በገጠር ሥራ ዕድል ፈጠራ መልካም ተሞክሮ ያላቸውና ከመላ ሀገሪቱ የተመረጡ ትጉህ ሠራተኞች በተለይም ወጣቶች ከጥር 2 እስከ 4 2012 ዓ.ም በተካሄደው ኤግዚቢሽንና ባዛር ላይ ለመሳተፍ በባህርዳር ከተማ ተገኝተዋል። ተሞክሮን መለዋወጥ፣ የገበያ ትስስርን መፍጠር፣ ማበረታታትና እውቅና መስጠት የዚህ መርሃ ግብር ዋና ዋና ዓላማዎች ናቸው።
የገጠርና የከተማ ሥራ ዕድል ፈጠራዎችን ማስተሳሰርና ተመጋጋቢነታቸውን ማስቀጠልም ሌላው ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነው። በግብርና ሚኒስቴር አስተባባሪነት እየተተገበረ ያለው የገጠር ሥራ ዕድል ፈጠራ ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ተስተውለውበታል። ሕይወታቸውን የቀየሩ ወጣቶችም ተፈጥረዋል።
ዮሴፍ ላንዳቦ በደቡብ ክልል ሀዲያ ዞን ሌሞ ወረዳ ጉራ ጡሜ ቀበሌ ነዋሪ ነው። ዮሴፍ በሚኖርበት የገጠር መንደር በከተማ አካባቢ እየተሰሩ የሚመጡ በርና መስኮቶችን በመግጠም ነበር የሚተዳደረው።
ኋላ ግን በገጠር ሥራ ዕድል ፈጠራ መርሃ ግብር ‹‹ጆሲ አንድነት ብረታ ብረት›› በሚል የማህበር ስም ከሦስት ሴትና ሁለት ወንድ ጓደኞቹ ጋር በመደራጀት ብድር ወስደው ወደ ሥራ ገቡ።
ቀደም ሲል ተሰርተው የሚቀርቡ በሮችን እንደሚገጥሙ የሚናገረው ዮሴፍ አሁን ግን እርሱ እና ጓደኞቹ በራሳቸው ጥረት የመበየጃ ማሽን በመስራት እዚያው በሚኖሩበት የገጠር ቀበሌ ለአዳዲስ ቤት የሚሆኑ በሮችንና መስኮቶችን እየሰሩ በመግጠም ይተዳደራሉ። እነ ዮሴፍ የኤሌክትሪክ ምጣዶችን፣ ስቶቮችንና ሌሎች መገልገያዎችን በመስራት ገቢያቸውን እያሳደጉ ይገኛሉ።
በአካባቢው የሚኖሩ ማህበረሰቦችም ዘመናዊ ሕይወትን እንዲላመዱና የእንጨት ጥገኝነታቸውን እንዲቀንሱ ማድረጋቸውን ይናገራል። በ38 ሺ ብር የተጀመረው ካፒታላቸው በአጭር ጊዜ ከ2 መቶ አርባ ሺ ብር በላይ ደርሷል። እነ ዮሴፍ የመበየጃ ማሽኖችን እየሰሩ በመሸጥ ለሌሎች ወጣቶችም ማሽኖቹን ተጠቅመው በብየዳ ሥራ ላይ እንዲሰማሩ አድርገዋል።
መምህር እንቢአለ መርከቡ በአማራ ክልል አዊ ዞን እንጂባራ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ መምህርና የኮሌጁ ዲን ነው። መምህር እንቢአለ ከውጭ ሀገር የሚገባውን ኢንኩቤተር (እንቁላል ማስፈልፈያ) ሊተካ የሚችል ማሽን በመስራት የከተማና የገጠር ሥራ ዕድል ፈጠራን ተመጋጋቢነት ያመላከተ ሥራ ይዞ ቀርቧል።
ማሽኑ በዶሮ እርባታ ላይ መሰማራት ለፈለጉ የገጠር ቀበሌዎች ትልቅ ጥቅም አለው ይላል። እንዲህ ዓይነት ማሽኖችን እየፈጠሩ ማቅረብ የውጭ ምንዛሬን ከማስቀረቱም በተጨማሪ የገጠርና የከተማ ሥራ ዕድል ፈጠራን የሚያስተሳስር ነው ይላል።
ከውጭ የሚገቡት እንቁላል ማስፈልፈያ ማሽኖች ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ በመሆናቸው በቀላል ብድር ወደ ሥራ ለሚገቡ ወጣቶች አመቺነት እንደሌላቸው የገለጸው ወጣቱ ከፍ ያለ አቅምን የማይጠይቁ ማሽኖችን ማምረት መንግሥት ለያዘው አቅጣጫ አቅም ነው ብሏል። ስለሆነም በዶሮ እርባታ ላይ ለመሰማራት ለሚፈልጉ ወጣቶች እንዲህ ዓይነቱ ማሽን ምቹ እንደሆነም ይናገራል።
መምህር እንቢአለ የሰራው የእንቁላል ማስፈልፈያ እስከ አንድ ሺ ሁለት መቶ ጫጩቶችን ማስፈልፈል እንደሚችልም ጠቁሟል። ማሽኑ ፍተሻ ተደርጎበት አዋጭነቱ እንደተረጋገጠ በመግለጽ ዋጋ ለመቀነስ የሚያስችሉ ማሻሻያዎች ተደርጎለት ለሽያጭ እንደሚውል አስረድቷል።
የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እንዲህ ዓይነት ማሽኖችን በየዞኑ ለጥቃቅን ኣና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች እያደራጁ ቢሰጧቸው ከዶሮ ብዜትና እርባታ ጋር ያለውን ችግር ለመፍታትና የወጣቶችንም ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያስችላል።
ሳህለምህረት ኪዳነወልድ የባህርዳር ከተማ ነዋሪ ስትሆን የዶሮ መኖ በማዘጋጀት በጅምላ ታከፋፍላለች። በአካባቢዋ እንደ ዋዛ የሚወድቀውን የዓሣ ተረፈ ምርት ለዶሮ መኖነት በማዘጋጀት ከፍ ሲልም ከተለያዩ ቦታዎች የተለያዩ መኖዎችን በማቅረብ ትሸጣለች። በዚህም እራሷንና ቤተሰቦቿን ታስተዳድራለች።
ሳህለምህረት እንደምታስረዳው እንደዋዛ ከሚወድቀው የዓሣ ተረፈ ምርት የዶሮ መኖን በማዘጋጀት በዶሮ እርባታ ለተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች በሽያጭ ማቅረቧ የተፈጠረላት የሥራ ዕድል በዘርፉ ለተሰማሩ ሌሎች ወጣቶች ሌላ ሥራ እንደሚፈጥር ትገልጻለች። በከተማ የሥራ ዕድል ፈጠራ የዶሮ መኖን ማቅረቧ በገጠር በዶሮ እርባታ ከተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ጋር እንደሚያስተሳስራትም ተናግራለች።
በግብርና ሚኒስቴር የገጠር ሥራ ዕድል ፈጠራ ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ በቀለ እንደገለጹት፣ የግብርናው ዘርፍ ለገጠር ሥራ ዕድል ፈጠራ ያለውን ትልቅ አቅም መጠቀም የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫ ነው። ይህም ከገጠር ወደ ከተማ የሚፈልሰውን ሥራ አጥ ወጣት ችግር ለመቅረፍ ያስችላል። ከ2008 እስከ 2011 ዓ.ም በገጠር ሥራ ዕድል ፈጠራ ሦስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ገልጸዋል።
በሚቀጥሉት አሥር ዓመታትም አሥር ነጥብ አምስት ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል ለመፍጠር መታቀዱን ተናግረዋል። ወጣቱ የሥራ ፈጠራ አመለካከቱን በማሳደግ፣ የገበያ ትስስርና የእሴት ሰንሰለትን መሠረት ያደረጉ የሥራ ዘርፎች ላይ በማተኮር፣ የመረጃና የክህሎት ማነስ ክፍተቶቹን በመድፈን የገጠር ሥራ ዕድል ፈጠራን ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያሸጋገርበት ዕድል እንደሚፈጠርለት አቶ ስለሺ ጠቅሰዋል።
‹‹የገጠር ሥራ ዕድል ፈጠራ ለሀገር ብልጽግና›› በሚል መልዕክት በተከበረው ኤግዚቢሽንና ባዛር ላይ የተገኙት የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ካባ ኡርጌሳ እንዳስረዱት፣ ወጣቶችና ሴቶች ሀገራዊ ዕድገቱ ከሚፈጥረው ምቹ ሁኔታና ከሚገኘው ውጤት ፍትሀዊ ተጠቃሚና ተሳታፊ እንዲሆኑ መንግሥት ጥረት እያደረገ ነው።
በዚህም መሠረት በሁለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን ለ4 ነጥብ አንድ ሚሊዮን ዜጎች በገጠርና መከተማ የሠራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል። የሚፈጠሩ የሥራ ዕድሎችን የተሳሰሩና የተመጋገቡ ማድረግም በቀጣይ ትኩረት የሚያሻው ጉዳይ ነው።
አዲስ ዘመን ጥር 7/2012
ኢያሱ መሰለ