በባህላችን ‹‹ቤት ለእንቦሳ›› ሲባል ‹‹እንቦሳ እሰሩ›› የሚል መልስ የማይሰጥ የለም። ምክንያቱም ውጣውረዱን አልፎ፣ ፈተናውን ተጋፍጦ አዲስ ቤት ሰርቷልና እንኳን ደስ አለህ ለማለት ታስቦ ስለሚባለው ነው። እናም ለዚህ ያበቃውን አምላክ ሲያመሰግን ለእናንተም ይሁንላችሁ መልስ ሲሰጥ ደግሞ ‹‹እንቦሳ እሰሩ›› ይላል። በእርግጥ ይህ አባባል ለሌላም የሚሰራበት ሁኔታ አለ።
አይተውት ወይም ገብተውበት የማያውቁት ቤት በእንግድነት ሲሄዱም ‹‹ቤት ለእንቦሳ›› ማለትዎ ግድ ነው። ምክንያቱም ቤቱ የሰላም፣ የፍቅርና የደስታ ቤት ይሁን የሚለውን ትርጓሜ ይይዛልና ነው። እንግዳ ተቀባዩም ለዚህም ቢሆን አሜን ሳይሆን መልሱ የአንተም ቤት በደስታ ይሞላ ለማለት ‹‹እንቦሳ እስሩ›› ይሆናል የሚለው። ይህ የመልካም ምኞት መግለጫ አባባል ሰሞኑን ደግሞ ለታላቅ ክብርና መጠሪያ መታጨቱን ከወደ ጎንደር የመጣው መረጃ ያስረዳል።
የመሰባሰቢያ፣የመረዳጃና፣ የፍቅር መግለጫ ሊሆን በአንድ ከተማ ላይ ከትሞና በኅብረተሰቡ ልቦና ላይ ታትሞ ሕዝብን ከሕዝብ ሊያጋባና ሊያስተሳስር ቀናትን እየተጠባበቀ ይገኛል። ከተማዋ ከላይ እንደተባለው ጎንደር ስትሆን፤ ቀደም ሲል በዩኒቨርሲቲ አካባቢ ቤተሰብን ብቻ ሳይሆን አገርን የሚያስደምም ሥራ ሰርተው አስደንቀውን ነበር። በምን ከተባለ አምጠው ያልወለዱትን ልጅ ልጄ በማለት ተረክበው ከልጃቸው እኩል እየተንከባከቡ የወላድን አንጀት በማሳረፍ ነው። ዩኒቨርሲቲዎቻችን ባልነበርንበት ባህል እርስ በእርስ እየተተራመሱና ወንድማቸው ላይ አደጋ እየጋረጡ ባሉበት ወቅት ጎንደሮች ግን ይህ ችግር ከእኛ ዘንድ መድረስ የለበትም በማለት የጎንደር ቤተሰብን መስርተዋል።
ልጆቼ እያለ የተሳሳተውን እያረመ ችግሩንም አርግቧል። በዚህም ‹‹ኢትዮጵያዊነት መገለጫውና ለዛው ይህ ነው›› የሚል ኩራትም ጥሎ አልፏል። ዛሬም ያንን የለመደውን የበጎነት ተግባር ለመከወን ‹‹ቤት ለእንቦሳ ፕሮጀክትን ቀርጾ›› በዩኔስኮ ዘንድሮ የተመዘገበውን የጥምቀት በዓል ለማክበር ሽርጉድ እያለ ነው። ሀሳቡ የቀረበው ምንም እንኳን ከከተማዋ ከንቲባ ቢሆንም የሕዝቡም ምኞት ነበረና በአንድ ጊዜ ነበር ተቀባይነት አግኝቶ ወደትግበራው የገባው።
‹‹ቤት ለእንቦሳ›› እልፍኝ ለምን?
ይህን ተከትሎ የዝግጅት ክፍላችንም በዛሬው የባህል አምድ ላይ ‹‹ቤት ለእንቦሳ›› ለመሆኑ ምን ያህል እውነታን በተግባር ያሳያል? ምን ጠቀሜታ አለው? አላማውስ ምንድን ነው? ዛሬ ላይ ለምን ሀሳቡ ተነሳ የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳት በጉዳዩ ዙሪያ እየሰሩ ያሉ አካላትን አነጋግረን ምላሽ አግኝተናል። በዚህ መሰረት በመጀመሪያ ሀሳባቸውን ያጋሩን የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ማስተዋል ስዩም ናቸው።
‹‹ድርሻዬ ሀሳብ ማቅረብ ብቻ ነበር። ሕዝቡ ደግሞ አገር ወዳድነቱና እንግዳ ተቀባይነቱን ለማሳየት ሀሳቡን ይፈልገዋል›› የሚሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው፤ ስያሜውን በአገርኛ ባህላዊ ንግግር በማድረግ ወደ ትግበራው መገባቱን ይገልፃሉ። እቅዱ በተለይ የጥምቀት በዓል በዩኔስኮ ከመመዝገቡ ጋር ተያይዞ የሚመጣውን ሕዝብ በሆቴሎች ብቻ ማስተናገድ ስለማይችል በፍቅራዊ የእንግዳ አቀባበል ለማስተናገድ የሚያስችል እንደሆነም ያነሳሉ። ከአሁን በፊት ከ700ሺህ በላይ ጎብኚዎች ጥምቀትን ለማክበር ይመጡ እንደነበር ይናገራሉ። ዘንድሮው ደግሞ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ጎብኚ ይጠበቃል። ይህን ሁሉ እንግዳ በሆቴሎች ብቻ ማሳረፍ ስለማይቻል ‹‹ቤት ለእንቦሳ›› በሚል መርሀ ግብር አዲስ አቀባበል ለማድረግ ተወስኗል።
እንደ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ከሆነ ከውጭ አገር ብቻ የሚመጡ ጎብኚዎች 10ሺህ ይደርሳሉ። አሁን ብዙዎቹ ገብተው ሆቴል በመያዝ ከተማዋን በመጎብኘት ላይ እንደሆኑ ተናግረዋል። በከተማዋ ከሦስት ኮከብ በላይ ያሉ ሆቴሎች 10 ሲሆኑ ሁሉም ተይዘዋል። ትንንሽ የሚባሉትም ቢሆን በማለቅ ላይ ይገኛሉ። ስለሆነም ሕዝቡ እንዳይንገላታ በቤት ለእንቦሳ ፕሮጀክት ማንኛውም ቤት አንኳኩቶ መስተናገድ እንዲችል ተደርጓል።
ቤት ለእንቦሳ የባህል ትስስርን ለማጠናከር፤ ለሌላ ጊዜ ቤተሰብ የሚሆን ዘመድ ለማግኘት፤ ኢትዮጵያዊነት መንፈስን ለማምጣት፣ መጪው ማህበረሰብ ጎንደርን እንደቤቱ እንዲቆጥር ለማድረግ ያስችላል። አሁን እየጠፋ የመጣውን የኢትዮጵያዊነት መንፈስ በእጅጉ የሚመልስና ያለውንም እየገነባ የሚሄድበትን መንገድ የሚጠርግ ነው።
አቶ ማስተዋል የጎንደር ሕዝብ በነካ እጁና በለመደው ባህሉ እንግዳውን እንዲያስተናግድ ለማድረግም ‹‹ቤት ለእንቦሳ›› ፍቱን መድኃኒት ነው ይላሉ። እንግዶች በአውሮፕላንም ሆነ በመኪና ሲመጡ በየፍላጎታቸው የሚያርፉበትን ቦታ እንዲያገኙ የሚያደርግ ኮሚቴ መቋቋሙን፤ ማረፊያቸው ሆቴል ከሆነ ወደዚያ ካልሆነ ደግሞ በቤት እንቦሳ የተዘጋጀው ቦታ እንደሚወሰዱ ገልጸዋል።
‹‹ይህ በዓል ሃይማኖታዊ ነው። ነገር ግን ከዚህ ልቆ እንዲከበር ለማድረግ እየተሰራ ነው›› በማለት ጉዳዩን ሰፋ ባለ መልኩ የሚያብራሩት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው፤ የጎንደር ሙስሊምም ሆነ ክርስቲያኑ በአንድነት ተባብሮ የሚተገብረው እንደሆነ ያነሳሉ። በዚህም ቤት ለእንበሳ ፕሮጀክት የሃይማኖት ልዩነት የለበትም ይላሉ። ክርስቲያኑም ሆነ ሙስሊሙ ለዚህ ሀሳብ ተፈጻሚነት እኩል እንደሚሰራበትም ተናግረዋል። ለኢትዮጵያ አንድ መሆን ይህ ተግባር ያስፈልጋል ብሎ በማመኑ በተለይ ሙስሊሙ የጎንደር ነዋሪ ‹‹ቤት ለእንቦሳ›› እያሉ የሚመጡትን ክርስቲያን ወንድሞቹን በፍቅር ለማስተናገድ ዝግጅቱን እንደጨረሰ ነግረውናል። ‹‹የበዓሉ እንግዶች የእኛም ናቸው›› የሚል መንፈስ እንዳላቸውና በቤታቸው ክርስቲያኑን ለማስተናገድ ከአሁኑ ቁርጠኛ ሆነው እየጠበቁ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።
‹‹የቤት ለእንቦሳ ሥራን አስፈጻሚውም ተግባሪውም ራሱ የጎንደር ሕዝብ ነው›› በማለትም ስለዚህም የክርስቲያን ወጣቶች ማህበር እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ወጣቶች ማህበር በሁለት መንገድ እንግዶችን ለመቀበል መዘጋጀቱን አስታውቀዋል። በአንድ መልኩ ሕዝቡን ድንኳን በመጣል አዳራሾችን በመጠቀም በቤተክርስቲያን ለማሳረፍና አልያም እንግዶች ይህንን ካልፈለጉ ደግሞ በየነዋሪው ቤት በመውሰድ እንዲያድሩ ያደርጋሉ። ለዚህም ደግሞ ሕዝቡ ራሱን ዝግጁ እንዳደረገም ያስረዳሉ።
ጥምቀት በዩኔስኮ ሲመዘገብ የእንግዳ አቀባበልን ያካተተ አልነበረም የሚሉት አቶ ማስተዋል፤ ይህ ሲጨመርበት ጠንካራ ግብዓት ሆኖ እንዲቀጥልና ለአገር ጥሩ ማንነት እንዲያላብስ ብሎም የገቢ ምንጭን እንዲያጠናክር ዕድል ይፈጥራል የሚል ሀሳብ ይሰነዝራሉ። ስለሆነም ይህ በዓል የጎንደር ሕዝብ ብቻ አይደለምና እንግዶችም ቤት ለእንቦሳ ብለው እንደገቡ ሁሉ መልካምነታቸውን አስተዋጽኦ አድርገው በሰላም እንዲመለሱ ያስፈልጋል የሚል መልዕክትም ያስተላልፋሉ።
የብዙ ችግሮች መከሰት ምንጭ ባህላችንን መተዋችን ነው የሚሉት አቶ ማስተዋል፤ ከእነዚህ ባህሎቻችን አንዱ ደግሞ እንግዳ ተቀባይነት እንደሆነ ይገልፃሉ። ነገር ግን እንግዳን ከመቀበልና ከማስተናገድ ይልቅ መጠራጠር እየሰፋ መጥቷል። በቤት ለእንቦሳ ማንነታችን ተመልሶ ከየትኛውም አካባቢ የመጣውን ሰው በኢትዮጵያዊነት ስሜት ብቻ እንድናስተናግድ ጎንደር ቀዳሚው አይን ገላጭ ይሆናል ብለዋል። ‹‹ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው›› በሚለው በትልቁ ጸጋው ማስተናገድን ለማስለመድ ተግባራዊ ይደረጋል ይላሉ። ይህ ሲሆን ደግሞ አገሪቱ ወደ ብልጽግና ጎዳና ትራመዳለች። ሰላምንና አንድነትን ማረጋገጥ ይቻላል። ስለሆነም የእንግዳ አቀባበል ልምድ የጎንደር ሕዝብ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የኢትዮጵያዊ ክፍል ውስጥ ያለ በመሆኑ የቀደመውን አንርሳ ለማለትም ጎንደሮች ተነስተዋል ብለውናል።
የብዙ አገራት ልምድንና ባህልን እንደተመለከቱ ነገር ግን እንደኢትዮጵያ በባህሉ ልዩ የሆነ አገር እንዳላዩ የሚናገሩት ምክትል ከንቲባው፤ ባህሏ በራሱ ቆሞ የሚናገርበትን አማራጭ አልተሰጠውም። ገንዘብ ሆኖም ሲያሳድጋትም እምብዛም አልታየም ይላሉ። ስለዚህም ቤት ለእንቦሳ ይህንን ሁኔታ በአንድ ደረጃ ከፍ ያደርገዋል ብለው እንደሚያምኑ ይገልጻሉ።
ሰላምና ፀጥታን በተመለከተ
በቤት ለእንቦሳ ፕሮጀክት ከአቀባበል በተጨማሪ በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ማድረግም ላይ ይሰራል። ስለሆነም አደጋና ዝርፊያ እንዳይገጥም ማህበራቱ ከሚሰሩት ባሻገር በየዘርፉ ያሉ የጸጥታ አካላት ብቁ ዝግጅት ማድረጋቸውን አቶ ማስተዋል አንስተዋል። ስለዚህም እንግዶች ምንም ስጋት ሳይፈጠርባቸው መምጣት እንደሚችሉ የነገሩን ምክትል ከንቲባው፤ በመልካም ሥራ ውስጥ መጥፎ ተግባር ላይ የሚሰማራ አይጠፋምና ሕዝቡ ይህንን ባህሪ የሚያሳየውን እያጋለጠ ክብረ በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ሊያግዝ ይገባል ብለዋል።
‹‹ሁሉም ባህላችን በዩኔስኮ ሊመዘገብ የሚችል ነው›› የሚል እምነት ያላቸው ደግሞ ጥምቀትን በተመለከተ የተመሰረተው የቤት ለእንቦሳ ፕሮጀክትን ተግባራዊ እንዲሆን የሚያደርገው የክርስቲያኖች ማህበር ሰብሳቢ ዲያቆን ሰለሞን አለሙ ናቸው። አሁን የተመዘገበው የጥምቀት ባህላዊ አከባበር አንዱ ማሳያ እንደሆነም ያነሳሉ። እርሳቸው እንደሚሉት፤ በቤት ለእንቦሳ ቀለም፣ ብሔር፣ ሃይማኖት ሳይሆን መለያው ሰው መሆን ብቻ ነው። ስለሆነም ሁሉም በእኩል ይስተናገድበታል። በሃይማኖቱ ለእግዚአብሔር ፍጥረት ሁሉ ክብር መስጠት ግዴታ ነውና በዚህም ሃይማኖታዊ በዓል የሚደረገው ይኸው ነው። ይህ ምልከታ ደግሞ አገሪቱ ላይ እየተፈጠረ ያለውን ክፉ መንፈስ ያርቀዋል የሚል እምነት አላቸው። መተሳሰብ እንዲነግስ፤ ፍቅር እንዲያይል፤ ቤተሰባዊነት እንዲጠናከር፣ ቱባ ባህላችን እንዲታወቅ ያደርጋል።
‹‹ቤት ለእንቦሳ ቤት ያፈራው ነገር የሚቀርብበት ነው›› የሚሉት ዲያቆን ሰለሞን፤ እንግዳ ሆኖ የመጣ ደግሞ ይህንን አድርግልኝ አይልምና መተሳሰብ እንዲሰፍንና ስለአንድነት ብቻ እንዲታሰብ ሰፊ ዕድል የሚሰጥ ነው ይላሉ። ስለሆነም አሁን በአገሪቱ ያለው መጥፎ ስዕል በእነዚህ ዓይነት መልካም ሀሳቦች መቀየር ያስፈልጋል። ምክንያቱን ሲገልፁ አገርን ማሳደግ የሚቻለው ተበታትኖ ሳይሆን አንድ በመሆን ብቻ እንደሆነ እየተናገሩ።
ችቦ ብርሃን መሆን የሚችለውና ስያሜውን የሚያገኘው በአንድነት ተሰብስቦ ታስሮ ሲለኮስ ነው ይላሉ ዲያቆን ሰለሞን። ሆኖም ነጠላ ከሆነ ጭራሮ ተብሎ ብርሃን አይሰጥምና ጥቅም አይኖረውም ይላሉ። እናም ለአገራችን ደህንነት አንድ መሆን አማራጭ የለውም የሚል ምክራቸውን ይለግሳሉ። ትክክለኛ ችቦ ሆኖ ለሁሉም ብርሃን ለመሆን መልካም ባህሎቻችን መዳበር አለባቸው ሀሳባቸው ነው። ለዚህም ደግሞ ቤት ለእንቦሳ ማሳያ ነውና በጎንደር ብቻ ሳይሆን በሁሉም ክልልና ከተሞች ይታይ የሚል ሃሳባቸውን አጋርተውናል።
የቤት ለእንቦሳ ዝግጅት ዋና አላማ ለተተኪ ትውልድ የምናስረክባት አገር ምን መሆን አለባት የሚለውን የሚመልስ ነው የሚሉት ዲያቆኑ፤ መጥፎውን ነገር አውጥተው በጥሩ ተግባር እንዲሞሉት የሚያስችልም መሆኑን አበክረው ለማንሳት ይሞክራሉ። ሕዝቡም ቢሆን ከአሉታዊ ይልቅ አወንታዊውን እያሰበ አንድ የሚያደርግን ነገር እንዲያፈልቅ ያደርጋል። እናም በቤት ለእንቦሳ መጠራራቱ ለአንድነት እንጂ ለተቃርኖ እንጠቀምበትም ይላሉ።
ሰብሳቢው እንደሚሉት፤ እንግዳው ቤት ለእንቦሳ የሚባለው ለሁሉም ነገር አዲስ በመሆኑ ነው። ስለዚህም ሳይንገላታ ተደስቶ ወደመጣበት እንዲመለስ ለማድረግ ብዙ ዝግጅት ተደርጓል። ለአብነትም መጠፋፋት እንዳይኖር ሲገቡ የሚሰጣቸው አድራሻ አለ። የተጠናከረ ጥበቃ ቢኖርም ሕዝቡ ለዝርፊያ እንዳይጋለጥ የኤቲኤም ማሽን በአማካኝ ቦታዎችና በሆቴሎች ውስጥ ዝግጁ ነው።
‹‹በቤት ለእንቦሳ አቀባበል እንግዳው ‹እንቦሳ እሰሩ› እያለ እንዲገባ መጀመሪያ ሕዝቡ ከዚያ ሆቴሎች ከክፍላቸው በተጨማሪ ጥሩ ጥበቃ አስቀምጠው ድንኳን ሊዘረጉ አስበዋል›› ያሉት ዲያቆን ሰለሞን፤ ቤተክርስቲያናትም በአዳራሾቻቸውና በድንኳኖች አሸብርቀው እየጠበቁት መሆኑን፣ ከዚያ ሲያልፍ ደግሞ ዩኒቨርሲቲዎች ጭምር እንግዶችን በቤታቸው ለማሳረፍ ዝግጅታቸውን መጨረሳቸውን ይናገራሉ። ስለሆነም እንግዶች በዓሉ ኢትዮጵያዊነት ቀለም እንዲኖረው ለማድረግ በአለባበስም ሆነ በተግባር ሊያሳዩ እንደሚገባ አሳስበዋል።
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በቤት ለእንቦሳ ለመስተናገድ ከጋሞ 1200 ሽማግሌዎች ሲመጡ ከኤርትራ ከጎረቤት አገር ኤርትራም ተጋባዥ እንግዶች እንደሚኖሩ ታውቋል። ከሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች እንዲሁ በርካቶች ታዳሚ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል። ይህንን ሁሉ ሕዝብ ለማስተናገድ ደግሞ ጠንካራ ክትትልና አቀባበል ማድረግ የግድ ነው። በመሆኑም እንግዶቹ የሚያርፉበት ስፍራ ብቻ ሳይሆን አገልግሎት የሚያገኙባቸውን ተቋማት ጭምር የማሳየቱ ተግባር የአስተባባሪ ኮሚቴውና የሁሉም ማህበረሰብ ኃላፊነት ነው።
አዲስ ዘመን ጥር 3/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው