አንድ ወጣት በትራፊክ ፖሊስ ተይዞ በመደናገጥ ስሜት በእጁ የያዘውን ወረቀት እያሳየው ያስረዳዋል:: መቼም ትራፊክ ፖሊስንና አሽከርካሪን የሚያገናኛቸው የትራፊክ ህግ ነው፤ አልኩ:: ወጣቱ የነበረበትን የክስ ቅጣት ሳይከፍል ዳግመኛ መቀጣቱ ነበር ያርበተበተው:: ክፍያው በባንክ የሚፈጸም እንደሆነና በወረፋ ምክንያት እንዳልከፈለም ያስረዳል:: እግረ መንገዴን ወጣትነትና የአሽከርካሪ ህግ አክባሪነት ላይ ሃሳቡን እንዲያካፍለኝ ጠየኩት:: ስላልተረጋጋ ሃሳቡን ሰብስቦ ሊያናግረኝ ባለመቻሉ ወደሌሎች ወጣት አሽከርካሪዎች አመራሁ::
ፒያሳ አካባቢ ነዋሪ የሆነው አማኑኤል ገብረአብ ላለፉት ስድስት አመታት መኪና አሽከርክሯል:: በዚህ ጊዜ ውስጥ አደጋ አላጋጠመውም:: የትራፊክ ህግ ተላልፎ ተቀጥቶ ግን ያውቃል:: ቅጣቱ ግን አላሳመነውም:: እርሱ እንደሚለው ትራፊክ ፖሊሱ ተንቀሳቃሽ ስልክ በእጁ መያዙን እንጂ ሲያነጋግርበት እንዳላየውና ሊያስረዳው ቢሞክርም ሊያምነው ባለመቻሉ ነው ቅጣቱን ያልተቀበለው::
ወጣት አማኑኤል ህግ አክባሪ እንደሆነም ነግሮኛል:: በጥንቃቄ ጉድለት ሊያጋጥም የሚችልን አደጋ ቀድሞ አለማሰብና ግድ የለሽነት ለአደጋ ከሚያጋልጡ ነገሮች መካከል እንደሆኑ ይጠቅሳል:: እርሱ መኪና በሚያሽከረክርበት ወቅት የመኪናውን አይነትና አቅም ግንዛቤ ውስጥ ይከታል:: በአሁኑ ወቅት ሀገር ውስጥ የሚገቡ አብዛኞቹ መኪኖች 10 አመትና ከዛ በላይ ያገለገሉ፣ አንዳንዶቹም መሪያቸው የዞረ በመሆናቸው ሊቆጣጠራቸው እንደሚችል አስቀድሞ የማረጋገጥ ልምድ አለው:: ይሄን የሚያደርገው የራሱንም የሌሎችንም ደህንነት ለመጠበቅ እንደሆነ ይገልፃል::
‹‹የሚቀጥለው ቀኔ ስለሚያጓጓኝ ይበልጥ እጠነቀቃለሁ እንጂ ቸልተኛ በመሆን ወይም ወጣትነቴ በራስ መተማመን አሳድሮብኝ ለአደጋ በሚያጋልጥ ሁኔታ ማሽከርከር የለብኝም:: ነገ በጡረታ ስገለል ተመችቶኝ የምኖርበትን ነገር አሁን መፍጠር አለብኝ ብዬ ነው የማስበው›› የሚለው ወጣት አማኑኤል፤ ወጣቱ አሽከርካሪ ለመሆን ሊጓጓ ይገባዋል ይላል:: ከጫት፣ ከመጠጥና ከሌሎችም ደባል ሱሶች ነፃ እንደሆነና አንዳንዴ ጓደኞቹ በመጠጥ መዝናናት ሲፈልጉ ለአሽከርካሪነት የሚመረጠው እርሱ እንደሆነም አጫውቶኛል:: ሰው ሰራሽ የሆነውን መኪና እንደጭንቅላት መቆጣጠር ስለማይቻል በመኪና አደጋ ህይወታቸውን ስላጡና ከፍተኛ አደጋ ስለደረሰባቸው ዜጎች ማሰብ ከእያንዳንዱ አሽከርካሪ ይጠበቃል ብሏል::
ህግ ማክበር ተገቢ እንደሆነ ቢያምንም በቅርቡ ተግባራዊ የሆነው ተሳፋሪዎች የደህንነት ቀበቶ ባለማሰራቸው እነርሱ መቀጣት ሲገባቸው ቅጣቱ አሽከርካሪው ላይ መወሰኑ ያበሳጫቸዋል:: ከማስተማር ይልቅ ቅጣት ላይ ትኩረት መደረጉንም ይቃወማል::
‹‹እኔ አንድ በጣም የምፈልገው ጉዳይ ቢያጋጥመኝ ስለምቀጣ ብዬ ህግ ከመተላለፍ ወደኋላ አልልም:: ስለዚህ ማስተማርና የግለሰቡን ሁኔታ መረዳት ይገባል›› ይላል አማኑኤል::ለተሽከርካሪ ምቹ የሆነ መንገድ አለመኖሩ እየታወቀ ግምት ውስጥ አለመግባቱም አግባብ እንዳልሆነ ይናገራል:: አደጋን መቀነስ ከአሽከርካሪው የሚጠበቅ እንደሆነ ግን ይገነዘባል::
የመኪናውን ደህንነት ማረጋገጥ፣የመንገዱንና የአየሩን ሁኔታ አይቶ በጥንቃቄ ማሽከርከር፣ ታጋሽና አስተዋይ እንዲሁም ከተለያዩ ተጽዕኖዎች ውጪ መሆን የአሽከርካሪው ኃላፊነት ነው ይላል:: ለአደጋ በሚያጋልጥ ሁኔታ ሲያሽከረክር የነበረን አንድ ሰው በመኪናው መንገድ ዘግቶ በማስቆም የሰራውን ስህተት በመንገር እንዲማር ያደረገበትን ጊዜም አስታውሷል::
‹‹ጠጥቼ ላሽከርክር ብል እንኳን የምነዳት መኪና አታስገባኝም:: በጩኸት ታስወጣኛለች›› በማለት ሃሳቡን ያካፈለኝ መርካቶ ኳስሜዳ ተብሎ በሚጠራው ሰፈር ነዋሪ ወጣት እሱባለው ተካ የሰጠው ሃሳብ ግራ ስላጋባኝ ጠይቄው እንደነገረኝ:: መጠጥ የጠጣ ተሳፋሪም እንዳይገባ ሚኪናዋ ድምጽ እንድታሰማ መሳሪያ ተገጥሟል:: በመሆኑም ወይ መጠጥ ወይንም መኪና ማሽከርከር ምርጫ ውስጥ ይገባል:: ወጣት እሱባለው የያዛት መኪና የሥራ በመሆኗ ሳይወድ በግድ ከመጠጥና ደባል ሱስ ርቋል:: ይሄ ደግሞ ለጤንነቱ ጠቅሞታል:: ከአደጋም እንዲጠበቅ አግዞታል::
ጫት እየቃሙና መጠጥ እየጠጡ የሚያሽከረክሩ ወጣቶች የሌሎችንም ዜጎች ህይወት ይዘው ለመጥፋት የተዘጋጁ ናቸው ሲል ይገልጻቸዋል:: ከትራፊክ ህግ ሥነ ምግባር ውጪ እንደሆነና ሁሉም ነገር ቦታና ጊዜ እንዳለው ይገልጻል:: ሁለት ነገር በአንድ ጊዜ መስራት ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝንም ይናገራል:: ከአደጋው ይልቅ የትራፊክ ፖሊሱን የሚፈሩ መኖራቸውን ታዝቧል:: አዩኝ አላዩኝ የሚለው አካሄድ ይበልጥ ችግር ውስጥ እንደሚከትም ከአንዳንዶች ተገንዝቧል:: ወጣቶች እንዲህ ካለው ድርጊታቸው እንዲታቀቡ መክሯል::
ላለፉት አምስት አመታት መኪና ያሽከረከረው በአራዳ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 02 ነዋሪ ወጣት መሐመድ ሰፋ ተሳፋሪ የደህንነት ቀበቶ ማሰር እንዲተገበር እየተከናወነ ያለው ጥብቅ ቁጥጥር አስደስቶታል::
ለራስ ደህንነት ጥንቃቄ ማድረግ ሲገባ ቸልተኛ መሆን አግባብ እንዳልሆነ ይገልጻል:: ቅጣቱ አንድ ሺ ብር ቢሆን ይስማማል:: በአጠቃላይ የትራፊክ ህግን የሚተላለፉ አሽከርካሪዎች ከፍተኛ ገንዘብ ቢቀጡ ይመርጣል:: የቅጣት አነስተኛ መሆን አሽከርካሪው እንዲዘናጋ እና ግዴለሽ እንዲሆን እንዳደረገው ይገልጻል:: በተለይ ወጣቱ ከቅጣቱ ተምሯል ብሎ አያምንም:: በግሉ የሚያሽከረክራትን መኪና ደህንነት ለመጠበቅ በባለሙያዎች ከማስፈተሽ ጀምሮ ማድረግ የሚገባውን ጥንቃቄ እንደሚያደርግ ነግሮኛል:: እስካሁንም አደጋ እንዳላደረሰና የትራፊክ ህግንም የሚተላለፍ ተግባር አለመፈጸሙን አጫውቶኛል::
ስለ ወጣት አሽከርካሪዎች የምትናገረው በሥራ ላይ ያገኘኋት ኮንስታብል ገነት ተሰማ እንደነገረችኝ ብዙዎቹ እያሽከረከሩ ስልክ ያወራሉ:: የደህንነት ቀበቶ አያስሩም:: ቸልተኞች ናቸው:: ከቅጣት ማስተማርን ብታስቀድምም:: ችግሩ ካልተቀረፈ ትቀጣለች:: ባነጋገርኳት ወቅትም አንድ ወጣት አሽከርካሪ እየቀጣችው ስለነበር ጉዳዩን ጠይቄያት በሰጠችው ምላሽ፤ የጫናቸው ተሳፋሪዎች የደህንነት ቀበቶ እንዲያስሩ ባለማድረጉ መቅጣቷን ትናገራለች:: በተለያየ የመገናኛ መንገድ ትምህርት በመሰጠቱ አሁን ቅጣት ተጀምሯል::
አዲስ ዘመን ጥር 7/2012
ለምለም መንግሥቱ