አዲስ አበባ:- ቀጣዩ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ ሴቶች እና እናቶች ከቤተሰብ ጀምሮ ሰላምና አንድነትን ማስተማር እንዳለባቸውም ተገለጸ።
ትናንት በሚሌኒየም አዳራሽ በተካሄደ ከተማ አቀፍ የአዲስ አበባ ሴቶች መድረክ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ እንደተናገሩት፣ የኢትዮጵያ ብልጽግና እውን እንዲሆን የሴቶች እና እናቶች ሚና ከፍተኛ ድርሻ አለው።
ሴቶች እና እናቶች ስለ ሰላም፣ ፍቅርና አንድነት ዘወትር ማስተማር አለባቸው ሲሉ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ሴቶች እና እናቶች ከቤተሰብ ጀምሮ የሚያደርጉት አርአያነት ያለው አስተምህሮ ምርጫው ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚኖረው ፋይዳ የጎላ መሆኑንም ገልጸዋል።
በዚሁ “በህብር ወደ ብልጽግና” በሚል መሪ ቃል በተዘጋጀ መድረክ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብዙ የሚጠበቁ ጉዳዮች እንዳሉ የተናገሩ ሲሆን ከትችት በመላቀቅና ከማይፈለግ አተካራ በመውጣት ጊዜአቸውን የተለያዩ ማህበራዊ ተሳትፎዎችና እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ከኅብረተሰቡ ጋር መዋሀድና መገናኘት እንዳለባቸው ጠቁመዋል። በተቻላቸው አቅም ሁሉ የዴሞክራሲ ባህልን በተመለከተ ልምምድ እንዲያደርጉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ያለው የልማት እንቅስቃሴ በሌሎች ከተሞች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለብልፅግና ፓርቲ መመስረት ዋናው ምክንያት ከአንድነት ወደ መለያየት በመሄድ ላይ በመሆናችንና ያንን አደጋ በመቀልበስ ወደ ነበረው አንድነታችን መመለስ አስፈላጊ በመሆኑ እንደሆነም ተናግረዋል።
ቀደም ሲል በነበረው አደረጃጀት እና ሲካሄድ በነበረው የልማት አካሄድ ድህነትን ማጥፋትና ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ አልተቻለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ፤ ይህም ሌላው ብልፅግና ፓርቲ እንዲፈጠር ያደረገ ምክንያት ሆኗል ብለዋል።
በመድረኩ ላይ ከ20 ሺህ በላይ የከተማዋ ሴቶች፤ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የፌዴራልና የከተማ አስተዳደር ኃላፊዎች፣ የተለያዩ ድርጅቶች ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች መገኘታቸውን ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያገኘነው መረጃ ጠቁሟል።
አዲስ ዘመን ጥር 7/2012
በጋዜጣው ሪፖርተር