አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የግብይት ሥርዓቱን ዘመናዊነት ለማጠናከርና ለማስፋፋት ከዘመን ባንክ ጋር የክፍያ አጋርነት ስምምነት ተፈራርሟል።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድምአገኘሁ ነገራ ትናንት ስምምነቱ በተደረገበት ሥነ ሥርዓት ላይ እንደገለጹት፣ ዘመናዊ የክፍያ አፈጻጸም ስምምነቱ ተገበያዮች ክፍያቸውን በተቀላጠፈ መልኩ ማካሄድ እንዲችሉ አማራጭ ከመስጠቱም በተጨማሪ ተደራሽነትን በማስፋት የግብይት ሥርዓቱን ይበልጥ ያግዛል።
ምርት ገበያው ለሀገራችን የውጭ ንግድ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ምርቶችን ወደ ግብይት ሥርዓቱ በማስገባት ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችል የጠቆሙት አቶ ወንድምአገኘሁ፤ ግብይቶችና አገልግሎቶች በሕጋዊ የፋይናንስ ሥርዓት ውስጥ ስለሚያልፉ ከምርት ገበያው ጋር የሚሰሩ ባንኮች የደንበኞቻቸውን ቁጥር እንዲያሳድጉና የአገልግሎት አድማሳቸውን እንዲያስፋፉ ይረዳቸዋል ብለዋል። ዘመን ባንክም ዘመናዊ የግብይት ሥርዓቱን መቀላቀሉ የአሠራር ሥርዓቱን ለማጠናከር ሌላ አቅም እንደሚሆን ገልጸዋል።
አቶ ወንድምአገኘሁ እንደገለጹት፤ ወደ ግብይት ሥርዓቱ የሚገቡ አቅራቢዎች፣ ህብረት ሥራ ማህበራትና ላኪዎች የዚህ ክፍያ ሥርዓት ተገልጋይና ተጠቃሚ ስለሚሆኑ ለጤነኛና ሕጋዊ የገንዘብ ፍሰት አስተዋጽኦ አለው።
ዘመን ባንክ አስተማማኝ የክፍያ ሥርዓትና ጤናማ የገንዘብ ዝውውር እንዲኖር ላበረከተው አስተዋጽኦ ምስጋና ያቀረቡት አቶ ወንድምአገኘሁ፣ አጋርነታቸው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።
የዘመን ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደረጀ ዘበነ በበኩላቸው ባስተላለፉት መልዕክት የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዘመን ባንክ ወደ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓቱ እንዲገባ ላደረገው ድጋፍና አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።
ዘመን ባንክ አክሲዮን ማህበር ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ድርጅት አባል እንዳልነበር ገልጸው ባንኩ ተደራሽነቱን እያሰፋ ለመሄዱ የያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ስምምነቱ መልካም አጋጣሚ እንደሆነ ተናግረዋል።
በሀገራችን ወሳኝ የሆነውን የውጭ ንግድ ለመደገፍ እና የክፍያ ሥርዓቱን ዘመናዊና ቀልጣፋ ለማድረግ ይረዳል ብለዋል። የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ድርጅት የሀገሪቱ የግብይት ሥርዓት በቦታ እንዳይወሰንና ቀልጣፋ የክፍያ ሥርዓት ለመፈጸም የሚያስችል አሠራር መዘርጋቱ የእድገት ማሳያ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ስምምነቱ የባንኩ ደንበኞች ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል በመሆኑ ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው ያስረዱት አቶ ደረጀ በተለይም በወጪ ንግድ ለተሰማሩ የባንኩ ደንበኞች የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት አመቺነት ያለው እንደሆነ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ 21 ሺ የሚጠጉ ደንበኞች የሚሳተፉበት የግብይት መደረክ ሲሆን 5 ሺ 250 የባንክ ሂሳቦች ይንቀሳቀሱበታል። እስከ አሁን ከአስራ ስድስት ባንኮች ጋር በጥምረት እየሰራ እንዳለና ዘመን ባንክ አስራ ሰባተኛ ሆኖ የግብይት ሥርዓቱን እንደተቀላቀለ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 7/2012
ኢያሱ መሰለ