የመርካቶ መናኸሪያ ግንባታ 80 በመቶ ተጠናቅቋል
አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ ከተማ የመገናኛ የብዙሃን ትራንስፖርት ተርሚናልና የየካ የአውቶብስ ዲፖ ስድስት ቢሊዮን ብር በሚደርስ ወጪ ለማስገንባት በጨረታ ሂደት ላይ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ የትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ፡፡ የመርካቶ አውቶብስ ተርሚናል ግንባታ 80 በመቶ መጠናቀቁም ተገልጿል፡፡
በቢሮው የፕሮጀክቱ ኃላፊ ኢንጅነር ናትናኤል ጫላ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ከተማዋ ለተሳፋሪዎችና ለተሽከርካሪዎች አገልግሎት የሚሰጡ ደረጃቸውን የጠበቁ መናኸሪያዎች (የተርሚናሎች)ና የአውቶብስ ዴፖዎች የሏትም፡፡ ይህንን ተግዳሮቶች ለመቅረፍም የመገናኛና የየካ ዘመናዊ የአውቶቡስ ዲፖዎችንና የብዙሃን ትራንስፖርት ተርሚናሎች ስድስት ቢሊዮን ብር በሚደርስ ወጪ ለማስገንባት በጨረታ ሂደት ላይ ናቸው፡፡
የመገናኛ የከተማ የብዙሃን ትራንስፖርት ተርሚናል በ11ሺህ 790 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚያርፍ ሲሆን ስምንት ወለሎች እንደሚኖሩት ኢንጅነር ናትናኤል ገልጸው አራቱ ወለሎች ለአውቶቡሶች እና ለታክሲዎች አገልግሎት መስጫ፣ አንድ የንግድ ማዕከል ወለል፣ አንድ የመኪና ማቆሚያ ወለል፣ የአስተዳደር ቢሮ እና የብዙሃን ትራንስፖርት ስምሪት ሥርዓትን ያካተተ ወለል እንደሚኖሩት ጠቅሰዋል፡፡
የየካ አውቶቡስ ዲፖ ለ850 አውቶቡሶች የማቆሚያ አገልግሎት የሚሰጥ ባለ አራት ወለል ህንጻ እንደሚኖረው ኃላፊው አመልክተው ዲፖው 12 የአውቶቡስ ማጠቢያ ማሽን ፣ 12 አውቶቡሶችን በአንዴ ማስተናገድ የሚችል የነዳጅ ማደያ፣ እንዲሁም በአንድ ጊዜ ለ50 አውቶቡሶች የጥገና አገልግሎት የሚሰጥ ዘመናዊ የአውቶቡስ ዲፖ እንሚይዝና 10 ወለል ያለው የአስተዳደር ህንጻንም እንደሚጨምር ተናግረዋል፡፡ ግንባታውን በተያዘው በጀት ዓመት ለማስጀመር በጨረታ ሂደት ላይ እንደሚገኙም ጠቁመዋል፡፡
በተመሳሳይ በአሁኑ ጊዜ በመርካቶ የገበያ ማዕከል በነባር ቦታ ላይ የመርካቶ አውቶቡስ መናኸሪያ 200 ሚሊዮን 120 ሺህ 905 ብር ወጪ ግንባታ እየተካሄደ እንደሚገኝ አውስተው ይህ አውቶቡስ መናኸሪያ በአንድ ጊዜ ለ20 አውቶቡሶች አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ተርሚናሉ በአንድ ሰዓት ውስጥ ስድስት ሺህ ለሚጠጉ የብዙሃን ትራንስፖርት ተጠቃሚዎች አገልግሎት መስጠት እንደሚያስችል የጠቆሙት ኢንጂነር ናትናኤል በውስጡም የአውቶቡስ መጠበቂያ ቦታ ፣ የትኬት ሽያጭ ፣ የተሳፋሪ መጫኛና የማራገፊያ ቦታ ፣ ዘመናዊ ስምሪት አገልግሎት ፣ የአውቶቡስ መርሃ-ግብር እና የአስተዳደር ቢሮዎች እንዲሁም ለአቅመ ደካሞች እና አካል ጉዳተኞች የሚሆኑ በጠቅላላው አምስት አሳንሰሮች ያካተተ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 8/2012
ጌትነት ምህረቴ