በሀገር ደረጃ ቀርቶ በክልላቸው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ሌሎችም ጉዳዮች ላይ ባይተዋር በመሆን ከሁለት አስርት አመታት በላይ ቆጥረዋል። የውሳኔ ሰጭነት ሚና ሳይኖራቸውም በእነዚህ አመታት በአጋርነት ከኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ጋር የቆዩት የአፋር፣ የጋምቤላ፣ የሱማሌ፣ የሐረሪና የቤኒሻንጉልጉሙዝ ክልሎች በኢህአዴግ 11ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ የውህደቱ መሰረት ተጣለ። ይህም መሰረት አጋር የነበሩ ፓርቲዎች በአገራቸው ጉዳይ ባይተዋር ከመሆን ወደ ወሳኝ አካል ለመሸጋገር አስቻለ።
በሀዋሳ ከተማ በተካሄደው ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ የተላለፈው ይህ ውሳኔ አጋር ለነበሩት ፓርቲዎች ልዩ ቀን ሆነች። ይህን ተከትሎም ስምንቱ ፓርቲዎች /አጋሮቹን ጨምሮ/ አንድ ሆነው የመሰረቱት ብልፅግና ፓርቲ የመጀመሪያ ስብሰባውን አድርጓል። ይህ ወቅት አጋር ይባሉ ለነበሩ ፓርቲዎች ታሪካዊ ቀን ናት፤ፓርቲዎቹ በአገራቸው ጉዳይ የመወሰን ስልጣን ተጎናፅፈው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ በመወሰንም ሆነ ሀሳብ በማመንጨት እንዲሁም ጉዳዩ ይጠቅማል አይጠቅምም በሚል አቋም ጭምር በመወያየት ታሪካዊ ቀናቸውን ጀምረዋል።
ስሜትን ፈጥሮባቸው ይሆን ስንል የሐረሪ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝና የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንቶችን ያለፈውን በማስታወስና አሁን የተፈጠረውን መነቃቃት እንዲህ አካፍለውናል።
‹‹አንዱ ባለቤት ሌላው አጋር ሆኖ ያለፈበትን የ28 አመት ጉዞ የሚቆጭ ነው›› ሲሉ የሚገልፁት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሌ ሐሰን የአጋር ድርጅቶች ውህደት የፈጠረው የደስታ ስሜት ቃላት የማይገልጸው ጥልቅ ስሜት እንደሆነ ይናገራሉ።
‹‹ተገፍቶ የነበረ አካል በአንድ ጠረጴዛ ላይ ለውይይት ሲጋበዝ እና ሀገራችንን በጋራ እናስተዳድር ሲባል ከዚህ በላይ ምን ደስታ አለ›› በማለት ውሳኔውም ትልቅ የፖለቲካ ውሳኔ እንደሆነና ሲጠብቁት የነበረ እንደሆነም ስሜት በተቀላቀለበት ሁኔታ ይገልፃሉ።
እርሳቸው እንደሚያስታውሱት የነበረው ከፋፋይ ሥርዓት ከፍተኛ የስነልቦና ጫና ያሳደረ፣ አመራሩ በራሱ እንዳይተማመን፣ነዋሪውም ኢትዮጵያዊ ስለመሆኑ እንዲጠራጠር ያደረገ በአጠቃላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ የፈጠረ ነበር። ስርዓቱ የተደበቀ ሴራም ነበረው ሲሉ ይወቅሳሉ። ውህድ ፓርቲው ስኬታማ ሆኖ እንዲቀጥልም ክልላቸው የሚችለውን ሁሉ እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል።
የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ውሳኔው ከልብ አስደስቷቸዋል። እርሳቸው እንደሚገልፁት ከመፈጸም ውጪ ተከራክሮ የማሳመንም ሆነ በማንኛውም ነገር ተሳትፎ አልነበራቸውም። አግላይ በሆነ ሥርዓት ውስጥ ነበር የቆዩት። ‹‹በአጋርነታችን እስከመቼ እንቀጥላለን?›› የሚል ጥያቄ በወቅቱ ስናቀርብ ይሰጠን የነበረው ምላሽ ‹ሐረሪ ክልል መሰረቱ አርብቶአደር ነው፤ ጎሰኝነቱም ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ ጋር የሚጣጣም አይደለም፤ በዚህ ምክንያትም ኢህአዴግ መሆን አትችሉም› የሚል ምላሽ ይሰጠን ነበር›› ርዕሰ መስተዳድሩ ምላሹ አሳማኝ እንዳልሆነና እነርሱን እንደማይገልጽ ለማስረዳት ቢጥሩም ተቀባይነት ሳያገኙ ለአመታት መዝለቃቸውን ያስታውሳሉ።
‹‹የኢትዮጵያ አንድ አካል ሆነን ግን በሀገር ጉዳይ ላይ ኦሮሚያ፣ትግራይ፣ደቡብና አማራ ክልሎች ናቸው በያገባኛል ስሜት ሲንቀሳቀሱ የነበሩት›› የሚሉት አቶ ኦርዲን ከውሳኔው ጊዜ ጀምሮ ውህደቱ እንደ ክልልና ሀገር ስላለው መልካም አጋጣሚና አስፈላጊነት ዙሪያ ጥናት በማካሄድ እንዲሁም ከህዝቡ፣ከድርጅት ከአባላትና ከደጋፊዎች ጋር የውይይት መድረክ በማዘጋጀት ምክክር መደረጉን አመልክተዋል።
የብልፅግና ፓርቲ መመስረት ሰላምንና ዴሞክራሲን በማረጋገጥ እንዲሁም መልካም አስተዳደርን በማስፈን የልማት ሥራዎችን ማጠናከርና ለሀገራዊ ምርጫም ዝግጁ መሆን እንደሚገባና ክልላቸውም በዚህ መልኩ እንደሚሰራ ተናግረዋል። በአሁኑ ጊዜ በየደረጃው ያለው የክልሉ አመራርና ነዋሪው በያገባኛል ስሜት ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ለማሸጋገር በእንቅስቃሴ ላይ መሆኑንም ገልጸዋል።
በድርጅታዊ ጉባኤው ላይ ውሳኔው ሲወሰን እርሳቸው ፕሬዚዳንት እንዳልነበሩ ያወሱት የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኡመድ ኡጁሉ የረጅም ጊዜ ጥያቄ መልስ ማግኘቱ የእርሳቸውም የክልሉ ነዋሪም ፍላጎትና ስኬት ጭምር እንደነበር ገልጸዋል።
አቶ ኡመድ እንዳስረዱት በነበረው አደረጃጀ ትና አካሄድ ደስተኞች አልነበሩም። እንደ ዜጋ አለመታየታቸው፣ በተለይም በአጋርነታቸው እስከ መቼ እንደሚቀጥሉ ለኢህአዴግ ጥያቄ ሲያቀርቡ ‹‹ጥያቄው ለአብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚሆን አይደ ለም›› በሚል የሚሰጠው ምላሽ ያናድዳቸው ነበር።
ከውህደቱ ወዲህ ያለውን ሁኔታ እንደተናገሩት ህገመንግሥታዊ መብታቸውን ተጠቅመው በእኩል መንፈስ በአገራዊ ጉዳይ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ‹‹አሁን ሀገር ሀገር ሆናለች። ልማትን እናፋጥናለን።›› ሲሉም ሃሳብ ሰጥተዋል። ክልሎቹ ሁሉን አቀፍ የሆነ በማህበራዊ፣በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካ ዕቅድ ነድፈው በእንቅስቃሴ ላይ እንደ ሆኑም ይናገራሉ።
አዲስ ዘመን ጥር 7/2012
ለምለም መንግሥቱ