በህብረ ቀለማት በተዋበ ቀለም ያጌጠች፤ በእምነት ልዩነት ያልተገደበ አብሮነት ማሳያ፤ በህብረ ብሄራዊ አንድነት ቆሞ በማይለያይ የታሪክ ሁነት የተጋመደ ህዝብ ምድር ናት ኢትዮጵያ፡፡
እዚህች አገር ላይ ለምዕተ ዓመታት በጥምረት ኖረው ያልተቃረኑ እምነቶች፤ በፍቅር አንድ ላይ የቆሙ አማኞች፤ እርስ በእርስ በመረዳዳት የታነፁ ቤተ እምነቶች ማግኘት የተለመደ መመልከትም የማያስደንቅ እውነት ነው፡፡ ገዝፈው ያሉ እውነቶች ተደብቀው፤ ጎልተው የታዩ ፍካቶች ለዝበው በአንፃሩ ደግሞ ጥቂት የጎደፉ ድርጊቶች ጎልተው መደመጣቸው እየተለመደ ነው፡፡
እውነታው አብሮነት፤ የሚታየው የተዋበ ህብራዊ ቀለማዊ ህብረት ሆኖ ሳለ በተቃራኒው ሰፍተው የሚነገሩ አሉታዊ ሁነቶች ለምን ሆኑ? ቤተ እምነቶች ሲታነፁ በጋራ አብሮ በማዋጣት ቆሞ የሚያሰራው ወገን ሲጎዳ ዘርና ዕምነት ሳይለይ በትብብር የሚረዳው ኢትዮጵያዊ ማንነት እርግጥም በአሉባልታ በደመቁ ጥቂት እኩይ ተግባሮች ተውጧል፡፡
አሁን ላይ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታዩ ችግሮች ማህበረሰባዊ መሰረት የሌላቸውና የግል ጥቅም አራማጅ በሆኑ ግለሰቦችና ቡድኖች ፍላጎት የተፈጠረ መሆኑን የማህበረሰብ ሳይንስ ባለሙያዎች ይገልፃሉ፡፡ አሉታዊ ጉዳዮችም ከጥሩ እሴቶች ይልቅ ጎልተው የሚደመጡበት ዋንኛው ምክንያትም የእነዚሁ አካላት ቅንጅታዊ ሴራ መሆኑን ያምናሉ፡፡
ዶክተር ወልደአብ ተሾመ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ሳይንስ መምህር ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ እምነት ሳይለያቸው በጋራ አብሮ መኖር የሚያስችል በፅኑ ፍቅር የተገነባ ማንነት የተላበሱ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ የእምነት ተቋማት ሲገነቡ አንዱ እምነት ሌላው በመዋጮና በልዩ ልዩ መልኩ መደገፉ፤ የምዕመናኑ በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች መተጋገዙ ለዚህ ማሳያ መሆኑንም ይጠቅሳሉ፡፡
ዶክተር ወልደአብ በቅርቡ በአማራ ክልል በተከሰተው ግጭት ለተቃጠሉ የዕምነት ተቋማት መልሶ ግንባታ የሚውል አምስት ሚሊዮን ብር አቶ ወርቁ አይተነው የተባሉ የክርስትና እምነት ተከታይግለሰብ ማዋጣታቸውን በመጥቀስ ሀሳባቸውን ያጠናክራሉ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የእስልምና እምነት ተከታይና የባህር ዳር ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ አወል አቡበከር ሰሞኑን የተከበረውን የገና (የልደት በዓል) ምክንያት በማድረግ ጧሪና ደጋፊ ላጡ አረጋውያን ሰንጋ ከብት ገዝተው በመለገስ ታላቅ ተግባር መፈፀማቸው በማህበረሰቡ ውስጥ የጠለቀ ህብረት መኖሩን አመላካች ነጥብ መሆኑንም ይገልፃሉ፡፡
በሀይማቶች መካከል ግጭት እንዲፈጠር የሚፈልጉ ሀይሎች በእምነቶች መካከል የሚደረጉ በጎ መስተጋብሮች እንዲለዝቡና አሉታዊ ተግባራት እንዲጎሉ አድርጓል በማለት ሀሳባቸውን ያብራራሉ:: “የኢትዮጵያዊያን ባህል አብሮነት ነው” የሚሉት ዶክተር ወልደአብ በእምነት ምክንያት የሚፈጠሩ ግጭቶች መነሻቸው ሌላ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡
አቶ ሀብታሙ ዱጉማ የስነ ልቦና ባለሙያ ናቸው:: ኢትዮጵያዊያን ሀይማኖትና ዘር ሳይለዩ በጋራ ዘመናትን የተሻገሩ የእርስ በርስ ትስስራቸው የጠነከረ መሆኑን የሚናገሩት ባለሙያው አሁን ላይ እየታዩ ያሉት አሉታዊ ጉዳዮች ተጋነው መቅረብና መልካም ጉዳዮች መለዘብ ታስቦበት የተሰራ አሉታዊ ተግባር መሆኑን ያምናሉ፡፡ አዎንታዊ ጉዳዮች ማህበረሰቡ ጋር በዝተው እንደሚገኙና አሁን የሚሰሙት አሉታዊ ጉዳዮች ማህበረሰቡን እንደማይወክሉም ያብራራሉ::
ማህበረሰቡ አሁን ድረስ የዘለቀ የጠነከረ ማህበራዊ ግንኙነት አለው ያሉት የስነ ልቦና ባለሙያው መልካም ግንኙነቱን የሚያጠነክሩ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራበት እንደሚገባም ይመክራሉ፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 4/2012
ተገኝ ብሩ