አዲስ አበባ፤ በተያዘው በጀት አመት መተግበር የጀመረው የትምህርትና ስልጠና ማሻሻያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን አለማቀፋዊ እይታ እንዲኖራቸው የሚያስችል መሆኑን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
በሚኒስቴሩ የምርምርና አካዳሚክ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል ዶክተር ኤባ ሚጀና በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት ማሻሻያው ተማሪዎችን አለማቀፋዊ እይታ እንዲኖራቸው በማድረግ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪው አለም የሚኖራቸውን ግንኙነት በማስተካከል ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያስችል ነው። እስካሁን ካለው አካሄድ በተለይም ትምህርቱ ተግባር ተኮር እንዲሆን በማድረግም ተማሪዎችን ከጊዜ ጋር እንዲራመዱ ይረዳቸዋል።
እስካሁን በነበረው አካሄድ ከታችኛው ክፍል ጀምሮ የሞራልና ሌሎች ጉዳዮችን እየተማሩ ይመጣሉ ተብሎ የሚታሰብ ቢሆንም የሚፈለገውን ያህል ውጤት አለመምጣቱ በተደረገው የፍኖተ ካርታ ጥናት ተረጋግጧል።
በተጨማሪም ተማሪዎች ግዜው የሚጠይቃቸውን ወሳኝ የሆኑ ጉዳዮች ሳይማሩ ወደ ዩኒቨርሲቲ እየመጡ በመሆናቸውና ከግዜው ጋር እንዲራመዱ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።በመሆኑም በማሻሻያው ለቀሪውም አለም አዲስ የሆነውን «ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂን» ጨምሮ ወሳኝ ኮርሶችን እንዲወስዱ ተደርጓል ሲሉ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
ማሻሻያው የስነ ዜጋና ስነ ምግባር ትምህርትንም አሁን ካለው በተለየ ሁኔታ የሞራልና የዜግነት እንዲሁም ሌሎች ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸውን ተጨማሪ እውቀቶችን እንዲያገኙ የሚረዳ ሲሆን፤ «ግሎባል ትሬይንድ» የሚባል እስካሁን ያልነበረ አለም የደረሰችበትን ደረጃና ወዴት እየሄደች እንደሆነ በማወቅ ከአለም ጋር አብረው እንዲጓዙ የሚያስችል ትምህርትን እንደሚያካትት ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
በተጨማሪ በቴክኖሎጂ እንደ ሀገር በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የምንገኝ በመሆኑ ይህንን ክፍተት የማጥበብ፤ ተማሪዎች በትምህርት ቤታቸው ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ህይወታቸው ምክንያታዊ አስተሳሰብን እንዲያዳብሩ የማስቻል፤ በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአለም አቀፍ ደረጃ ያላቸውን የተግባቦት ክህሎት የማሳደግ፤ ስራ ፈጠራ ላይ ያላቸውን እይታና ክህሎት የማስፋት እንዲሁም ክፍተት የሚታይበትን የተማሪዎች ስነ ምግባር የማስተካከል እንዲሁም ስለ ሀገር አንድነትና ስለዜጎች እንዲያውቁና እንዲቆረቆሩ ለማስቻል ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ተገናግረዋል።
ዳይሬክተሩ ጨምረው እንዳብራሩት «እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ» ያሉ ቀድሞ ይሰጡ የነበሩ አንዳንድ ኮርሶችም በዝቅተኛው የትምህርት ክፍል ይማሩታል ተብሎ የተገመተ ቢሆንም በቂ እውቀት ይዘው ባለመምጣታቸው እንደአዲስ ተስተካክለው የሚማሩበት ሁኔታ ወደ ፊት ይመቻቻል።
እየቀነሰ የመጣውን የትምህርት ጥራትም ለማስጠበቅ ከስርአተ ትምህርት ማሻሻያው ባለፈ በየአመቱ የሚወስዱትን ኮርሶች አለም አቀፍ ደረጃ እንዲኖራቸው ተደርጎ ይከለሳል። እንዲሁም መምህራን አለምአቀፍ እይታ እንዲኖራቸው ለማድረግና ተመራማሪ እንዲሆኑ ስልጠና ይሰጣቸዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 4/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ