- ሀላባ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ “ሴራ” በዓል ተከብሯል
ሀላባ፡- እንደ ‹‹ሴራ›› አይነት ከትውልድ ወደትውልድ የተሸጋገሩ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊቶች ሕዝቦች በሰላም፣ በአንድነትና በፍቅር ተሳስበውና ተቻችለው እንዲኖሩ ያስቻሉ ሀብቶች መሆናቸውን የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ገለፁ። የሀላባ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ የ‹‹ሴራ›› በዓል ለዘጠነኛ ጊዜ በሀላባ ዞን ተከብሯል፡፡
ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው በበዓሉ ላይ እንደተናገሩት፤ የሀላባ ብሔረሰብ ካሉት ትውፊቶች ውስጥ አንዱ የሆነው ጥንታዊ የዳኝነት ስርዓት ‹‹ሆገቴ›› በአካባቢው ሰላምና ፍትህ መስፈን ላይ እየተጫወተ ያለው ሚና ሳይደነቅ የሚታለፍ አይደለም።
በቅርቡ በዞኑ ተከስቶ በነበረው ችግር የባህሉ መሪ አባቶችና የሃይማኖት አባቶች ከአጎራባች ክልልና ብሔረሰብ መሪዎች ጋር በመሆን እርቅ እንዲወርድ ማድረጋቸውም የዚህ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው ምስጋና አቅርበዋል።በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አካባቢዎች በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ወይም አፍራሽ ተልዕኮዎችን ተቀብለው እንደ አገር የተያዘውን የብልፅግና ጉዞ ለማስተጓጎል በእምነቶችና በብሔሮች መካከል ግጭቶችን ለመፍጠር ሙከራዎች እየተደረጉ እንደሚገኙ አቶ ርስቱ አብራርተዋል።
ይህ አይነቱ ሰው ሰራሽ ግጭት በሃይማኖትም ይሁን በብሔሮች ተቀባይነት የሌለው የተወገዘ ተግባር በመሆኑ የሃይማኖትና የባህል መሪዎች የሕዝቦችን ሰላም ለማስጠበቅ የጀመሩትን ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉ ‹‹አደራ›› ብለዋል።የሀላባ ሕዝብ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ የሚያነሳቸውን እንደ ዩኒቨርሲቲ ግንባታና ሌሎች ጥያቄዎችን ለመፍታትም ክልሉ ከፌዴራል መንግስት ጋር በጋራ በመሆን ትኩረት ሰጥቶ እንደሚመለከታቸው አቶ ርስቱ ቃል ገብተዋል።
የሀላባ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር መሐመድ ኑርዬ በበኩላቸው በበዓሉ አከባበር ስነስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ባህሎቻቸው፣ ቋንቋዎቻቸውና እምነቶቻቸው የማንነታቸው መገለጫ ቢሆኑም ኢትዮጵያዊነት አንድ የሚያደርጋቸው ማስተሳሰሪያ ገመድ መሆኑን ገልፀዋል።
ዶክተር መሐመድ የብሔር ብሔረሰቦችን ታሪክና እሴቶቻቸውን ለትውልድ በአግባቡ መዝግቦ ማስቀመጥና እውቅና መስጠት ለአገር ግንባታ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ቢሆንም የነበረው ስርዓት ለሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች እኩል እውቅና የሰጠ እንዳልነበረ በማስታወስ የታሪክ ምሁራንም ከአድሎ በፀዳ መልኩ የሕዝቦችን ታሪክ በመመዝገብ ረገድ ሙያዊ ግዴታቸውን በአግባቡ እንዳልተወጡ አስቀምጠዋል፡፡
በዚህ ዙሪያ በአግባቡ አለመሰራቱ በሕዝቦች መካከል የሃሰት ትርክቶች እንዲስፋፉ በር መክፈቱን የተናገሩት ዶክተር መሐመድ፤ በተለያዩ ማህበረሰቦች መካከል ግጭትና አለመረጋጋት እንዲፈጠር ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
‹የማህበረሰቡን ባህላዊ እሴቶች ጠብቆና አጎልብቶ ለትውልድ ማሻገር ለአገር ግንባታ እንዲሁም ብሔራዊ መግባባት ያለው ጥቅም ትልቅ በመሆኑ አባቶች ያላሳለሰ ጥረት እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።
የሀላባ ሕዝብ በሰላም ወዳድነቱ፣ በአቃፊነቱ እንዲሁም ሐዘንና ደስታን ማስተናገድ የሚችል መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር መሐመድ፤ የሀላባ ቁሊቶ ከተማ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ ትንሿ ኢትዮጵያ ስትሆን ነዋሪዎቿ ያለምንም ልዩነት ተዋደውና ተፋቅረው የሚኖሩባት የሰላምና የፍቅር ከተማ መሆኗን ገልፀዋል።ለዚህም በሀላባ ብሔረሰብ ዘንድ ‹‹ሆገቴ›› ተብሎ በስፋት የሚታወቀው ፍፁም ዲሞክራሲያዊ የሆነው ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት የድምፅ ብልጫና የሃሳብ የበላይነት የሚንጸባረቅበት መሆኑ አስተዋፅኦው ከፍተኛ እንደሆነ ይናገራሉ።
‹‹አገር የምትቀጥለው በአገር ሽማግሌዎችና በሃይማኖት አባቶች ተግሳፅ ነው›› ያሉት ዶክተር መሐመድ ከዚህ ቀደም በዞኑ የተከሰቱ ግጭቶችን በማርገብና በመፍታት ረገድ ከሀላባ ብሔረሰብ በተጨማሪ የሌሎች ብሔረሰቦች የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ሚና ትልቅ እንደነበር በማስታወስ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ምሁራንና ወጣቶች የመከፋፈል፣ የጥላቻና ቂም በቀል ፅሁፎችና ንግግሮችን እንዲሁም ለአገር እድገት የማይጠቅም የትውልድን አዕምሮ፣ ጉልበት፣ጊዜና ገንዘብ አባክኖ የንፁሃንን ደም ከሚያፋስስ ተግባር እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።የሀላባ ሕዝቦች የተፈጠረውን ለውጥ ለማስቀጠል በተባበረ ክንድ ለመስራት ቁርጠኛ እንደሆነም ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።
በበዓሉ አከባበር ላይ በእንግድነት ከተገኙት የአገር ሽማግሌሎች መካከል አዲስ ዘመን ያነጋገራቸው መሐመድ ጫፎ ኢማም አብዶ የ‹‹ሴራ›› በዓል ከሀላባ ብሔረሰብ አልፎ ለሌሎችም ትልቅ ጥቅም እንዳለው ይናገራሉ።በተለይም በብሔሮች መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶች ሲፈቱ ለነገ ቂም በቀል አዝለው እንዳይቆዩ በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና እንዳላቸው ያብራራሉ።
ለዚህም በቅርቡ በዞኑ ተከስቶ የነበረውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ የተሄደበት መንገድ አንድ ማሳያ መሆኑን ያስቀምጣሉ።መንግስትም በቀጣይ እንዲህ አይነት ባህላዊ ትውፊቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እገዛ ሊያደርግ ይገባል ይላሉ፡፡
‹‹በአገራችን ኢትዮጵያ ከዚህ በኋላ ግጭትና ደም መፋሰስ ይብቃ፣ አንዱ ለአንዱ ስጋት የሚሆንበት ዘመን አብቅቶ አገራችን የበለፀጉት አገራት ተርታ እንድትሰለፍ ሁላችንም የበኩላችንን አስተዋፅኦ ማበርከት አለብን›› ያሉት የአገር ሽማግሌው፤ ቀጣዩ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ በተለይም ወጣቶች ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው አብራርተዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 5/2012
ቦጋለ አበበ