“ሠርቼ እለወጣለሁ” በሚል ሃሳብ ከመቐለ ከተማ ለሥራ ፍለጋ ወደ አዲስ አበባ የመጣው ወጣት ቴዎድሮስ መሀሪ ያሰበው አልተሳካለትም። ህይወት ፊቱን አዙራበት ሳያስበው የጎዳና ተዳዳሪ ሆኗል።
የጎዳና ህይወት እጅግ አስከፊ መሆኑን የሚገልጸው ቴዎድሮስ ከስምንተኛ ክፍል ወደ ዘጠነኛ ክፍል ቢያልፍም ከዚህ በላይ ትምህርቱን መቀጠል አልቻለም። የጎዳና ህይወትን ለሁለት ዓመታት ሲያሳልፍ ስቃይ የተሞላበት መሆኑን በምሬት ያስታውሳል።
“በክረምት ወቅት ዝናብ ሲኖር ወዴት እንደምትሄድ ይጨንቀሀል። ፖሊሶች ያባርሩሃል፤ ስትታመም የምትተኛበትና ህክምና የምታገኝበት ሁኔታ የለም። ስናገኝ የጉልበት ሥራ እንሠራለን ፣ ሥራ ሲጠፋ ደግሞ እንለምናለን፤ የሆቴሎች ትራፊ ምግብ እንበላለን። በየቆሻሻ ገንዳ እየዞርን የሚሸጡ ዕቃዎች እየፈለግን ለቁራሌው እንሸጣለን። የጎዳና ህይወት እኔንም ሆነ ጓደኞቼን የሲጋራና የጫት ሱሰኛ አድርጎናል” ሲል ሃሳቡን አጋርቶናል።
በጎዳና ህይወት እያለ ነው በእናቶችና ሕፃናት ዘርፈ ብዙ የልማት ድርጅት (MCMDO) አማካኝነት ከጎዳና ህይወት ወጥቶ ማገገሚያ ማዕከል የገባው። በማዕከሉም የምግብ፣ የአልባሳት፣ የመኝታ፣ የትምህርትና የምክር አገልግሎት እያገኘ መሆኑን ገልጾልናል። በማዕከሉ ባለሙያዎች በተሰጠው ምክርም በአሁኑ ጊዜ የጫት ሱስን ሙሉ ለሙሉ የተወ ሲሆን ሲጋራ የማጨስ መጠን ቀንሻለሁ ብሏል።
ስለ ብር አያያዝ፣ስለ ሰው አከባበር፣ቀጣይ ህይወትን እንዴት አድርገው መምራት እንዳለባቸው ትምህርት እያገኙ መሆኑን ገልጾ፣ከአሁን በኋላ ወደ ጎዳና ህይወት ላለመመለስ መወሰኑንም ይናገራል፤ የብድር አቅርቦት ካገኘም ከትንሽ ንግድ ተነስቶ ራሱን ለውጦ ራሱንና አገሩን ለመጥቀም ዕቅድና ፍላጎት እንዳለውም ገልፆልናል።
ካሊድ ጀማል ደግሞ 17 ዓመቱ ነው። የመጣው ከጅማ ሲሆን በ2010 ዓ.ም ለሥራ ፍለጋ በሚል እንደመጣና ለአንድ ዓመት ያህል ሆቴል ውስጥ መስተንግዶ ሲሠራ ቆይቶ የአረፋን በዓል ከቤተሰብ ጋር ለማሳለፍ ወደ አውቶቡስ ተራ ትኬት ሊቆርጥ ሲሄድ የተደራጁ ሌቦች ዓመት ሙሉ ሠርቶ ያገኘውን ገንዘብ እንደዘረፉት ነው የነገረን።
መሄጃ ሲያጣም ጎዳና ቤቴ ብሎ ከጎዳና አዳሪ እኩዮቹ መልካም ፈቃድ አግኝቶ ሊቀላቀል መቻሉን ያስታውሳል። “ጎዳና ላይ ስኖር የሱስ ተጠቂ አልሆንኩም፤ አብዛኛዎቹ ጓደኞቼ ግን የጫት፣የሲጋራና የቤንዚን ሱሰኛ ሆነዋል። እነሱ ጫት ሲቅሙ እኔ ፊልም ቤት ወይም በየጎዳና እየዞርኩ ጊዜዬን አሳልፍ ነበር” ብሏል። ከአራት ወራት የጎዳና ቆይታ በኋላ በእናቶችና ሕፃናት ዘርፈ ብዙ የልማት ድርጅት(MCMDO) አማካኝነት ከጎዳና ህይወት ሊወጣ የቻለው ወጣት ካሊድ።
በአሁኑ ወቅትም ቦሌ አየር መንገድ ካርጎ ፊት ለፊት በሚገኘው በድርጅቱ ማዕከል ውስጥ አልጋ፣ምግብና የህክምናና የትምህርት አገልግሎት እንደሚያገኙ ገልጾ፣ አሁን በድርጅቱ ድጋፍ ወደ ቤተሰቦቹ ተመልሶ ያቋረጠውን የሰባተኛ ክፍል ትምህርቱን ለመቀጠል መወሰኑንም ነግሮናል። ወደፊትም በትምህርቱ ውጤታማ ሆኖ እራሱን፣ ቤተሰቡንና አገሩን ለመለወጥ ሃሳብ እንዳለው አጫውቶናል።
የ16 ዓመቱ መሰረት አበበ ከጎጃም ዲማ ጊዮርጊስ ለሥራ ፍለጋ በሚል በ2008 ዓ.ም እንደመጣ ይናገራል። ሥራ ማግኘት ሲቸግረውና በቂ ገንዘብ ስላልነበረው የጎዳና ህይወት መጀመሩንም ይገልጻል። በጎዳና ኑሮውም አንድ ቀን ሲበላ ሌላ ጊዜ ሳይበላ አስቸጋሪ ጊዜያትን አሳልፏል። እግሩን ቆስሎም ለአንድ ዓመት ያህል ሲሰቃይ ቆይቷል።
አዲሱ ገበያ አካባቢ የጎዳና ህይወት ሲኖር የነበረው ወጣት መሰረት አባቱ በህይወት ያለመኖሩን፤ እናቱ ብቻዋን ሦስት ወንድምና እህቶቹን ማስተዳደሯንና ያሳደገችው አያቱ አቅሟ እየደከመ ሲመጣ ሦስተኛ ክፍል ትምህርቱን አቋርጦ ለሥራ ፍለጋ በሚል በ12 ዓመት ዕድሜው ወደ አዲስ አበባ እንደመጣ ነግሮናል።
“አራት ዓመታትን በጎዳና ህይወት አሳልፌያለሁ። የጎዳና ህይወት አስቸጋሪ ነው። በስሜት ወደ ሱስ ያስገባል፤ ረሃብና ጥማት ያጋጥማል። ብርዱ አይጣል ነው ፤የፖሊስ ዱላ አለ። በጥቅሉ ለሰው ልጅ የማትመኘው አስከፊ ህይወት ነው” ብሏል፤
‹‹በእናቶችና ሕፃናት ዘርፈ ብዙ የልማት ድርጅት የጎዳና ልጆች ማገገሚያ ማዕከል መሰረት ወደ ማዕከሉ ከገባሁ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለእግሬ ህክምና ተደርጎልኝ ተሽሎኛል። ምግብ በቀን ሦስቴ ነው የምንመገበው። በህይወት ክህሎት፣ በገንዘብ ቁጠባና በስነ ምግባር ትምህርት በማዕከሉ እየተሰጠን ነው›› ሲል ገልጾልናል።
“ከጎዳና ህይወት በመውጣቴ ታላቅ ስሜት እየተሰማኝ ነው” የሚለው ወጣቱ በማዕከሉ የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግለት ከሆነ የራሱ የፀጉር ቤት ከፍቶ መሥራትና ህይወቱን መለወጥ እንዲሁም ያሳደገችውን አያቱን መርዳት ምኞቱ መሆኑን አጫውቶናል።
በእናቶችና ሕፃናት ዘርፈ ብዙ የልማት ድርጅት የጎዳና ልጆች ማገገሚያ ማዕከል ለጎዳና ልጆቹ የህክምና አገልግሎት ሲሰጥ ያገኘነው ጤና መኮንን አብርሃም ጸጋው፣ በሠራተኛና ማህበራዊ ሚኒስቴር አማካኝነት የተመለመሉ የጎዳና ልጆች ወደ ማዕከሉ ሲገቡ ሙሉ ለሙሉ ልብስ የመቀየር፣ ፀጉራቸውን የመላጨት፣ የመኝታ፣ የምግብና የህክምና አገልግሎት እንደሚያገኙ ገልጸውልናል።
ከጎዳና ወደ ማዕከሉ ከመጡ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት አብዛኛዎቹ ልጆች የሱስ ተጠቂ በመሆናቸው የህክምናና የስነ አዕምሮ ህክምና የሚሰጣቸው መሆኑን ገልጸው፣ በተለይ ሲጋራ የሚጠቀሙ ልጆች በአንዴ ማቆም ስለሚከብዳቸው በሂደት የሚያጨሱትን ቁጥር እየቀነሱ እየቀነሱ ከሱስ ውስጥ እንዲወጡ የማድረግ ሥራ እንደሚሠራ አስረድተዋል።
የእናቶችና ሕፃናት ዘርፈ ብዙ የልማት ድርጅት(MCMDO) የአዲስ አበባ አካባቢ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ርዕሶም ሲሳይ፣ አንድ ሺህ 842 የጎዳና ሕፃናት ወደ ማዕከል እየገቡ መሆናቸውን እና ለሕፃናቱ አስፈላጊውን አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ነግረውናል።
የማህበራዊ አገልግሎት የጤናና ልማት ድርጅት(OSAD) አስተባባሪ አቶ በቀለ ሰንበቴ በበኩላቸው 895 የጎዳና ተዳዳሪዎችን ወደ ማገገሚያ ማዕከል በማስገባት ልጆቹ የባህሪ ለውጥ እንዲያመጡ፣ሠርተው እንዲለወጡና ቤተሰብ ያላቸው ወደ ቤተሰብ እንዲመለሱ የሚያደርግ የስነ ልቦና ስልጠና እየተሰጣቸው መሆኑን ነግረውናል።
“በልጆቹ ፍላጎት መሰረትም ወደ ቤተሰብ መመለስ የሚፈልጉት ይመለሳሉ፤ በትንሹ ሠርተው መኖር ለሚችሉ ስልጠናና ንግድ ለሚሰማሩት የብድር አቅርቦት ይመቻችላቸዋል፤ትምህርት የሚማሩት ደግሞ ወላጅ በማፈላለግ ድጋፍ እንዲያገኙ ይደረጋል” ብለዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የማህበራዊ ደህንነት ልማት ዳይሬክተር አቶ እንደሻው አበራ እንደገለጹት ከጥቅምት 1 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ አራት ሺ 132 ሕፃናት በልዩ ድጋፍ ምግብ ዋስትና ፕሮግራም አማካኝነት ከጎዳና ህይወት ወጥተዋል።
የልዩ ድጋፍ የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ዓላማው የጎዳና ተዳዳሪዎችን ከጎዳና ህይወት ማላቀቅ መሆኑን አመልክተው፣ መስፈርቱን አሟልተው በጨረታ የተለዩ ስምንት ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ዕድሜያቸው 18 እና ከዚህ በታች የሆኑ የጎዳና ተዳዳሪ ሕፃናት የመንከባከብና ከዚህ ህይወት እንዲወጡ የሚያስችሉ ሥራዎችን እየሠሩ መሆናቸውን አቶ እንደሻው ጠቁመዋል።
የልዩ ድጋፍ ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ተጠቃሚ መሆናቸው ካሉበት የጎዳና ህይወትና ደባል ሱስ ተላቀው እንደማንኛውም ሰው መደበኛ ህይወታቸውን የሚመሩበትን ሁኔታ ይፈጥራል ሲሉ አስረድተዋል። በ10 ክፍለ ከተሞች የሚገኙ አራት ሺ 132 የጎዳና ተዳዳሪ ሕፃናት ለአንድ ሰው የወር ወጪ አንድ ሺህ 500 ብር የተተመነ ሲሆን ጥቅል የሁለት ዓመት ወጪ 148 ሚሊዮን 752 ሺ ብር በኢትዮጵያ መንግሥትና በዓለም ባንክ ድጋፍ የሚሸፈን መሆኑን ነግረውናል።
አዲስ ዘመን ጥር 8/2012
ጌትነት ምህረቴ