መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ፤ በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን የእቅድ ዘመን የዘርፉ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት አፈጻጸም 27 ነጥብ 7 በመቶ እንዲሁም በያዝነው የሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የመጀመሪያ ሶስት አመታት በአማካይ 20 ነጥብ 3 በመቶ እድገት አስመዝጓቧል።ለአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ከ9 ነጥብ 5 በመቶ በላይ ደርሷል።
ዘርፉ የተለያዩ ተግዳሮቶችም አሉበት። ግንባታዎች ይጓተታሉ፤ጥራት ይጎላል፤ ፕሮጀክቶች የሚጠናቀቁት ከተያዘላቸው በላይ በጀት እየጠየቁ ነው፤ ሙስና እና ኪራይ ሰብሳቢነት ትልቁ የዘርፉ ችግር መሆናቸው ይታወቃል።ለመሆኑ ይህ ከፍተኛ የሀገር ሀብት የሚያንቀሳቅስበት ዘርፍ ከሙስና አዙሪት መፈወስ ለምን ተሳነው?እንዴትስ ይውጣ?
የኢትዮጵያ ስራ ተቋራጮች ማህበር ፕሬዚዳንት ኢንጂነር አምሃ ስሜ የዘርፉ ተግዳሮት ከሆኑት መካከል የግዥው ስርአት ኢፍትሃዊነት አንዱ ነው ይላሉ።በዚህ ውስጥ ሙስና እና ብልሹ አሰራሮች እንዳሉ ይጠቅሳሉ። ይህም በፕሮፌሽናል እና በሚመለከተው አካል ከሙስና በጸዳ መልኩ ሊመራ ባለመቻሉ የተከሰተ መሆኑን ጠቅሰው፤ የግዥው ስራ እንደ ገቢ ምንጭ እየተቆጠረ መሆኑን ያመለክታሉ።
የመንግስት ባለስልጣናት እና በተለያዩ ኃላፊነቶች ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ይህን ገቢ ለማመቻቸት በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ የኢንዱስትሪው ዘርፍ ሙስና ገዝፎ መውጣቱን ያብራራሉ፡፡
ሙስና እና ኪራይ ሰብሳቢነቱ እንዲቆም ኢንዱስትሪው ስራውን በባለቤትነት መንፈስ መምራት ይኖርበታል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በኢንዱስትሪው ውስጥ የሚቋቋመው ካውንስል እነዚህን ተግዳሮቶች የሚፈቱ የአሰራር ስርአቶችን ከዘረጋ ችግሩን ማስቆም እንደሚቻልም ይገልጻሉ፡፡
‹‹ዘርፉ ለሙስና የተጋለጠበት ምክንያት ዋናው የባለቤት ችግር ነው፤ አንድ የዩኒቨርሲቲ ተቋም የመማር ማስተማሩን ተግባር ትቶ ፕሮጀክት ማስተዳደር የተሻለ ጥቅም የሚያስገኝ ከሆነ ስራውን ትቶ ወደ ማስተዳደሩ ያዘነብላል››ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ በዚህ የተነሳ ስራውን ለመስራት የሚገቡ ተቋራጮችም ሆኑ የተለያዩ ወገኖች ለእዚህ አይነቱ ችግር በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ተጋላጭ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይጠቁማሉ፡፡
እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፤ በኢንዱስትሪው ውስጥ የሚታዩ የጥራት ፣የበጀት የጊዜ ጥያቄዎችን ሊፈታ የሚችል እንዲሁም የማያሰሩ ፖሊሲዎችን ለመለወጥ ካውንስሉ ያስፈልጋል፡፡ መንግስት ይህን ኃላፊነት ለካውንስሉ መስጠት ይኖርበታል፡፡ከመንግስት የፕሮጀክት ተቆጣጣሪነት ውጪ መንግስት በፕሮጀክት ውስጥ እየሰራ ያለውን ስራ ወደ ግሉ ዘርፍ ማስተላለፍ ይኖርበታል ፡፡ ስራው ለባለቤቱ ከተላለፈ ሙስና ፣ ደላላ እና ሌብነት ሊቆሙ ይችላሉ፤ እነዚህ ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉት በአሰራር ነው፡፡
ኢኒጂነር አምሃ መሰረታዊውን ችግር ከመፍታት የሀገርን እድገት ከማፋጠን አኳያ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን በሚገባ ማገዝ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ ችግሮቹን የጋራ አድርጎ መፍታትና ወደሚቀጥለው መሄዱ ይጠቅማል ይላሉ፡፡
የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚሰሩት ዶክተር ኢንጂነር ውብሸት ዠቅ አለ በኮንስትራክሽን ዘርፉ ላይ በቂ ግንዛቤ እንደሌለ ይናገራሉ፤ በቅድሚያም በዚህ ላይ መስራት እንደሚገባ ያመለክታሉ፡፡
ዘርፉን ከሙስና ለመታደግ በጋራ መስራት እንደሚገባም አስገንዝበው፤ አንዱ አንዱን እየከሰሰ ሊመጣ የሚችል ለውጥ እንደሌለ ነው የሚገልጹት፡፡ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ መፍትሄ ማፈላለግ እንደሚገባም ያስገነዝባሉ፡፡
የከተማ ቤቶች ልማትና የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በቅርቡ ባካሄደው ሁለተኛው ሀገር አቀፍ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ንቅናቄ መድረክ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ላይ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን መንግስት በጥናት መለየቱን ጠቅሰው፤ እነዚህን ለመፍታት ከዘርፉ ተዋናዮች ጋር እንደሚሰራ ይገልጻሉ፡፡የኮንስትራክሽን ዘርፉን ያልያዘ መንግስት የሀገር ብልፅግናን ማረጋገጥ አይችልም ብለዋል፡፡
የግንባታው ዘርፍ ለሙስና እና ለስርቆት የተጋለጠ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከስርቆት ነጻ የሆነ የግንባታ ዘርፍ ሳይኖር ብልፅግና ጋር መድረስ አዳጋች መሆኑንም ያመለክታሉ። በዘርፉ የሚስተዋለው ብልሹ አሰራር እንዲቆምና መንግስት ለህዝብ አገልጋይ እንዲሆን ባለሀብቱ ማገዝ እንደሚኖርበትም አሳስበዋል፡፡በዘርፉ የተሰማሩ ኩባንያዎችም ከስርቆትና ከሙስና በፀዳ መልኩና በጥራት ለሀገር ዕድገት እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 5/2012
ኃይሉ ሣህለድንግል