አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ በየዓመቱ ስምንት ሺህ የሚደርሱ ሰዎች ራሳቸውን እንደሚያጠፉ ጥናት አመለከተ። ራስን በራስ የማጥፋት ድርጊት የሥነ ልቦና ጫና ከማሳደሩም በላይ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስን እንደሚያባብስም ተገልጿል።
በጤና ሚኒስቴር የአዕምሮ ጤና ፕሮግራም ቡድን መሪ ዶክተር ደረጀ አሰፋ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ በሰጡት መረጃ፤ አንድ የማህበረሰብ አባል ራስን በማጥፋት ለህልፈት መዳረጉ ማህበራዊ ቀውስን እንደሚያስከትልና ለአገር ብዙ ጥቅም ሊሰጡ የሚችሉ ሰዎች ራሳቸውን ሲያጠፉ በሚባክነው ሀብት ምክንያት በቤተሰብም ሆነ በአገር ደረጃ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንደሚያስከትል ጠቁመዋል።
ወቅታዊ የሆኑ ሰፊ ጥናቶች ባይጠኑም ትንንሽ ጥናቶችና ዓለም አቀፍ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፤ በኢትዮጵያ ቢያንስ ከአንድ ሚሊዮን ሰዎች 80ዎቹ ራሳቸውን ያጠፋሉ የሚሉት ዶክተር ደረጀ ለማህበረሰቡ ዕድገትና ሌሎች በጎ መስተጋብሮች ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ሰው ማጣት ለማህበረሰቡም ብቻ ሳይሆን ለተቀሩት የቤተሰብ አባላትም የስነ ልቦና ጫና እያሳደረ ይገኛል ብለዋል።
ዶክተር ደረጀ፤ የማኅበራዊ ሳይንስ፣ የሥነ ልቡናና ሥነ ህይወት ልሂቃን አስተምሮን በማጣቀስ ራስን ለማጥፋት ከሚያነሳሱ ምክንያቶች ውስጥ በማህበራዊ ትስስር ላይ ያለ ክፍተት፣ በትዳር አለመጣመር፣ ትዳር መስርቶ ልጅ አለማግኘት፣ የወደዱትን ማጣት፣ ሰውን ለመጉዳት ራስ ላይ ርምጃ መውሰድ፣ የአካላዊ ጤንነት መጓደል፣ በአዕምሮ ስርዓት ውስጥ የኬሚካል ማነስ፣ ተጠቃሽ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በተደረጉ የዘረመል ጥናቶች የአንዳንድ ጂን ሁኔታዎችም ራስን የማጥፋት ፍላጎት መነሻ ሊሆን እንደሚችል የጠቀሱት ዶክተር ደረጀ ዕድሜያቸው ከ45 ዓመት በላይ የሆኑ ወንዶችና ከ55 ዓመት በላይ የሆኑ ሴቶች ራሳቸውን የማጥፋት ችግሩ ቀላል እንዳልሆነ የሚናገሩት ዶክተር ደረጀ፤ በኢትዮጵያ ባህል ሁኔታው በሚፈጠርበት ወቅት የተለያዩ ማህበራዊ ቀውሶችን በመፍራት እንዲህ ዓይነት ሞት በግልጽ የሚነገር ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ ቁጥሩ ከዚህም ከፍ ሊል እንደሚችል ተናግረዋል።
የችግሩ ስፋት በአገር፣ በማኅበረሰብና በቤተሰብ ደረጃ የሚገለጽ እንደመሆኑ የተለያዩ የጤና ተቋማትን ጨምሮ ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ጉዳዩን ትኩረት ሰጥተውበት በማቀድ መሥራት ይኖርባቸዋል ያሉት ዶክተር ደረጀ፤ ችግሩን ለመቅረፍም እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ቢኖሩም ውጤታማነታቸውን መፈተሽ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የአዕምሮ ህመም ራስን ለማጥፋት 95 በመቶ ያህል አስተዋፅኦ እንዳለውና ችግሩ ሥር ሳይሰድ በመለየት ሰዎች ህክምና እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በዓለም ላይ በዓመት 800 ሺ የሚሆኑ ሰዎች ራሳቸውን የሚያጠፉ ሲሆን ይህም በየ40 ሰክንድ ውስጥ ቢያንስ አንድ ሰው ራሱን ለህልፈት እንደሚዳርግ ያመላክታል።
አዲስ ዘመን ጥር 8/2012
አዲሱ ገረመው