– በ200 የእንሰት ዝርያዎች ላይ ምርምር እየተደረገ ነው
ወልቂጤ፡- እንሰት በዓለም አቀፍ ደረጃ የምግብ ዋስትና በማረጋገጥ ረገድ ከስንዴ ባልተናነሰ መልኩ እውቅና እንዲሰጠው ምርምርና ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ፡፡ በ2012 ዓ.ም የ‹‹እንሰት›› ተክልን ማዕከል ያደረገ የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ ስብሰባ ለማድረግ ዝግጅት ተጀምሯል፡፡
የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የጥናት ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሲሳይ ሸዋአማረ በተለይም ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት፤ እንሰት በበርካታ የኢትዮጵያ ክፍሎች ለምግብነት እየዋለ የሚገኝ እና ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው ተክል ነው፡፡ በውስጡ በሚይዛቸው ንጥረ ነገሮችና ይዘቱ ብሎም ለሰው ልጅ ካለው ፋይዳ አኳያ ወደር የለሽ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በተጨማሪ ለመድሃኒት ቅመማ እንሰት ትልቅ ፋይዳ ያለውና ከተረፈ ምርቶቹም ውስጥ አንድም ሳይቀር ለበርካታ አገልግሎት የሚውል ነው፡፡ ይሁንና በዘርፉ ላይ የተደረጉ ምርምሮች አነስተኛ መሆንና ትኩረት አለመስጠት እንሰት ከሌሎች እጽዋትና ተክሎች አንጻር ስሙ በዓለም ላይ እንዳይናኝ አድርጓል፡፡
ዶክተሩ ሲሳይ እንዳሉት፤ በዓለም ላይ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ረገድ ስንዴ ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ሲሆን ዓለም አቀፍ ተቋማት በስንዴ ላይ ለሚደረጉ ጥናቶችና ምርምሮች ትልቅ ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡
ሆኖም እንሰት ከስንዴ ባልተናነሰ መልኩ ድጋፍ ሊደረግለት የሚገባ እና የዓለም የትኩረት ማዕከል ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት እንሰት በደቡብ ብሄር፤ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልልና በኦሮሚያ ክልል በስፋት ለምግብነት የሚውል ሲሆን፤ በአማራ እና ሌሎች ክልሎችም በፍጥነት እየተስፋፋና ፋይዳው እየታወቀ መጥቷል፡፡
እንደምክትል ፕሬዚዳንቱ ገለፃ፤ እንሰት አስቸጋሪ የሆኑ የአየር ንብረትና ፀባይን በመቋቋም ረገድም የተመሰገነ ተክል ነው ብለውታል፡፡ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ወቅት 200 የሚሆኑ የእንሰት ዝርያዎች በመለየት ምርምር እያካሄደ ሲሆን ዓለም አቀፍ ዝና እንዲላበስ እየተሰራ ነው፡፡ በተጨማሪም በቀጣይ በዓለም ላይ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በቀዳሚነት ከሚፈለጉ የተክል ዝርያዎች ውስጥ ቀዳሚው እንደሚሆን ገልፀዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው የጀመረውን ጥረት ለማስገንዘብና የጥናት ውጤቶችንም ለማሳወቅ ይረዳ ዘንድ ብሎም በእንሰት ተክል ላይ ለሚደረግ ምርምር ትኩረት እንዲሰጠው በ2012 ዓ.ም የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የእንሰት ጉባዔ ለማካሄድ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ዩኒቨርሲቲው ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያላቸውን የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በስፋት እያከናወነ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡ የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በ2004 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ መርሐግብሮች 15ሺ ተማሪዎችን እያሰለጠነ ይገኛል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 4/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር