አዲስ አበባ፡- በአማራ ክልል የሕዝቡን የውሃ አቅርቦት ለማሟላት አነስተኛ የውሃ ተቋማትን ግንባታ፣ የገጠር ባለ መስመር ውሃ ዝርጋታ እና የከተማ ውሃ አቅርቦት ስራ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ።
በአማራ ክልል ውሃ መስኖና ኢነርጂ ቢሮ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ዳይሬክተር አቶ አስራት ካሳዬ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፣ በክልሉ በተሰሩት ስራዎች በከተማ 75 በመቶ በገጠር ደግሞ 88 በመቶ የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋን ማድረስ ተችሏል፡፡
ባለፈው ዓመት ከ15 በላይ የከተማ የውሃ ተቋማትና ከ5 ሺህ በላይ አነስተኛ የውሃ ተቋማት ተገንብተው አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኙ የተናገሩት ዳይሬክተሩ፤ ከዓለም ባንክና ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በትብብር በከተማ 24፣ በገጠር 31 የውሃ ተቋማት ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህ በፊት በገጠር አካባቢዎች ይሰሩ የነበሩት አነስተኛ የውሃ ተቋማት የእጅ ጉድጓድና ምንጭ ማጎልበት ሲሆን ፣ አሁን ላይ ግን ባለመስመር የሆኑ እስከ 15 ቀበሌዎችን የሚያገናኙ ትላልቅና የብዙ ሰዎች የውሃ ፍላጎት የሚያሟሉ ተቋማት ናቸው ብለዋል፡፡
በክልሉ በተሰሩ የውሃ ተቋማት ሽፋኑን ባልተለመደ ሁኔታ አሳድጎታል ያሉት ዳይሬክተሩ፣ በከተሞች በቀን 20 ሊትር በሰው የነበረው ስሌት አሁን ላይ ዝቅተኛው 40 ከፍተኛው ደግሞ 80 ሊትር እንዲሆን አድርጓል ብለዋል።
በክልሉ ከተሰሩ የውሃ ተቋማት ከ20 በመቶ በላይ አገልግሎት መስጠት ማቆማቸው በቆጠራ እንደተረጋገጠ የተናገሩት አቶ አስራት፤ ይሄ ሁኔታ የተደራሽነት ሽፋኑን አሁን ከሚገኝበት ደረጃ ሊያሳንሰው እንደሚችል ግምታቸውን ተናግረዋል።
በክልሉ ውሃ ተደራሽ ያልሆነባቸው ወረዳዎችና ቀበሌዎች ምን ያህል እንደሆኑና የት አካባቢዎች እንደሚገኙ አዲስ ዘመን ላነሳላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ እንዳሉት፤‹‹ ውሃ ተደራሽ ያልሆነባቸው ወረዳዎች ባይኖሩም ቀበሌዎች ግን አሉ።ለድርቅ ተጋላጭ የሆኑት እንደ ምስራቅ በለሳ ያሉ ቀበሌዎች ሙሉ በሙሉ ውሃ የላቸውም። እስከ 60 ሜትር ተቆፍሮ ውሃ ማግኘት አልተቻለም። ዋግኸምራ አካባቢዎች ደግሞ እስከ 450 ሜትር ተቆፍሮ ውሃ ያልተገኘባቸው አካባቢዎች አሉ።
በሰቆጣ ከተማ የተቆፈረውም ቢሆን ከታሰበው በታች በግማሽ ያነሰ ውሃ ነው በመስጠት ላይ የሚገኘው ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ምክንያቱ ደግሞ የከርሰ ምድር ውሃ መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ በመምጣቱ የተፈጠረ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በመፍትሄነት የተወሰዱት ርምጃዎችም ከከርሰ ምድር ውሃ ጥገኝነት በመላቀቅ የገጸ ምድር ውሃን መጠቀም መሆኑን ጠቁመው፣ በሰቆጣ አካባቢዎች ያሉ 16 ቀበሌዎች ጥናት ተጠናቅቋል ብለዋል።ስራውን በማፋጠን በሚቀጥለው ዓመት ውሃ ማግኘት እንዲችሉ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በምስራቅ በለሳ አካባቢዎች ደግሞ ሀሙሲትን ጨምሮ 17 ቀበሌዎችን የሚያገናኝ ዲዛይን በመጠናቀቁ የከርሰ ምድር ውሃ ተጠቃሚ ይሆናሉ ሲሉ አቶ አስራት ካሳዬ አብራርተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 8/2012
ሙሐመድ ሁሴን