አዲስ አበባ፦ ባለፉት ዓመታት ገጭቶ ያመለጠን ተሽከርካሪ በቁጥጥር ስር በማዋል በኩል ሰፊ ችግሮች እንዳሉ የመድን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ አስታወቀ::
የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ታምራት ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ተጠየቅ አመድ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፤ ገጭቶ የማምለጥ ጉዳይ የተከማቸ ወንጀል ነው:: ኤጀንሲው ወንጀልን የመከላከል ስራ ባይሰራም አይመለከተኝም ሳይል የሚመለከታቸውን አካላት በማስተባበር ባከናወነው ተግባር አመርቂ ውጤት አስመዝግቧል ብለዋል::
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ባለፉት ስድስት ወር ውስጥ ብቻ ሶስት ገጭተው ያመለጡ አሽከርካሪዎች ተይዘው ፍርድ ቤት ቀርበው ቅጣታቸውን ተቀብለዋል:: ኤጀንሲውም የከፈለውን ገንዘብ ለማስመለስ ችሏል ብለው ይህ ቁጥር ትንሽ ሊመስል ቢችልም ከምንም ተነስቶ እዚህ መድረስ ትልቅ ስኬት ነው::
በሌላ በኩልም ይህ ውጤት ባለድርሻ አካላት በተለይ ፖሊስ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ያሳያል ያሉት ዳይሬክተሩ ፤ ወንጀለኛን አድኖ ከመያዝ ባሻገር የቁጥጥር ስራውም ትልቅ ለውጥ እየታየበት መሆኑን አስታውቀዋል::
ኤጀንሲው በተሽከርካሪ አደጋ የሚደርሰውን የሞት߹ የአካል ጉዳትና የንብረት ኪሳራ የሚያስከትለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለማቃለል ሁሉም ተሽከርካሪዎች የሶስተኛ ወገን መድን ሽፋን እንዲኖራቸው ፣ የተሽከርካሪ አደጋ ተጎጂዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ አስቸኳይ ህክምና እርዳታን በነጻ እንዲያገኙና ለሞትና ለአካል ጉዳት እንዲሁም ለንብረት ጉዳት ካሳ እንዲከፈላቸው በመስራት ላይ መሆኑን አቶ ሽመልስ ገልፀዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 6/2012
እፀገነት አክሊሉ