-ዘጠኝ ሚሊየን ብር የሚገመት ህገወጥ የእንስሳት ግብይት በቁጥጥር ስር ውሏል
አዲስ አበባ:- የአበርገለ አለም አቀፍ እንስሳት ሀብት ልማት ድርጅት ቀጣይነት ያለው የቁም እንስሳት አቅርቦት ባለማግኘቱ ማምረት ከሚገባው የስጋ ምርት 10 ከመቶ ብቻ እያቀረበ መሆኑ ተገለጸ። በህገወጥ መንገድ ከአገር ሊወጡ የነበሩ ግምታቸው ከዘጠኝ ሚሊዮን ብር በላይ የሆኑ የቁም እንስሳት በቁጥጥር ስር ማዋሉን የጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ።
የድርጅቱ የማርኬቲንግ መምሪያ ኃላፊ አቶ አማኑኤል ግደይ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ የቁም እንስሳት በህገወጥ መንገድ ከሀገር ስለሚወጡ ቀጣይነት ያለው አቅርቦት ባለማግኘቱ ማምረት ከሚገባው የስጋ ምርት በታች እያመረተ ነው።
እንደ ኃላፊው ማብራሪያ፤ ፋብሪካው በሶስት ፈረቃ የሚሰራ ሲሆን፤ በአንድ ፈረቃ ብቻ 240 በሬዎች፣ 960 በግና ፍየሎች እርድ በማከናወን ምርቱን ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ የማቅረብ አቅም አለው።
ከ2004 እስከ 2006 ዓ.ም በሶስት ፈረቃ በሙሉ አቅሙ እርድ በማከናወን ምርቱን ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ሲያቀርብ ነበር ያሉት ኃላፊው፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ ህገወጥ የእንስሳት ዝውውር እያደገ መምጣቱ በአገሪቱ የመጣውን ፖለቲካዊ ለውጥ ተከትሎ የተፈጠሩ አለመረጋጋቶች፣ የቁም እንስሳት አቅርቦት በተመጣጣኝ ዋጋ ገበያው ላይ አለማግኘት ማምረት ከሚገባው አቅሙ 10 በመቶ የሚሆነውን ብቻ እንዲጠቀም እንዳስገደደው ጠቁመዋል።
ድርጅቱ ምርቱን ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚያስችለው የምስክር ወረቀት ቢኖረውም አሁን ላይ በቀን ከ15 ያልበለጡ በግና ፍየሎችን እንዲሁም ከ40 እስከ 50 የሚሆኑ በሬዎች ብቻ ነው የሚያርደው ያሉት ኃላፊው ፤ በአገር ውስጥ ያለው የእንስሳት ዋጋና ድርጅቱ ምርቱን ለውጭ ገበያ የሚያቀርብበት ባለመጣጣሙ ምርቱን ለውጭ ገበያ መላክ አለመቻሉን አስረድተዋል።
አቶ አማኑኤል እንዳሉት፤ በአገር ውስጥ የአንድ ኪሎ ስጋ ዋጋ በአማካኝ ከ250 እስከ 350 ብር ነው፤ ለውጭ ገበያ የሚቀርበው ደግሞ ከአራት ነጥብ አራት እስከ አምስት ዶላር ነው። ይህም በወቅቱ ባለው የምንዛሬ ዋጋ ሲሰላ አንድ ኪሎ ስጋ ለውጭ ገበያ የሚቀርበው 150 ብር ነው። ስለዚህ ድርጅቱ በኪሳራም ቢሆን ምርቱን ወደ ውጭ ልኮ አገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ታግኝ ቢባል እንኳን ገበያው ላይ ቀጣይነት ያለው የእንስሳት አቅርቦት ባለመገኘቱ አስቸጋሪ ነው።
ኢትዮጵያ በቁም እንስሳት ሀብቷ ከቀዳሚዎቹ ተርታ የምትጠቀስ ቢሆንም፤ የኮንትሮባንድ ንግዱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ገቢ እንዳታገኝ አድርጓታል ያሉት አቶ አማኑኤል፣ በሌላ በኩልም መንግስት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት አናሳ መሆን ድርጅቶችን ከጨዋታ ውጪ አድርጓቸዋል ብለዋል። በመሆኑም ለዘርፉ ተገቢው ትኩረት እንዲሰጠው ጥሪ አቅርበዋል።
በጉምሩክ ኮሚሽን የጉምሩክ ህግ ተገዥነት ዘርፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሸናፊ ባሳ በበኩላቸው፤ ኮሚሽኑ ህገወጥነትን ለመከላከል የአገሪቱ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ ላይ የዳሰሳ ጥናት በማድረግ መተላለፊያ መስመሮች የሚባሉ አካባቢዎችን በመለየት ቀድሞ የነበረውን 55 የመቆጣጠሪያ ኬላ ወደ 94 ከፍ የማድረግ ስራ መሰራቱን ጠቁመዋል።
እነዚህ ተጨማሪ ኬላዎች ወደ ስራ በመግባታቸው ኮንትሮባንዱ ላይ ጠበቅ ያለ ቁጥጥር ለማድረግ ማስቻሉን የሚናገሩት ኃላፊው፤ የጉምሩክ አዋጅ 859/2006 መሰረት ህጋዊ ስርዓትን ያልተከተሉ ሸቀጦች፣ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች፣ ምግብና መጠጥ ነክ ነገሮች፣ አልባሳት፣ የግብርና ምርቶች፣ የቁም እንስሳትና ሌሎችንም በህገወጥ መንገድ ከአገር የሚያወጡና የሚያስገቡ ላይ ከፍተኛ የሆነ የቁጥጥር ስራ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል::
የቁጥጥር ስራው በተከናወነባቸው ባለፉት አምስት ወራት ግምታቸው ከዘጠኝ ነጥብ አራት ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆን 810 በሬዎች፣ 181 ላሞች፣ 299 በጎች፣ 45 ወይፈኖችና መሰል የቁም እንስሳት በህገወጥ መንገድ ከአገር ሊወጡ ሲሉ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቀዋል።
ከዚህም ባሻገር በህገ ወጥ ስራው ላይ ተሳታፊ የነበሩ 709 ተጠርጣሪዎች መገኘታቸውን ገልጸው 504ቱ በህግ ቁጥጥር ስር ውለው ምርመራቸው ተጠናቆ ጉዳያቸው ወደ ፍርድ ቤት መላኩን አቶ አሸናፊ ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል በገንዘባቸውና በንብረታቸው እንዲሁም ሌሎች ሰዎችን በመጠቀም በተዘዋዋሪ በህገ በወጥ ስራው ላይ ተሳታፊ የነበሩ 205 ሰዎች እስካሁን የፌዴራል ፖሊስና የክልል የጸጥታ መዋቅሮች ክትትል እያደረጉባቸው እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
የተለያዩ የአገሪቱን ድንበሮች አቋርጠው በኮንትሮባንድ የሚወጡ የቁም እንስሳትን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር ባይቻልም ኮሚሽኑ ከሌላው ጊዜ በተሻለ ቁጥጥሩን እያጠናከረ መሄዱን እንደሚያመለክት ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 6/2012
ሶሎሞን በየነ