“ክሱ የድርጅቱን ስም ለማጠልሸት የሚደረግ ጥረት ነው”
-አየር መንገዱ
አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ አስተዳደር የሚያደርስባቸው የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰት መባባሱን ሠራተኞች ተናገሩ:: አየር መንገዱ በበኩሉ ተቋሙ በጥብቅ ሥነ-ምግባር በመመራቱ የተቋሙን ገጽታ ለማጠልሸት ጥረት የሚያደርጉ ሠራተኞች ወቀሳ ነው ሲል ክሱን አስተባብሏል::
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ መሠረታዊ የሠራተኛ ማህበር ሊቀመንበር ካፒቴን የሺዋስ ፈንታሁን ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ምንም እንኳ በተቋሙ አለቃ የመፍራት መንፈስ የቆየ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ግን ሁኔታው ተጠናክሮ አስተዳደሩ ቢሮ ድረስ ጠርቶ ያስፈራራል:: በተለያዩ ማህበራዊ ሚድያዎችም አስተዳደሩን ዘልፋችኋል በሚል ብቻ ከዋና አብራሪዎች ጀምሮ የሥራ ዕግድና ስንብቶች ይደረጋሉ::
በሌላ በኩል ተቋሙ የሥራ ልምድ የማይሰጥ፣ ባለሙያዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳድረው መቀጠር እንዳይችሉ የሙያ ማረጋገጫ ማስረጃቸውን የሚከለክልና አልፎም ፓስፖርት የመቀማት ልምድ አለው:: እንዲሁም የምዘና ሥርዓቱ (KPI) የሠራተኞችን የሥራ ተነሳሽነት የሚቀንስ፣ ተፈጥሯዊ የሆነውን ሕመምና የሴቶች ወሊድን እንደባከነ ጊዜ የሚቆጥር ነው::
ይህንን ትግል የሚያደርግ የሠራተኛ ማህበር የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት ከተቋቋመ በኋላም ሊሠራው አልቻለም:: ይልቁንም ለሌላኛው ማህበር ዕውቅና እንደሰጠ ይገልፃል:: ይህም ችግሮቹ እንዳይቃለሉ ምንጭ ስለሚሆን መንግሥት በትኩረት ሊያየው እንደሚገባ ሊቀመንበሩ ጠይቀዋል::
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም፤ ከሰሞኑ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለቀረበላቸው አስተያየትና ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፤ አየር መንገዱ ለስኬታማነቱ ትልቁ ሚስጥሩ ሥነምግባር እንደሆነ ገልፀዋል:: ነገር ግን በአገሪቱ ካለው የሥራ ባህል አንፃር ይህ የማይዋጥላቸውና ምቾት የሚነሳቸው ሠራተኞች አይጠፉም::
አራት መቶ መንገደኞችን ይዞ ከባህር ወለል 40 ሺህ ጫማ ከፍታ ላይ የሚበር አውሮፕላን የሚጠግን ቴክኒሺያን ትንሿ ስህተት ሕይወት ልታስከፍል ስለምትችል ከፍተኛ ጥንቃቄ ይጠበቅበታል:: በዚህ ደረጃ ሕጉን ለማስፈፀም ጠንከር ያሉ እርምጃዎች ሲወሰዱ ደግሞ ቅሬታዎች ይበዛሉ::
አቶ ተወልደ አየር መንገዱ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የሰው ሀብት አስተዳደር እንዳለው ገልፀው፤ በአገሪቱ የይቅርታ ፖሊሲ ያለው ብቸኛ ተቋም እንደሆነ ተናግረዋል:: በዚህም ሠራተኛው ከሥራ እስከመሰናበት የሚያደርስ ስህተት ሠርቶ ስድስት ወር ቆይቶ ‹‹አጥፍቻለሁ ይቅርታ ይደረግልኝ›› በሚልበት ወቅት ጉዳዩ ፍርድ ቤት ሳያመራ ድርጅቱ ይቅርታ አድርጎለት እንዲመለስ ይደረጋል::
‹‹የሠራተኛ ደመወዝ በድርድር ሳይሆን በፈቃደኝነት የሚጨምር፣ ከሥራ ወደ መሥሪያ ቤትና ከመሥሪያ ቦታ ወደ መኖሪያ ቤት ማመላለሻ የትራንስፖርት አገልግሎት ያለው፣ ሽሮ በስድስት ብር የሚበላበት ድርጅት፣ የመኖሪያ ቤት ገንብቶ ለሠራተኞቹ የሠጠና መሰል ጥቅማ ጥቅሞችን የሚሰጥ በመሆኑ ሠራተኛው በአጠቃላይ ደስተኛ ነው::›› በማለት አረጋግጠዋል::
አየር መንገዱ ላይ በተለያዩ ማህበራዊ ድረገጾች የሚጽፉ አካላት ተቋሙን ፖለቲካ ውስጥ ለመክተት ፍላጎት ቢኖራቸውም ድርጅቱ ግን በምንም መልኩ ፖለቲካ ውስጥ አይገባም:: ሠራተኞች በተቋሙ ለረጅም ዓመት የሚቆዩትም አየር መንገዱ ለአገሪቱ ወሳኝ በመሆኑና በቁጭት ለማሳደግ ካላቸው ተነሳሽነት እንደሆነ አቶ ተወልደ ተናግረዋል::
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የሰው ሀብት ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ መሳይ ሽፈራው፤ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ‹‹ይገፉናል ይጨቁኑናል ከማለታቸው በፊት አካሄዱን ያውቁታል ወይ? ማህበር ማለትስ ምን ማለት ነው? የሚለውንስ ያውቃሉ ወይ? በሚል መታየት አለበት::
የሠራተኞች የሥራ ስንብትም በተለያዩ ማህበራዊ ድረገጾች ስለሚያደርጉት እንቅስቃሴ አይደለም:: ይልቁንም ማንም ሰው ዕውነትነት በሌለው ጉዳይ ድርጅቱንም ሆነ አስተዳደሩን መወነጃጀል እንዲቆም ማሳሰቢያ አውጥተናል:: ማሳሰቢያውን ተከትሎ ተግባራዊ ካልተደረገ ግን የኢንዱስትሪ ሠላሙን የሚያናጋ በመሆኑ ይህንን ተላልፎ በተገኘ ሠራተኛ ላይ እርምጃ ይሰወዳል›› ብለዋል::
በዚህ ሒደት ያለው መመሪያና አካሄድ የማያሰራ ሆኖ ከተገኘ ደግሞ ውስጥ ሆኖ አሠራር የመቀየር የእያንዳንዱ ሠራተኛ ኃላፊነት ነው:: ከዚህ ውጪ ግን የድርጅቱን አሠራር በጣሰ መንገድ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ሕጋዊ አያደርጉም::
ምክትል ፕሬዚዳንቱ፤ የምዘና ሥርዓቱ፣ እንዲሁም የሕመም ፈቃድና ወሊድ ላይ የሚነሱት ቅሬታዎችም ተገቢነት የጎደላቸው እንደሆኑ ተናግረዋል:: አየር መንገዱን የሚያክል ግዙፍ ድርጅት ያለምዘና ሥርዓት መምራት አይቻልም:: ተቋሙ በውድድር ውስጥ እንዳለ ሁሉ በውስጡ የሚገኙ ሠራተኞችም መወዳደር መቻል አለባቸው:: ፍትሃዊ እንዲሆን ደግሞ የሠራተኞች ተሳትፎ ታክሎበት ነው የሚሠራው:: በምዘናው አፈፃፀም ዝቅ ያሉ ሠራተኞች ደግሞ ያሉበት ደረጃ ታውቆ ክፍተታቸውን የሚሞሉ ሥራዎች ይሠራሉ:: በዚህም ተቋሙ ግቡን ለመምታትና ውጤታማ ለመሆን ይረዳዋል ብለዋል::
የሕመምና የወሊድ ፈቃድም ሠራተኞቹ ደመወዝም ሆነ የሕክምና ጥቅም ሳይነካባቸው በሕጉ መሠረት ፈቃድ ይወስዳሉ:: በዓመቱ መጨረሻ የሚከፈለው ጉርሻ ግን በሕግ የሚመራ በመሆኑና የሚበረታታው ደግሞ የሠራና በየደረጃው ውጤታማ ሆኖ ድርጅቱን ለተሻለ ትርፋማነት ማብቃት የቻለ ሠራተኛ ነው::
በተቋሙ የሚነሱ ችግሮችን ለማቃለል ውይይቶች እየተደረጉ ሲሆን፤ ዘላቂ መፍትሔውም ዳር ሆኖ መመልከት ሳይሆን ክፍተት ካለ ለመሙላት ጥረት ማድረግ መሆኑን ገልፀዋል:: ለዚህም ሁሉም ሠራተኛ በባለቤትነት መንፈስ የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንደሚገባው ምክትል ፕሬዚዳንቱ ጥሪ አቅርበዋል::
አዲስ ዘመን ጥር 6/2012
ፍዮሪ ተወልደ