-የስንዴ ግዥ መጓተቱ የኑሮ ውድነትን ማባባሱ ተጠቁሟል
አዲስ አበባ፡- ከ234 የፌዴራል የመንግስት ተቋማት ውስጥ የግዥ ፍላጎታቸውን አሳውቀው ግዥ እየተፈጸመ ያለው ለ69ኙ ተቋማት ብቻ መሆኑን የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት አስታወቀ። የስንዴ ግዥ መጓተቱ ለኑሮ ውድነት አስተዋጽኦ ማድረጉም ተገልጿል።
የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ጽዋዬ ሙሉነህ ትናንት የድርጅታቸውን የስራ አፈጻጸም አስመልክተው እንደገለጹት፤ በአገሪቱ 189 የፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች ቢኖሩም ለአገልግሎቱ የግዥ ፍላጎታቸውን አሳውቀው ግዥ እየተፈጸመላቸው የሚገኘው ለ47ቱ ብቻ ነው። እንዲሁም በአገሪቱ ከሚገኙ 45 ዩኒቨርሲቲዎች የግዥ ፍላጎታቸውን አሳውቀው ግዥ እየተፈፀመ የሚገኘው ለ22 ብቻ ነው።
የተቋማቱ የግዥ ፍላጎታቸውን በወቅቱ አለማሳወቅ በአገልግሎቱ አሰራር ላይ ትልቅ ጫና እንዳለው የገለጹት ዋና ዳይሬክተሯ ተቋማቱ በራሳቸው የተዝረከረከ አሰራር ምክንያት ዘግይተው የግዥ ፍላጎታቸውን ሲያሳውቁ አገልግሎቱ በአቅራቢዎች ላይ አላስፈላጊ ጫና እንዲፈጥር እያደረጉ ነው ብለዋል።
በወቅቱ የግዥ ፍላጎታቸውን የሚያሳውቁ ተቋማት በማዕቀፍ ግዥ ለመፈጸም ጨረታ ሂደት ተጠናቅቆ አገልግሎቱ ከአቅራቢዎች ጋር ውል ቢታሰርም አቅራቢዎች ዕቃዎችን ከውጭ ለማስመጣት የውጭ ምንዛሬ በወቅቱ አለማግኘታቸው ግዥውን እንደሚያጓትተውም ጠቅሰዋል።
በአገልግሎቱ ከ400 በላይ የተለያዩ አይነት ዕቃዎች ግዥ የሚፈጸም መሆኑን አመልክተው ዕቃዎቹ በማዕቀፍ ግዥ መገዛታቸው ከፍተኛ የመንግስትን ወጪ መቀነስ መቻሉን ተናግረዋል። ለአብነት አንድ መስሪያ ቤት ኤል ሲዲ ፕሮጀክተር ለመግዛት ቢፈልግ ከነጋዴ የሚገዛበት የገበያ ዋጋ 23ሺ 885 ብር መሆኑን ገልጸው አገልግሎቱ ግን ዕቃውን በ14 ሺ 950 ብር የገዛው መሆኑን ገልጸዋል።
በአሁኑ ጊዜ አገልግሎቱ 409 ሚሊዮን 546 ሺህ 273 ብር የሚያወጡ የተለያዩ 48 የገዥ ውሎች መፈጸሙን፤ ለዩኒቨርሲቲዎችና መስሪያ ቤቶች አገልግሎት የሚውሉ 594 ሚሊዮን 903 ሺህ 049 ብር የቢሮ ዕቃዎች ውል ማሰሩን ገልጸው እንዲሁም ለፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶችና ለዩኒቨርሲቲዎች 430 ተሽከርካሪዎችና ለብሄራዊ ቤተመዛግብ ኤሌክትሮ መካኒካል ግዥዎችን ለመፈጸም ጨረታ ሂደት ላይ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ ንግድ ስራ ኮርፖሬሽንና በብሄራዊ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን 400 ሺህና 200 ሺህ ሜትሪክ ቶን ግዥ ጨረታዎች ቢወጡም በጨረታው ሂደት በተፈጠሩ ችግሮች ግዥውን በወቅቱ ማካሄድ አለመቻሉን አመልክተው የስንዴ ጨረታዎች መጓተትም በኑሮ ውድነት ላይ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውና እንደ አማራጭም መንግስት ከመንግስት ግዥ ለመፈጸም ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል ብለዋል። የ75 ሺህ ና 80 ሺህ ሜትሪክ ቶን የስንዴ ግዢ ጨረታ በሂደት ላይ መሆኑንም ተናግረዋል።
ቀደም ሲል አንድ የማዕቀፍ ግዥ ጨረታ ወጥቶ ውል ታስሮ ዕቃው እስኪመጣ ድረስ ከስድስት ወራት እስከ አንድ ዓመት ጊዜ እንደሚፈጅ አውስተው ከደረጃ መዳቢና ከተስማሚነት ምዘና ድርጅቶች ተቀራርቦ በመስራትና የአገልግሎቱን አሰራሮች በማሻሻል የጨረታ ሂደቱ የሚወስደውን ጊዜ በሁለት ወራት ማሳጠር መቻሉን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ 688 ተሽከርካሪዎች እንዲወገዱ ጥያቄ የቀረበ ቢሆንም መስሪያ ቤቶች ዲከላራሲዮንና ሊብሬ አሟልተው ባለማቅረባቸው ምክንያት የማስወገድ ስራው ሊዘገይ መቻሉን አመልክተው አገልግሎቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋጋር ተሽከርካሪዎቹን የማስወገድ የመጨረሻ ሂደት ላይ እንደሚገኙ አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ከአጠቃላይ ዓመታዊ በጀቷ 65 እስከ 70 በመቶ የሚሆነው የመንግስት ግዥ የሚውል ሲሆን ግዥ ዋነኛ የመንግስት የፖሊሲ ማስፈጸሚያ መሳሪያ መሆኑን ማሳያ መሆኑን ታውቋል።
አዲስ ዘመን ጥር 8/2012
ጌትነት ምህረቴ