የሙያ ማህበራት ለስኬታቸው ስምረት በአንድነት በመሆን መትጋታቸው የተለመደ፤ አንድ አላማን ሰንቀው በጋራ መስራታቸው ነባራዊ እውነታ ነው፡፡ ከዚህ መሰረታዊ ሀቅ በመነሳትም በአዲስ አበባ የሚገኙ መምህራን ከዛሬ 70 ዓመት በፊት ስለ መምህራን ለውጥና እድገት የሚሰራ የመምህራን ማህበር አቋቋሙ፡፡
ይሁንና በሂደት መምህራንን በአንድነት አቅፎ ሲመራ፣ ስለ መምህሩ መብትና ለውጥ ሲሰራ የቆየው ማህበር ለሁለት መከፈሉ ተሰማ፡፡ ማህበሩ ለሁለት የተከፈለው መብታችን ማስከበር አልቻለም በራሳችን መንገድ ሌላ ማህበር መስርተን የመምህሩን ጥቅም እናስከብራለን ባሉ የከተማዋ መምህራን መሆኑ ተገልጿል፡፡
የመምህራን መብት ማስከበርና ጥቅም ማስጠበቅ ዓላማቸው መሆኑን የሚናገሩት የሁለቱም ማህበራት ተወካዮች ህጋዊ እውቅና ያላቸው መሆኑን ያስረዳሉ:: መጠሪያቸው የአዲስ አበባ መምህራን ማህበርና የአዲስ ተስፋ መምህራን ማህበር በሚል ለሁለት የተከፈሉት ማህበራቱ በየፊናቸው ለመምህሩ ወኪል በመሆን እየሰሩ መሆኑንም ይገልጻሉ፡፡
የአዲስ አበባ መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ደበበ ገ/ጻዲቅ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ የአዲስ አባበ መምህራን ማህበር ባለፉት 70 ዓመት ለመምህሩ ሲሰራ የኖረ 19ሺህ አካባቢ አባላት ያሉት ማህበር ነው፡፡ ይሁን እንጂ አዲስ ስለተቋቋመው ማህበር በማህበራዊ ሚዲያ ከመስማት ባሻገር፤ በማንና እንዴት እንደተቋቋመ? የሚያውቁት መረጃ አለመኖሩን ይገልጻሉ፡፡
እንደ አቶ ደበበ ገለጻ፤ እርሳቸው የሚመሩት ማህበር ከመንግሥት ጋር በጋራ በመሆን መምህራን በሚያነሷቸው ጥያቄዎች ላይ እየሰራ የሚገኝ ሲሆን ህጋዊ የሆነ መስመር ተከትሎ፣የመምህሩ ጥያቄ ስርዓትና ህግን በጠበቀ መልኩ፣ ከከተማው ከንቲባ ጀምሮ እስከ ፌዴራል የሚያደርስ ነው፡፡ በየደረጃው የሚመለሱ ጥያቄዎችን ደግሞ ለኢትዮጵያ መምህራን ማህበር እያቀረበ መልስ እንዲሰጥባቸው በማድረግ ላይ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
የመምህራንን ጥቅም ለማስከበር ጎራ መለየት ተገቢ አለመሆኑን የሚናገሩት ፕሬዚዳንቱ ማኅበራቸው ከመምህራን የደመወዝ መዘገየት ጋር ተያይዞ የሚነሳውን ከፍተኛ ቅሬታ ለመፍታት የተለያዩ ስራዎች ሰርቷል፡፡ በዚህም ከፐብሊክ ሰርቪስ ኮሚሽን ጋር ተከታታይ ስራዎች በመስራት ለማስተካከል ተችሏል በማለት ማብራሪያ ይሰጣሉ፡፡
በሌላ በኩል ነባሩ የመምህራን ማህበር ጥቅማችንን ማስጠበቅ ባለመቻሉ አዲስ ማህበር መመስረት አስፈላጊ ነው ብለን እንምናለን የሚሉት የአዲስ ተስፋ መምህራን ማህበር ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት መምህር በሀይሉ አስማረ ናቸው፡፡ ማህበሩ መንግሥት በሰጠው መብትና የማህበራት ማደራጃ ህግ በሚፈቅድ መልኩ የተመሰረተ መሆኑንም ይገልፃሉ፡፡
የማህበሩ መቋቋም ለመምህራን አማራጭ እንዲኖራቸው ያደርጋል የሚሉት መምህር በሀይሉ፤ ለትምህርት ጥራቱና ለሀገር እድገትም አስተዋፅኦ አለው፡፡ የአዲስ ተሰፋ መምህራን ማህበር እውቅና ያገኘና እስካሁን 4 ሺህ የሚሆኑ አባላት ያለው ማህበር መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ የማህበሩ ዋነኛ ዓላማም መምህሩን ከፖለቲካ ተፅጽኖ በማላቀቅ ነጻ የሆነ ትውልድ በመፍጠር፤ገለልተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ተቋም ለማቋቋም እንደሆነም ይናገራሉ፡፡
ከአዲስ አበባ መምህራን ማህበር ጋራ ያላቸውን ልዩነት ሰፊ መሆኑን የሚገልፁት መምህሩ የቀድሞው ማህበር ከመንግስት ተፅዕኖ ነፃ አለመሆኑና በዚህም መምህራን መብታቸው ለማስከበር የሚያቀርቡት ጥያቄ በተገቢው መልኩ ምላሽ እንዳያገኝ አድርጎታል፡፡
የቀድሞው መምህራን ማህበር አመራሮች የመንግስት ተከፋይ ናቸው የሚሉት ፕሬዚዳንቱ በአንፃሩ ደግሞ አዲሱ ማህበር በሌሎች ሀገራት እንዳሉ የሙያ ማህበራት ነፃ በሆነ መልኩ መምህሩን አደራጅቶ አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሚሰራ ነው፡፡
አክለውም አዲሱ ማህበር ገለልተኛ ሆኖ ለመምህሩ ጥቅም ወግኖ ከመንግስት ጋር እየተደራደረ የሚንቀሳቀስና የመምህሩን ጥቅም የሚያስከብር መሆኑ በማስረዳት የማህበሩ አመራሮች በአባላቱ መዋጮ ብቻ የሚተዳደሩ መሆኑን ያብራራሉ፡፡
ከነባሩ መምህራን ማህበር በጋራ ሊያሰራን የሚችል ጉዳይ ካለ አብረን እንሰራለን በማለት የሚገልፁት ጊዜያዊ ፕሬዚዳንቱ እስካሁን ግን ምንም አይነት ግንኙነት የለንም በማለት የሁለቱን ማህበራት ልዩነት ያጎላሉ፡፡
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አበበ ቸርነት በበኩላቸው ቢሮው እስካሁን ባለው ሂደት ከአዲስ አበባ መምህራን ማህበር ጋር እየሰራ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ አዲሱ ስለተቋቋመው ማህበር እስካሁን ምንም የደረሳቸው መረጃ አለመኖሩን ገልጸው ቢሮው በማህበራቱ መካከል ጣልቃ እንደማይገባም ይናገራሉ፡፡
መምህር በላይ ካሳ አዲስ አበባ በሚገኝ አንድ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት መምህር ናቸው፡፡የመምህራን ማህበር ለሁለት ጎራ መከፈል መምህራን ጥቅማቸውን ለማስከበር በሚያደርጉት ጥረት እንቅፋት የሚፈጥር መሆኑን ይናገራሉ፡፡
አንድን አላማ ለማሳካት በተለያየ ጎራ መሰለፍ ለምን አስፈለገ?” የሚሉት መምህሩ ተግባብቶ መስራትና በአንድነት መቆም ለመምህራን ማህበራቱ አስፈላጊ ነው ሲሉም ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 4/2012
ወርቅነሽ ደምሰው