በታላቁ የሕዳሴ ግድብ የደን ምንጣሮ ሥራ በዚህ ዓመት ሁለት ሺ የአካባቢው ሥራ አጥ ወጣቶች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ገለጸ። በቀጣዮቹ ዓመታት ቁጥሩ በእጥፍ እንደሚጨምርም አስታውቋል።
የክልሉ የሥራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ማኔጅመንት ቢሮ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈቃዱ ተሰማ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ የሕዳሴው ግድብ በክልሉ የሚሰራ በመሆኑ ውሃው የሚያርፍበት ቦታ ላይ የሚገኘውን ደን የመመንጠር ስራ ይከናወናል።
ስራውንም የክልሉ ማህበረሰብ በተለይም የክልሉ ሥራ አጥ ወጣቶች ተደራጅተው እንዲሰሩ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በዚህ ዓመት ብቻ ሁለት ሺህ ሥራ አጥ ወጣቶች ተደራጅተው በምንጣሮ ሥራው እንደሚሳተፉ የገለጹት አቶ ፈቃዱ፤ በቀጣዮቹ ዓመታት ደግሞ ቁጥሩ ከእጥፍ በላይ እንደሚጨምር ጠቁመዋል።
ወጣቶችን አደራጅተው ወደስራ ለማስገባት ከሕዳሴው ግድብ አመራሮችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ማድረጋቸውን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በግድቡ ዙሪያ ከሚገኙ ወረዳዎች ሥራ አጥ ወጣቶችን በበቂ መጠን በመመልመል የማራጀት ሂደቱን በማጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን ከፊሎቹም ወደ ስራ መግባታቸውንም አክለዋል።
አቶ ፈቃዱ እንደተናገሩት፤ የሕዳሴው ግድብ የግንባታ ሥራ በክልሉ ከሚገኙ አራት ወረዳዎች በሰዳል፣ ጉባ፣ ወምበራና ሸርቆሌ ይገኛል። በእነዚህ ወረዳዎች ይኖሩ የነበሩ አርሶ አደሮች በልማቱ ምክንያት ተነስተዋል። ከነዚህ ውስጥ ደግሞ የጉባና የሸርቆሌ ወረዳ አርሶ አደሮች ሰፊውን ቁጥር የሚይዙ ናቸው።
በመሆኑም አሁን ላይ የደን ምንጣሮ ሥራው በክልሉ ወጣቶች እንዲከናወን መደረጉ የእነዚህን ወረዳዎች ሥራ አጥ የማህበረሰብ ክፍል በሰፊው ተሳታፊ እንዲሆኑ በማድረግ የተረጋጋ ኢኮኖሚያዊ መሰረት መፍጠር እንደሚያስችል ተናግረዋል።
በህዳሴው ግድብ የምንጣሮ ስራ ለመሳተፍ ከሚጠባበቁ ሥራ አጥ ወጣቶች መካከል ሳምሶን ተስፋዬ እንዳለው፤ ሥራው በክልሉ ወጣቶች እንዲከናወን መደረጉ ከፍተኛ የሆነ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ፋይዳ አለው።
እንደ ወጣት ሳምሶን ገለፃ፤ የሚጀምሩበት ወቅት ስላልተገለፀላቸው የሚያስፈልጉ የመደራጀት ሂደቶችን በማከናወን በርካታ ወጣቶች ዝግጁ ሆነው እየተጠባበቁ ይገኛሉ።
ወጣት ዳንኤል ወንድሙ በበኩሉ፤ ለክልሉ ሥራ አጥ ወጣቶች እድሉ መሰጠቱ እንዳስደሰተው ገልጾ፤ ከዚህ በፊት በጉልበት ሰራተኛነት በመሰማራት አካባቢውን እንደሚያውቀውና አሁንም ለስራው ዝግጁ መሆኑን ጠቁሟል።
በአካባቢው ያለው ሙቀት ከፍተኛ ቢሆንም በስራው ላይ ተሰማርተው የምንጣሮ ስራውን ለማከናወን ወጣቶቹ ዝግጁ መሆናቸውንና እድሉ እንደሚሰጣቸው ከሰሙበት ጊዜ ጀምሮም አስፈላጊውን ሂደት በማከናወን ላይ እንዳሉም ወጣት ዳንኤል ተናግሯል።
መንግስት ስራውን የክልሉ ወጣቶች እንዲሰሩት አቅጣጫ ማስቀመጡ ፍትሃዊ የሀብት አጠቃቀም እንዲኖር የሚያደርግ መሆኑን የጠቀሱት ወጣቶቹ ፤ ይህንን አገራዊ ኃላፊነትን በብቃት መወጣት የሚያስችል ወኔ በመሰነቅ፣ የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ፣ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እንደሚያረጋግጡም ተናግረዋል።
ባለፉት ጊዜያት በነበሩት የደን ምንጣሮ ሂደቶች በርካታ ብልሹ አሰራሮች ተፈጥረው የአገር ሀብት ለብክነት መዳረጉ ይታወሳል።
አዲስ ዘመን ጥር 8/2012 ሙሐመድ ሁሴን