አዲስ አበባ፡- በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ እንዲሁም ኤሌክትሪክና ኤሌክትሮኒክስ ምርቶች ከወጪ ንግድ 24 ነጥብ 99 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ቢታቀድም 10 ነጥብ 07 ሚሊዮን ዶላር /ከ50 በመቶ በታች/ መገኘቱን በኢንስቲትዩቱ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ፊጤ በቀለ ገልጸዋል፡፡
ወደ ውጭ የተላኩት የኤሌክትሮኒክስና የኢንጅነሪንግ ምርቶች መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ ፊጤ ይህ ሲታይ የወጪ ንግዱ አፈፃፀም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ማሳያ እንደሆነ አመልክተዋል:: ለአፈፃፀሙ ዝቅተኝነት የማምረት አቅም ማነስና የግብዓት እጥረት እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የማምረት አቅም አጠቃቀም፣ የምርት ጥራት፣ ስብጥርና ምርታማነትን ለማሳደግ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን የሚተኩ የሀገር ውስጥ ምርቶችን የማምረት ስራ ተከናውኗል ያሉት አቶ ፊጤ በዚህም በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ እንዲሁም ኤሌክትሪክና ኤሌክትሮኒክስ ምርቶች ከሶስት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር በላይ የምርት አፈፃፀም ተገኝቷል ብለዋል፡፡
እንደ አቶ ፊጤ ገለፃ፤ የተገኘው የምርት መጠን በምርት ዓይነት በመሠረታዊ ብረታ ብረት 2.2 ቢሊዮን ብር፣ በኢንጅነሪንግ ምርቶች 6 መቶ ሺህ 547 ብር እና በኤሌክትሪካልና ኤሌክትሮኒክስ 4 መቶ ሺህ 14 ብር ነው፡፡ ባለፈው በጀት ዓመት በተመሣሣይ ወቅት የነበረው የምርት አፈፃፀም የሶስት ነጥብ 236 ቢሊዮን ብር የተመረተ ሲሆን አፈፃፀሙ አንድ ነጥብ 41 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 4/2012
መርድ ክፍሉ