አዲስ አበባ፡- ‹‹ዕንባ ያፈሰሰው የመመሪያ አፈፃፀም›› በሚል ርዕስ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጥቅምት 12 እና 19 ቀን 2012 ዓ.ም የተስተናገደው የሠራተኞች ቅሬታ ላይ አስተዳደሩ ያሳረፈው ቅጣት እንዲነሳ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፐብሊክ ሠርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ አስተዳደር ፍርድ ቤት ወሰነ፡፡
ፍርድ ቤቱ በታኅሳስ 24 ቀን 2012 ዓ.ም በቁጥር አስ/ፍ/ቤት 6468/2018/2012 ወጪ ባደረገው መዝገብ ግልባጭ ላይ በሦስቱ ሠራተኞች እና በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጽሕፈት ቤት መካከል ሲካሄድ በነበረው የሥራ ክርክር ላይ ውሳኔ መስጠቱን አመላክቷል፡፡ በዚህም ፍርድ ቤቱ ለክርክሩ መነሻ ምክንያት የሆነውን በ08/11/2011 ዓ.ም የተላለፈውን ሠርኩላር ደብዳቤ መርምሯል፡፡
የደብዳቤው አጠቃላይ መንፈስ በዜሮ ዓመት በወሳኝ ኩነቶች ጽሕፈት ቤት የተቀጠሩ ሠራተኞችን ድልድል የሚመለከት ሲሆን፤ በተቋሙ የተቀጠሩና ሥልጠና ወስደው በአዲሱ የሠራተኞች ድልድል መሠረት ወደ ሌሎች ተቋማት የተደለደሉትን ሠራተኞች የሚመለከት እንጂ በትውስት ወደ ወሳኝ ኩነቶችና ምዝገባ ማስረጃ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የመጡትን የሚመለከት አለመሆኑን ለመረዳት መቻሉን አብራርቷል፡፡
በ08/11/2011 ዓ.ም የተላለፈውን ደብዳቤ መሠረት ተደርጎ ሠራተኞቹ መቀጣታቸው ተገቢ አለመሆኑን ያሰፈረው መዝገብ ግልባጭ፤ የነበረውን የግራ ቀኝ ክርክር ካደመጠና አስፈላጊ ማስረጃዎችን ከመረመረ በኋላም ውሳኔውን ሰጥቷል፡፡
በዚህም ሠራተኞቹ አለአግባብ የደመወዝና ከደረጃ ዝቅ የማለት ቅጣት መቀጣታቸው ተገቢ ባለመሆኑ ውሳኔው ሊሻር እንደሚገባ ያቀረቡትን ይግባኝ ፍርድ ቤቱ ተቀብሎ የወረዳ 12 ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጽሕፈት ቤትን በማስቀረብ ጉዳዩን ሲያጣራ ቆይቷል፡፡ ሰራተኞቹም የኃላፊውን ትዕዛዝ ተቀብሎ አገልግሎት እየሰጡ ቅሬታውን ለሚመለከተው አካል ማቅረብ ሲገባቸው ፈቃደኛ አለመሆናቸው ጥፋት በመሆኑ በዚህ ጉዳይ ላይ ጥፋተኛ ተብለው መቀጣታቸው ተገቢ ነው ብሎ ፍርድ ቤቱ መወሰኑን በመዝገብ ግልባጩ አስፍሯል፡፡
በፍርድ ቤቱ በተደረገው ክርክር መልስ ሰጪ ሆኖ የቀረበው የወረዳ 12 ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሠራተኞቹ የፈፀሙት ጥፋት ተመሳሳይ ቢሆንም የተለያየ ቅጣት መቅጣታቸው ሕግን ያልተከተለና ለተመሳሳይ ጥፋት ተመሳሳይ ቅጣት የሚለውን መርህ የጣሰ መሆኑን ፍርድ ቤቱ ወስኗል፡፡
በአዋጅ ቁጥር 56/2010 አንቀጽ 68 መሠረት የቅጣት ዓላማው ሠራተኞች በፈፀሙት ጥፋት ተፀጽተው መልካም ዜጋ እንዲሆኑ መርዳት መሆኑን በመግለጽ፤ መልስ ሰጪ በሠራተኞች ላይ ያስተላለፈው ቅጣት ግን ተደራራቢ ነው ሲልም ወስኗል፡፡
ፍርድ ቤቱ በውሳኔው፤ ቅጣቱ የአዋጁን አንቀጽ 69 /1/ የሚጻረር መሆኑን በመዝገብ ግልባጩ አስፍሯል፡፡ በመሆኑም የመልስ ሰጪ መሥሪያ ቤት ኃላፊ የሰጠው የደመወዝ ቅጣትና የደረጃ ዝቅታ ውሳኔ ከዚሁ ዓላማ ውጪ በመሆኑ ተገቢ አይደለም፡፡ በአጠቃላይ በኃላፊው የተላለፈው ቅጣት ከሠራተኞቹ ጥፋት ጋር የማይመጣጠን በመሆኑ የቅጣት ውሳኔውን በማሻሻል ሠራተኞቹ እያንዳንዳቸው በ16 ቀን ደመወዝ እንዲቀጡ በማለት በመንግሥት ሠራተኞች ደንብ ቁጥር 24/2002 አንቀጽ 55/3/ መሠረት ቅጣቱን አሻሽሎ ወስኗል፡፡
በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ የወረዳ 12 ዋና ሥራ አስፈፃሚ በውሰት ወሳኝ ኩነቶችና ምዝገባ ማስረጃ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት እንዲሰሩ የተላለፈላቸው ትዕዛዝ ከመመሪያ ውጪ በመሆኑ ባለመቀበላቸው እግድ እንደተጣለባቸው፣ ከደረጃቸው ዝቅ እንዲሉ መደረጋቸውን፣ ለሁለት ወር ከ11 ቀናት ደመወዝ እንዳልተከፈላቸውና ለተመሳሳይ ጥፋት የተላለፈባቸው ውሳኔም የተለያየ መሆኑን ያቀረቡት ቅሬታ ተስተናግዶ ነበር፡፡
ዋና ሥራ አስፈፃሚው በበኩላቸው ቅጣቱ ትክክለኛ እንደነበር ቢናገሩም፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፐብሊክ ሰርቪስና ሠው ሀብት ልማት ቢሮ ግን እግድ የሚጣለው ሠራተኛው ሠነድ ያሸሻል ተብሎ ከታመነና በመሠል ምክንያቶች መሆኑን በማስረዳት የሥራ ኃላፊዎች ላይ የሕግ ማዕቀፎችን አውቆ መተግበር ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ክፍተቶች መኖራቸውን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 6/2012
ፍዮሪ ተወልደ