አዲስ አበባ፡- ኢትዮ ቴሌኮም በስድስት ወራት 22 ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ። ገቢው ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ32 በመቶ ዕድገት እንዳለውም አስታውቋል።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ፍሬሕይወት ታምሩ የተቋሙን የ2012 በጀት ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ አፈጻጸም አስመልክተው ትናንት በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለጹት፤ ድርጅቱ ከመደበኛ የቴሌኮም አገልግሎቶች በተጨማሪ ሌሎች እሴት የሚጨምሩ ስድስት አዳዲስ እና 16 የተሻሻሉ የሀገር ውስጥ፣ የዓለምአቀፍ ምርትና አገልግሎቶችን ለገበያ በማቅረብ ባከናወኗቸው ተግባራት እና ተቋሙ በወሰዳቸው ሌሎች የአሠራር ማሻሻያዎች 22 ነጥብ አራት ቢሊዮን ገቢ ለማግኘት አስችሎታል።
ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ የተገኘውን ገቢ በአገልግሎት ዓይነት ሲያብራሩም፤ የሞባይል ድምጽ ገቢ ድርሻ 50ነጥብ አራት፣ የዳታና ኢንተርኔት ገቢ ድርሻ 27ነጥብ ሦስት በመቶ፣ የዓለምአቀፍ ንግድ ገቢ ድርሻ 9ነጥብ 8 በመቶ፣ እሴት ከሚጨምሩ አገልግሎቶች 8ነጥብ አምስት በመቶ፣ ከሌሎች አገልግሎቶች ደግሞ ሦስት በመቶ ድርሻ ያለው ሲሆን፣ ውጭ ምንዛሪ ከሚያስገኙ አገልግሎቶችም 73ሚሊዮን ዶላር ገቢ አግኝቷል።
ድርጅቱ እየሰጠ ባለው በኤሌክትሮኒክስ የአየር ሰዓት የብድር አገልግሎት በ17 ወራት ጊዜ ውስጥ 20ሚሊዮን ደንበኞች የአየር ሰዓት መበደራቸውንና በገንዘብም ስድስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በብድር ማዘዋወር መቻሉን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ጠቁመዋል።
ለማለማመድ ተብሎ በተሞከረው የዩኒቲ ፓርክ ጎብኚ ደንበኞች በተሰጠው አገልግሎት 23ሺ ደንበኞች ተጠቃሚ መሆናቸውንና ስድስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን አስረድተዋል። አገልግሎቱ ለዲጂታል ኢኮኖሚው መንገድ መክፈቱንም ገልጸዋል።
ለረጅም ጊዜ የገንዘብ ግብይት የለመደን ማህበረሰብ በአንድ ጊዜ ከለመደው ማስወጣት አስቸጋሪ እንደሆነና በሂደት ግን ወደተፈለገው አቅጣጫ በማምጣት የታለመውን ለማሳካት እንደሚቻል ገልጸዋል።
ተቋሙ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ አንድ መቶ ሚሊዮን ብር ያጣበት ስርቆትና የኃይል መቆራረጥ ባያጋጥመው አፈጻጸሙ አሁን ካዝመዘገበው በላይ ይሆን እንደነበር የጠቆሙት ሥራ አስፈጻሚዋ፤ እነዚህ ችግሮች እንዳይቀጥሉ አስፈላጊውን ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ፣ እርምጃዎችን በመውሰድ፣ ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ጋርም በመነጋገር ለችግሮች እልባት በመስጠት ቀጣዩን ጊዜ በተሻለ ለመፈጸም እንደሚሰራ ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 7/2012
ለምለም መንግሥቱ