ሐዋሳ፡- ‹‹የሲዳማ ክልል የሚመራበት ህገ መንግስት በረቂቅ ደረጃ ተጠናቋል›› ሲሉ የሲዳማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደስታ ሌዳሞ ገለፁ።ተቋማትን የመገንባት ስራ ከዚሁ ጎን ለጎን እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።
ዋና አስተዳዳሪው አቶ ደስታ ሌዳሞ ሰሞኑን ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት፤ በአሁኑ ወቅት አዲሱ የሲዳማ ክልል የሚመራበት የራሱ ህገ መንግስት በረቂቅ ደረጃ ተጠናቋል።ህገ መንግስቱን የማርቀቅ ስራ ቀደም ሲል የተጀመረ ሲሆን፣ ከተረቀቀም አንድ ዓመት ያህል ሆኖታል።
ረቂቅ ህገ መንግስቱ ላይ የሲዳማ ህዝብ አንድ ጊዜ እንዲወያይበት መደረጉን የተናገሩት አቶ ደስታ፤ በህዝቡ መተቸቱና ማስተቸቱ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።ይህም በአንድ ወር ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስረድተዋል።
እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ ረቂቅ ህገ መንግስቱ በህዝቡ ከተተቸ በኋላ በትችቱ ወቅት የተገኙ ግብዓቶችን አካቶ የመጨረሻው ረቂቅ ይወጣል።
እሱንም የምክር ቤት አባላት በአግባቡ አይተው የሚያጸድቁት ይሆናል። ከዚህ በኋላ ሲዳማ ውስጥ የሚሰራው ስራ ሁሉ ህግን መሰረት ያደረገ ይሆናል።
ከዚህ ጎን ለጎን ተቋማትን የመገንባት ስራ እንደሚካሄድ አቶ ደስታ አስታውቀዋል። ስራው ሁሉ በአንድ ጀምበር የሚያበቃ እንዳልሆነም ጠቁመው፤የሲዳማ ክልል የሌላውን ተሞክሮ እየወሰደ እና በየጊዜው ራሱን እያበቃ እንደሚሄድም አመልክተዋል። እንዲህም ሲባል ወደ ክልል የሚያድገው በዞን ደረጃ ያለው መዋቅር መስመሩን ጠብቆ እንደሆነም አቶ ደስታ ገልፀዋል።
‹‹በዚህ መልኩ ሲዳማ ክልልነቱን ካረጋገጠ በኋላ ወዲያው የሚካሄደው የክልል ምስረታ ጉባኤ ነው።›› ያሉት አቶ ደስታ፣ በዚህ ጉባኤ የሚወሰኑ መሰረታዊ ጉዳዮች ካሏቸው መካከል አንደኛው የመንግስት አስፈፃሚ አካላትን በአዋጅ ማቋቋም እንደሆነ አስረድተዋል።
የመንግስት ማስፈፀሚያ አዋጅ ቀርቦም እንደሚፀድቅ ተናግረዋል።የሲዳማ ህዝብም ደስታው ሙሉ የሚሆነው እነዚህ ነገሮች ሲከናወኑ እንደሆነም ገልፀዋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ ደማቅ ስነ ስርዓት እንደሚካሄድና ለዚህም ዝግጅት እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 5/2012
አስቴር ኤልያስ