አዲስ አበባ፦ መንግስት የሚያወጣቸው ሕጎች፣ደንቦችና መመሪያዎች ለግሉ ዘርፍ አመቺ መሆናቸውን ለመተፈሽና አሳታፊ ለማድረግ የጀመረው ጥረት እንደሚጠናክር ተገለፀ።
የኢትዮጵያ አሰሪዎች ኮንፌዴሬሽን ያዘጋጀው የምክክር ጉባኤ ትናንት በኢንተር-ኮንቲኔንታል ሆቴል ተካሂዷል። በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢንቨስትመንት ኮሚሽን የፕሮሞሽንና ፖሊሲ ጥናት ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ተመስገን ጥላሁን በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ ወቅቱ አገሪቱ የፖሊሲ ለውጥ እያደረገች የምትገኝበት ነው።
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በሀገሪቱ መንግስትን ማእከል ያደረገ የኢኮኖሚ ስርአት ሲተገበር ቆይቷል።በአሁኑ ወቅት የግሉን ዘርፍ ማእከል ያደረገ አቅጣጫ መከተል ተጀምሯል።ይህም በአገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ በግልፅ ተቀምጧል።
‹‹ኢንቨስትመንት የአሰሪዎች ሰራተኞችና የመንግስት ግንኙነት ውጤት ነው፤ ይህ ካልሆነም ኢንቨስትመንቱ የተሳካ አይሆንም›› ያሉት አቶ ተመስገን፤ኮሚሽኑ ይህን በመረዳት አገሪቱን ወደ ብልፅግና ለማሸጋገር ለግሉ ዘርፍ በተለይ የአሰሪዎችን ተሳትፎ ለማጎልበት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት በመሻሻል ላይ በሚገኘው የኢንቨስትመንት አዋጅም የግል ዘርፉ በተለይ የአሰሪዎች ተሳትፎና ሚና ከፍ እንዲል የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውንም ጠቅሰዋል።
‹‹ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩም በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ የግሉ ዘርፍ ኢንቨስተሮችና አሰሪዎች ተወክለው የመንግስትን ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ውሳኔዎች የሚከታተሉበትና ሃሳብ የሚሰጡበት እንዲሆን ተደርጓልም›› ብለዋል።የግሉን ዘርፍ በመሰል መልኩ አሳታፊ ለማድረግ የተጀመሩ ጥረቶች በቀጣይም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቅሰው፣ ይህም ለአገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር አስገንዘበዋል።
የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አየለች እሸቴ በበኩላቸው፤ ለሁለንተናዊ ልማት መንግስት አሰሪና ሰራተኛ በቅርበት መስራትና መነጋገራቸው በተለይ ለኢኮኖሚ ማሻሻያው ውጤታማነት የላቀ ፋይዳ እንዳለው አብራርተዋል።መንግስት የሚያወጣቸው ሕጎች፣ደንብና መመሪያዎች ለግሉ ዘርፍ አመቺ መሆናቸውን ለመተፈሽና አሳታፊ ለማድረግ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ጠቁመዋል።
የገቢዎች ሚኒስትር ተወካይ አቶ ብርሃኑ ማሞ በበኩላቸው፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መንግስት የሚያወጣቸው ሕጎች፣ደንብና መመሪያዎች ላይ በተለይ ከአሰሪዎች ጋር ከቀድሞው በተሻለ መልኩ በቅርበት ለመስራት ቁርጠኛ ስለመሆኑ አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ አሰሪዎች ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ጌታሁን ሁሴን በበኩላቸው፣ቀደም ሲል በአገሪቱ በሚወጡ ሕጎች፣አዋጅና መመሪያዎች ላይ የግሉ ዘርፍ በተለይ ያልተደራጁ አሰሪዎችን ማሳተፍ ላይ ውስንነት እንደነበረበት አስታውሰዋል።
ለውጦች ሲተገበሩ አሰሪዎችን ማሳተፉና ተጎጂ እንዳይሆኑ ከለላ የሚሰጥና የሚደግፍ መሆኑን ማረጋገጥ እንደሚገባ የጠቆሙት ኢንጂነሩ፤‹‹አሰሪን ማሳተፍ በተዘዋዋሪ ሰራተኞችንም ማሳተፍ ነው፤ሁለቱንም ማሳተፍ ደግሞ የአገር ጥቅምን ማስጠበቅ ነው›› ብለዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 5/2012
ታምራት ተስፋዬ