- ሕገወጥ አጭበርባሪዎች አሁንም መኖራቸው ተጠቁሟል
አዲስ አበባ፡- ባለፉት ስድስት ወራት 10 ሺ 155 ዜጎች በሕጋዊ መንገድ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አረብ አገራት ለሥራ መሄዳቸውን የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ በሕገወጥ ወጥ መንገድ ዜጎችን ወደውጭ የሚልኩ አጭበርባሪዎች እንዳሉም ተጠቁሟል፡፡
የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ታዬ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ በውጭ አገር ተቀጥረው መሥራት የሚፈልጉ ዜጎች በሕጋዊ መንገድ ሄደው ክብራቸውና ደሕንነታቸው ተጠብቆ መሥራት እንዲችሉ ሰፊ ሥራ ተሠርቷል፡፡ የውጭ አገር የሥራ ስምሪት አዋጅ ከማውጣት ጀምሮ ከተቀባይ ቀጣሪ አገራት ጋር ሰፊ ውይይትና ድርድር ተደርጓል፡፡
በመሆኑም አሁን ላይ ዜጎች በሕጋዊ መንገድ ወደ ውጭ አገራት በተለይም ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አረብ አገራት ሄደው በመሥራት ላይ የሚገኙ ሲሆን ሳውዲ አረቢያ ሰባት ሺ 788፣ ኳታር ስምንት መቶ 23፣ ጆርዳን አንድ ሺ 101 እና የተባበሩት አረብ ኢምሬት አራት መቶ 43 ዜጎች በሕጋዊ መንገድ መሄዳቸውን ገልጸዋል፡፡
በተመሳሳይም ዜጎች በነፃ (ያለምንም ወጪ) ሄደው የሚሠሩባቸው ዕድሎች በመንግሥት በኩል ተመቻችተው እያለ በማታለልና በማጭበርበር ገንዝብ የሚቀበሉ አካላት መኖራቸውም ተደርሶበታል፡፡ አራት ኤጀንሲዎች ከሥራቸው ታግደዋል፤ በተጨማሪም ጉዳያቸው በሕግ በመታየት ላይ የሚገኙም እንዳሉ አስረድተዋል፡፡
የሄዱት ዜጎች በአብዛኛው በቤት ሠራተኛነት እና በጥበቃ ሠራተኛነት የሥራ ዘርፎች መሰማራታቸውን የገለጹት አቶ ደረጀ፤ ለሥራቸው አስፈላጊ የሆኑ ስልጠናዎችንም ከአንድ ወር እስከ ሦስት ወር ድረስ የወሰዱ ናቸው፡፡ በሚሠሩበት አገርም ሕጋዊ ሆነው፣ መብታቸው ተጠብቆና አስፈላጊው ክብር እና ክፍያ ሳይጓደልባቸው መሥራት ይችላሉ፡፡
ይሁን እንጂ አሁንም በተጭበረበሩ ሰነዶች በሕገወጥ መንገድ በመሄድ ለመብት ጥሰት፣ ለክብር መዋረድና ለስቃይ የሚዳረጉ ዜጎች መኖራቸውን መረጃዎች እንደሚደርሷቸው አብራርተዋል፡፡
አቶ ደረጀ እንዳሉት፤ ሚኒስቴር መስርያ ቤቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ሰፊ ክትትል እያደረገ ሲሆን በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች፣ ደላሎችና አጭበርባሪዎች ላይ የማያዳግም ርምጃ ለመውሰድ እየተሠራ ነው፤ ዜጎችም መንግሥት ያመቻቸላቸውን ዕድል አሳልፈው ለሌቦች መስጠት እንደሌለባቸው ገልጸዋል፡፡
በውጭ አገራት ሥራና ሠራተኛን በማገናኘት ከ750 በላይ ሕጋዊ ኤጀንሲዎች እንደተሰማሩ የገለጹት አቶ ደረጀ፤ በቀጣይ ሙያዊ ክህሎት በሚጠይቁ በሕክምና(ነርስ) እና በግንባታ ሥራዎች የሚሳተፉ ባለሙያዎችን ጭምር ለማቅረብ እንደሳውዲ አረቢያ ካሉ ተቀባይ አገራት ጋር በውይይት ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
እ.ኤ.አ አቆጣጠር ከጥር እስከ ሰኔ 2019 ባለው ጊዜ 57 ሺ 843 ኢትዮጵያውያን ለሥደት የተዳረጉ ሲሆን 260ዎቹ መመለሳቸውን የአለም አቀፍ ስደተኞች ድርጅት ሪፖርት ያሳያል፡፡ ኢኮኖሚያዊ ችግርም ለመሰደዳቸው በዋና ምክንያትነት ተጠቅሷል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 8/2012
ሙሐመድ ሁሴን