ ወጣቶችም መሠረታዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት እንዲሁም የኪስ ገንዘብ ለመስጠት ከ900 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚፈጅና ይህም በመንግሥት እንደሚሸፈንም አብራርተዋል።
ወይዘሮ አስማ በዚህ በመላው ሀገሪቱና በሁለቱም ከተማ አስተዳደሮች በሚተገበረው ፕሮግራም የምዝገባ ሂደት በየወረዳዎች ባሉ የሰላምና የፀጥታ ቢሮች በቀጥታ እንዲሁም https://www. eservices.gov.et/application/…/1033//instruction በመጠቀም መመዝገብ ይቻላልም ብለዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 9/2012
ዳግማዊት ግርማ