አዲስ አበባ፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በደቡብ አፍሪካ ቆይታቸው ለፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ኢትዮጵያውያን በደቡብ አፍሪካ ተከብረው እንዲኖሩ ሕጋዊ ፈቃድ እንዲሰጣቸው ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱን ይፋ አድርጉ።
ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት በደቡብ አፍሪካ ለቀናት ቆይታ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጆሐንስበርግ ከተማ ኢምፔሪያል ዎንደረርስ ክሪኬት ስታዲየም በመገኘት በስፍራው ለተገኙት ኢትዮጵያውያን ንግግር ባደረጉበት ወቅት ፤ወቅቱ የሀገራችሁ መሪ በእናንተ ጉዳይ ግድ ብሎት ከደቡብ አፍሪካ መንግሥት ጋር ተነጋግሮ ፍሬያማ እና ተስፋ ሰጪ ድርድር ያደረገበት የመጀመሪያው ወቅት መሆኑን ጠቅሰዋል።
‹‹ኢትዮጵያ ለማዲባ በጭንቁ ዘመን ፓስፖርት ሰጥታ የትግል አጋር እንደሆችው ሁሉ ዛሬ ደቡብ አፍሪካን ቤታችን ብለው የሚሠሩ፣ የሚተጉ ኢትዮጵያውያን ተከብረው እንዲኖሩ ሕጋዊ ፈቃድ እንዲሰጣቸው ያቀረብነው ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቷል››ሲሉ ይፋ ማድረጋቸውን የኢቢሲ ዘገባ አመልክቷል።
የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪየል ራማፎሳ በውጭ ጉዳያቸው የሚመራ ኮሚቴ አቋቁመው የኢትዮጵያን ዳያስፖራ ጉዳይ በተለየ መንገድ በማየት ሕጋዊ ርምጃ እንደሚወስዱ ቃል እንደገቡላቸውም አስታውቀዋል።“ኢትዮጵያውያን ኩሩ ሠርቶ አደር መሆናችሁ በመረጋገጡ ሀገራችሁ ኢትዮጵያ እና እኔም እጅግ የኮራሁባችሁ መሆኑንልገልጽላችሁ እፈልጋለሁ” ሲሉም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ፣ “2020 በኢትዮጵያም በደቡብ አፍሪካም አዳዲስ ዜና የምንሰማበት የብልጽግና እና የተስፋ ዘመን ስለሆነ እንኳን ደስ ያላችሁ!››ብለዋል። ‹‹ውድ የሀገሬ ልጆች ራስን አሸንፎ ለወገን ለመትረፍ መታተር ኢትዮጵያዊ ማንነት ሆኖባችሁ በየብስ እና በባሕር፣ በእግር እና በአየር ሀገራትን አቋርጣችሁ ከኢትዮጵያ እስከ ደቡብ አፍሪካ በተዘረጋ ጉዞ ውስጥ ያለፋችሁት ውጣ ውረድ እጅግ ከባድ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም፤ ለሕዝባችሁ እና ለሀገራችሁ የምታደርጉት ጥረት ሁሉ ከፍተኛ ዋጋ የምንሰጠው መሆኑን ስገልጽላችሁ በታላቅ ደስታ እና አክብሮት ነው” ሲሉም አስገንዝበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በንግግራቸው ወቅት የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ የነፃነት ታጋይ እና ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላን፣ “ታላቁ የነፃነት እና የሰላም አባት፣ የይቅርታ እና የፍቅር ሰው፣ የአፍሪካ ኩራት እና የኢትዮጵያችን ልዩ ወዳጅ” ሲሉ አስታውሰዋቸዋል። ኔልሰን ማንዴላ ዘረኝነትን በመቃወም፣ ለወገኖቻቸው ነፃነት እና እኩልነት ባደረጉት መራራ ትግል ሳቢያ በብዙ መንገላታታቸውንም ገልጸዋል።
ስቃያቸው እኩልነትን፣ እንግልታቸው ሰላምን፣ መታሰራቸው ነፃነትን፣ መገፋታቸው እርቅን ማስገኘታቸውን አብራርተው፤በእንቅፋት ከተሞላው መንገድ ባሻገር ያለውን ደልዳላ ሜዳ ማየት በመቻላቸው ለሀገራቸው እና ለወገናቸው አንፃራዊ ለውጥ ማስገኘታቸውንም ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድና ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ጋር በሁለቱ ሀገራት የጋራ ግንኙነት ላይ የሁለትዮሽ ውይይት አካሂደዋል።መሪዎቹ በውይይታቸው በሁለቱ ሀገራት መካከል ለረዥም ጊዜ የዘለቀውን ግንኙነት ወደ ስትራቴጂያዊ አጋርነት ከፍ ለማድረግ ተስማምተዋል::
በኢትዮጵያ በመጠናከር ላይ ባሉ ዘርፎች የደቡብ አፍሪካ ባለሀብቶችም ኢንቨስት ማድረግ በሚችሉበት ሁኔታ ላይም መምከራቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትን መረጃ ዋቢ በማድረግ ኢቢሲ ዘግቧል።
አዲስ ዘመን ጥር 5/2012