- ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ ከወጪው ጋር ሲነፃፀር 0.06 በመቶ ነው
አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ በአመት ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ስራ አምስት ቢሊዮን ብር እንደምታወጣ አንድ ጥናት አመለከተ፡፡ አገሪቱ ለዘርፉ የምታወጣው ወጪ ከምታስገባው ጋር ሲነፃፀር 0.06 በመቶ ብቻ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ኢንስቲ ትዩት ያስጠናው ጥናት እንደሚያመላክተው ለፌዴራል የመንግስት መስሪያ ቤቶችና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ብቻ አገሪቱ በዓመት ለዘርፉ አምስት ቢሊዮን ብር ወጪ ታደርጋለች፡፡
ወጪዎቹ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የተመለከቱ ለስልጠ እና ለጥናት ምርምሮችና አገልግሎት ማካሄጃ እንደሚውል የጥናት ግኝቱ ያስረዳል::
በአፍሪካ ደረጃ ከደቡብ አፍሪካ ቀጥሎ የተጠና ሁለተኛው ጥናት መሆኑን የሚናገሩት የኢንስትቲዩቱ የመረጃ አደረጃጀትና እውቀት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ቃልኪዳን ተሾመ፤ሀገሪቱ ያላትን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ወጪ በመለየት በዘርፉ ያለውን አቅምና ፋይዳውን ለመለካት እንደሚያስችልም ያስረዳሉ፡፡
121 የመንግስት መስሪያ ቤቶችና 41 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ያካተተው ጥናት 86 በመቶዎቹ ወጪያቸውን በውስጥ በሚያደርጉት አገልግሎቶች፣ በስልጠናና ልዩ ልዩ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ተዛማጅ እንቅስቃሴዎች ሲያውሉ ቀሪዎቹ በሌሎች ተቋማት ላገኙት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ግልጋሎት እንደሚያወጡ ተመላክቷል፡፡
ጥናቱ አገሪቱ በሳይንስና ቴክኖሎጂው ዘርፍ ያላትን መረጃ ያጠናክራል ያሉት ዳይሬክተሩ በቴክኖሎጂ ዘርፍ ያለውን የመረጃ ክፍተትም የመሙላት ሚና እንዳለው ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም መንግስት በሳይንስና ቴክኖሎ ጂው ዘርፍ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ አመላክቷል ያሉት ዳይሬክተሩ ዘርፉን ለማጠናከርና የተሻለ እንቅስቃሴ ለማድረግ የሚያስችል መረጃ አስገኝቷልም ብለዋል:: በዚህም መንግስት ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ እያወጣ ያለው ወጪ ለዘርፉ መነቃቃት እንደፈጠረ ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩል የቴክኖሎጂ ክፍያ ምጣኔ ላይ የተደረገ ጥናት እንዳመለከተው ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ጋር ተያይዞ የምታገኘው ገቢ እጅግ አነስተኛ ሲሆን ከወጪው አንፃር ሲነፃፀር 0.06 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ይህም ሀገሪቱ ለቴክኖሎጂ የምታወጣውና ከሌሎች ሀገራት የምታስገባው የቴክኖሎጂ እውቀት ለሌሎች ከምትሸጠው አንፃር እጅግ በጣም ዝቅተኛ መሆኑን አመላክቷል፡፡
ሀገሪቱ ታዳጊ እንደመሆንዋ ልዩነቱ ሊፈጠር የሚችልና የሚገመትም መሆኑን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፣ በዘርፉ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ማድረግ የሚገባ መሆኑን ጥናቱ እንዳመላከተም ጠቁመዋል:: ጥናቱ እንደሚያመላክተው የቴክኖሎጂ እውቀቶችን ለኢትዮጵያ ከሚሸጡ ሀገራት አሜሪካ በቀዳሚነት ስትጠቀስ በቁስ ቴክኖሎጂዎች ደግሞ ቻይና በመሪነት ተቀምጣለች፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 4/2012
ተገኝ ብሩ