አዲስ አበባ፡- በአማራ ክልል ምን ያህል የማአድን ሀብት እንዳለ በትክክል እንደማይታወቅ የክልሉ የመአድን ሀብት ማስፋፊያ ኤጀንሲ አስታወቀ።
የኤጀንሲው ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሰይድ አሊ በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋር በስልክ ባደረጉት ቃለምልልስ እንደገለጹት፤ በክልሉ ልዩ ልዩ የማአድን ሀብቶች አሉ ተብሎ የሚገመት ቢሆንም በማአድን ዙሪያ በትክክል የተካሄደ ጥናት ባለመኖሩ ምን ያህል የማአድን ሀብት እንዳለ አይታወቅም።
ከአፄ ሃይለስላሴ አንስቶ እስከ ኢህአዴግ መንግስት ድረስ ከወርቅ ማእድን ጋር በተያያዘ የተሰሩት አብዛኛዎቹ ጥናቶች በደቡብ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ሰሜን ኢትዮጵያና የስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች ላይ ብቻ የተካሄዱ መሆናቸውን ጠቅሰው፤በአማራ ክልል ግን ይህ ነው የሚባል ጥናት እንዳልተካሄደ አስታውቀዋል።በዚህ የተነሳም የክልሉን የማእድን ሀብት በትክክል ማወቅ እንደማይቻል ገልፀዋል።
እንደ ምክትል ዳይሬክተሩ ገለጻ፤የማእድን ጥናት ሰፊ ካፒታል ፣ ቴክኖሎጂ፣ እውቀት፣ ክህሎት፣ ጊዜና ትእግስት ይጠይቃል።እነዚህ ጉዳዮች አሁን ባለው ሁኔታም ሆነ በቀደመው ጊዜ በመንግስት የሚሰሩ ስራዎች ባለመሆናቸው በክልሉ ያለውን የማእድን ሀብት በትክክል በመለየት ጥቅም ላይ ለማዋል አልተቻለም።
‹‹የኢንዱስትሪው ዋነኛ ሞተርና ይህንኑ ስራ የሚያከናውነው የግል ባለሀብቱ›› ነው ያሉት ምክትል ዳይሬክተሩ፤ ባለሀብቱ የካፒታል ኪሳራ ቢያጋጥመው እንኳን ኪሳራውን መሸከም እንደሚችልና ስራዎችንም በጥራት ለማከናወን አቅሙ እንዳለው ተናግረዋል።የመንግስት አቅም ውስን መሆኑን ጠቅሰው፤መንግስት የግሉ ዘርፍ በክልሉ የማእድን ጥናቶችን እንዲያከናውን ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባም አስታውቀዋል።
‹‹መንግስት በማእድን ፍለጋና ክምችት ግመታ ላይ በሚፈልገው ልክ ለመስራት ይቅርና የተለየውንና መልማት የሚችለውን የማእድን ሀብት ለህዝብ ሊጠቅም በሚችል መልኩ በክልሉ ውስጥ ማልማት አልቻልም››ሲሉም ምክትል ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።
መንግስት የማእድን ፍለጋና ክምችት ስራን በመስራት ረገድ ሊመጡ የሚችሉ አደጋዎችንና ችግሮችን የመሸከም አቅም እንደሌለውም ተናግረዋል፡፡አቅሙ ቢኖረው እንኳ የቴክኖሎጂ፣ ካፒታል፣ እውቀትና ባለሙያ እጥረት እንዳለበትም ጠቅሰው፤በዚህ የተነሳም በክልሉ ያለውን የማእድን ሀብት አጥንቶ ጥቅም ላይ ማዋል እንዳልተቻለ ጠቅሰዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 5/2012
አስናቀ ፀጋዬ