አዲስ አበባ:- የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ አገር አቀፍ የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጫ ማዕቀፍ ባለመኖሩ ከውጭ አገር የተገኘ የትምህርት ማስረጃ ላይ የሚያከናውነው የአቻ ግመታ አሰጣጥ ስራው ላይ እንቅፋት እንደፈጠረበት አስታወቀ።
በኤጀንሲው የአቻ ግመታና የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጫ ዳይሬክተር አቶ ጎበዜ ይመር ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በውጭ አገር የተማሩ ግለሰቦች ይዘው የሚመጡት የትምህርት ማስረጃዎች ከአገር ውስጥ ከተገኘ የትምህርት ማስረጃ ጋር ለማዛመድ ወይም አቻ እንዲሆኑ ለማድረግ አገር አቀፍ የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጫ ማዕቀፍ አለመኖሩ በግመታ አሰጣጡ ላይ ጉራማይሌ አሰራር ፈጥሯል።
ደቡብ አፍሪካና መሰል አገሮች የአቻ ግመታ ስራ የሚያከናውኑበት መመሪያ አላቸው የሚሉት አቶ ጎበዜ፣ ኢትዮጵያ ከውጭ አገር ተሰጥተው ለሚመጡ የትምህርት ማስረጃዎች የአቻ ግመታ መስጫ መመሪያ የምትሰጥበት አገር አቀፍ የትምህርት ማስረጃ ማዕቀፍ የላትም ፤ ይህ መሆኑ ደግሞ የትምህርት ማስረጃዎችን ወደ ዩኒቨርሲቲዎች በመላክ ገምግመው ምላሻቸው ለኤጀንሲው እንዲሰጡና ግመታውም በዛ መልክ እንዲሰራ እየተደረገ ነው፡፡ በተመሳሳይ የህክምና ባለሙያዎች ለትምህርት አይነቱ የሚገባውን ደረጃ እንዲያወጡለት ይደረጋል ብለዋል ።
ወጥ የሆነ አገራዊ ማዕቀፍ አለመኖሩ ከውጭ አገር የትምህርት ማስረጃ ይዘው የሚመጡ ግለሰቦች በአቻ ምዘናው ዲግሪ ማግኘት ሲገባቸው ማስተርስ፣ ማስተርስ ማግኘት ሲገባቸው ደግሞ ዲግሪ እንዲሁም ዲፕሎማ ማግኘት ሲገባቸው ዲግሪ እና ዲግሪ ማግኘት ሲገባቸው ዲፕሎማ የሚያገኙበት አጋጣሚ መኖሩን ተናግረዋል።
ከዚህ ባሻገር በሌሎች አገሮች ያለው የአቻ ግመታ ስራ በእያንዳንዱ የትምህርት ዓይነት ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ግን የሚሰራው በአገር ውስጥ ካለው የትምህርት ደረጃ ጋር አቻ የሚሆኑት ላይ ብቻ ነውⵆ ይህ ደግሞ አቻ የማይሰጥባቸው የትምህርት ማስረጃዎች እንዲኖሩ ማድረጉን ጠቁመዋል።
ለአብነትም የአቻ ግመታ አገልግሎት ፈልገው የሚመጡ አንዳንድ ግለሰቦች “ፕሮፌሽናል ማስተርስ” የሚል የትምህርት መረጃ (በዲግሪና በማስተርስ ደረጃ መካከል) ይዘው ሲመጡ፤ በአገሪቱ የዚህ ደረጃ አቻ ስለሌለው በተማሩበት መስክ መስራት አይችሉም። ስለዚህ ይሄንን መረጃ ይዘው የሚመጡ ሰዎች ቀጣይ ትምህርት እንዲማሩ እንጂ በስራ አለም እንዲሰማሩ የአቻ ግመታ የትምህርት ማስረጃ ኤጀንሲው እንደማይሰጥ ተናግረዋል።
አቻ የሚሰራበት ዋናው ምክንያት አንድ ሰው በተማረበት የትምህርት መስክ ወደ ስራ አለም እንዲገባ ብሎም ትምህርት ለመቀጠል ሲፈልግ እንዲችል ነው ያሉት አቶ ጎበዜ፤ ነገርግን አገር አቀፍ የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጫ ማዕቀፍ ባለመኖሩ ተገቢውን የአቻ ግመታ የትምህርት ማስረጃ ባለማግኘት ወደ ስራ ዓለም መሰማራት ያልቻሉ መኖራቸውን ገልጸዋል።
ከውጭ ለተገኙ የትምህርት ማስረጃዎች የአቻ ግመታ መስጠት ከጀመረች ከ30 ዓመታት በላይ ያስቆጠረችው ኢትዮጵያ እስካሁን አገር አቀፍ የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጫ ማዕቀፍ ስለሌላት፤ ከውጭ ለሚመጡ የትምህርት ማስረጃዎች ቋሚ የአቻ ግመታ የትምህርት ማስረጃ ለመስጠት ክፍተት መፍጠሩን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 6/2012
ሶሎሞን በየነ