ዛሬ በኪነጥበቡ ዘርፍ ሀብት የሆኑ ሰዎች የመዘከርን ፋይዳ ለመረዳት እንሞክራለን። ታዲያ ይህን ጉዳይ ስናነሳ በደረቁ ሳይሆን ተዘካሪውን መርጠን በርሱ የህይወት ደርዝ ላይ እየተጓዝን ጭውውታችንን በማድራት ነው አላማችንን ግብ እንዲደርስ የምንጥረው። ለዚህ ምክንያት ደግሞ የዚህ ፅሁፍ አዘጋጅ አገር በቀል እውቀቶች ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፉት በተለይ በኪነጥበቡና በባህሉ ዘርፍ ያሉት በተለይ በግለሰቦች ጥረት እንደሆነ በማመኑ ነው።
ለመሆኑ የአገር በቀል ዕውቀት ምንድነው?
ይህን ጥያቄ ምሁራን በተለያየ መልኩ በዚህ መንገድ ይመለከቱታል። በዋናነትም ለሁለት ይከፍሉታል። የመጀመሪያው ክፍል የአገር በቀል ዕውቀት የአንድ ማኅበረሰብ መለያ የሆነ፣ የተካበተ የነገሮችና ሁኔታዎች ዕይታ፣ የአስተሳሰብና የግንዛቤ ችሎታ ዘርፈ ብዙ የባህላዊ አሠራር ሥርዓትና ልማድ ተመጣጣኝ ቴክኖሎጂና ክህሎትን ሁሉ ይመለከታል።
እንደ ዘርፉ ተመራማሪዎች ከሆነ የአገር በቀል ዕውቀት በሁለት ምድቦች ይመደባል። አንደኛው ምድብ የአገር በቀል ዕውቀት ተቋማዊ የማኅበረሰብ ዕውቀት (Tacit) ይባላል። ይህ የአገር በቀል ዕውቀት ከማኅበረሰቡ ትዕይንተ ዓለም (World View) የሚመነጭ፣ በማኅበረሰቡ የእርስ በርስ ግንኙነትና ከተፈጥሮ ጋር ባለው መስተጋብር ውጤት ላይ የተመሠረተ፣ የማኅበረሰቡን የጋራ ማንነት ገላጭ የሆነና ማንኛውም ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ዘመን ተሻጋሪ እሴቶች ሁሉ ያቀፈ ነው።
ሃይማኖት፣ ሥነ ቃል፣ ወግ፣ ትውፊት፣ አፈ ታሪክ፣ ተረት፣ ተረትና ምሳሌ፣ ሞራል፣ ዘርፈ ብዙ የማይዳሰስ ባህል፣ የአሠራር ሥርዓታት (የቅራኔ አፈታት፣ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምና ልማት፣ የምግብ አዘገጃጀት፣ የአለባበስ፣ የዳኝነት፣ የባህላዊ አስተዳደር መዋቅር፣ ወዘተ) ሁሉ በዚህ የአገር በቀል ዕውቀት ምድብ ይካተታል። ይህ የአገር በቀል ዕውቀት ዘርፍ ከማኅበረሰቡ የጋራ ሥነ ልቦናና ታሪክ ጋር በጥብቅ የተቆራኘ በመሆኑ የዕውቀቱ መጥፋት ወይም መዳከም የማኅበረሰቡ ማንነት መዳከም ወይም መጥፋት አመልካች ነው። ዕውቀቱ እንደ ማኅበረሰቡ የዕድገት ደረጃ በሥነ ቃል ወይም በሥነ ጽሑፍ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሊተላለፍ ይችላል።
ሁለተኛው ምድብ የአገር በቀል ዕውቀት በጠበብት ወይም የአካባቢ ባለሙያዎች የተያዘ ዕውቀት (Explicit) ሲሆን፣ የዕውቀቱ ባለቤቶች በማኅበረሰቡ ውስጥ ታቅፈው የሚኖሩ በመሆኑ በግል የያዙት ዕውቀት የማኅበረሰብ ዕውቀት አካል ነው። ይህ ዕውቀት የአካባቢውን ማኅበረሰብ፣ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም፣ አያያዝና ጥበቃ ሥርዓት የሚጠቁም ሲሆን፣ ዕውቀቱ በብዙኃኑ ሲሰርፅና ሲስፋፋ ወደ ተቋማዊ የማኅበረሰብ ዕውቀት የመሸጋገር ዕድል አለው። ማኅበረሰቡ ዕውቀቱን ቀስ በቀስ የጋራ ዕውቀት (Common knowledge) ስለሚያደርገው በአንድ የአካባቢ ጠበብት ብቻ የተያዘ ዕውቀት ሆኖ አይቀርም። የአገር በቀል ዕውቀት የይዞታ ባለቤትነት (Patent Right) የሌለው በዚህ ምክንያት ነው። እያንዳንዱ የጠበብት ዕውቀት ማለትም የሥር ማሽ ሕክምና፣ ሽመና፣ ሸክላ ሥራ፣ አናጢነት፣ ግንበኝነት፣ አንጥረኝነት፣ ፋቂነት፣ የአካባቢ ባህላዊ ግብርና ዘዴ (ጥምር ግብርና፣ ቅይጥ ግብርና) ወዘተ ልዩ ዕውቀት ባካበቱ የማኅበረሰቡ አባላት መንጭቶ ቀስ በቀስ በመዳበር ወደ ሌላው የማኅበረሰቡ አባል በልምድ ቅስሞሽ ሲተላለፍና በስፋት ሲሠራጭ ተቋማዊ ዕውቀት ሊሆን የሚችል የአካባቢ ማኅበረሰብ ዕውቀት ይሆናል።
መንደርደሪያ
ከዓመታት በፊት «እስኪ ቴአትር እንይ» በሚል ርዕስ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ጥበባት ትምህርት ቤት የመጀመሪያውን የቴአትር ፍስቲቫል ማዘጋጀቱ የሚታወስ ነው። ይህ ፌስቲቫል ከጥቅምት 26 እስከ ህዳር 6 ቀን 2007 ዓ.ም የቆየ ነበር። በጊዜው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ጥበባት ትምህርት ቤት ዘጠኝ ቴአትሮች ቀርበው ነበር። እዚህ መሰናዶ ላይ እግር ጥሎኝ የመገኘት እድሉን አግኝቼ ነበር። መቶ ዓመታትን ባስቆጠረው የቴአትር ጥበብ ውስጥ አሻራቸውን ያስቀመጡ ስምንት ባለሙያዎችን ለማስታወስም በምሁራን ቀርቦ የነበረው ጥናታዊ ፅሁፍም ትኩረቴን ጨምድደው ከያዙት ጉዳዮች መካከል እንደነበር አስታውሳለሁ። በተለይ ደግሞ በመጨረሻው የመታሰቢያ ቀን እንዲታወስ የተመረጠው የትውፊት አባቱ ፍሰሐ በላይ ይማም አሁንም ድረስ ጊዜውን መለስ ብዬ እንድመለከተው የሚያስገድዱኝ ተወዳጅ ሁነቶች ውስጥ ዋንኛው ነው። በጊዜው የእዚህን የጥበብ ሰው የመታሰቢያ ዕለት ሊያበስር የተመረጠው ደግሞ ተዋናይ ሽመልስ አበራ (ጆሮ) ነበር። እናም ዛሬ ከአምስት ዓመት በኋላ መቅረጸ ድምፄን ስፈታትሽ የዚህን ዘመን አይሽሬ የተውኔት ባለሙያ ህይወት እና ስራዎች የሚያስታውስ ድምፅ ማግኘት ቻልኩ። እናም ‹‹ትውስታ ፍሰሀ በላይ ይማም›› በሚል ርእስ ሰድሬ በዚህ መልክ እነሆ አልኳችሁ።
የተውኔትና የትውፊት አባት
ሽመልስ አበራ ከፍሰሐ በላይ ይማም ጋር «የወፍ ጎጆ» የተሰኘውን የፍሰሐ በላይ ይማምን ተውኔት አብረው ሲሰሩ ነበር የተዋወቁት። የቴአትር ጥበባት ትምህርት ቤት እነዚህን የጥበብ ሰዎች በማስታወሱ በጣም መደሰቱን አስቀድሞ በሚሠራበት ዕድሜው በሞት ከተለየው ፍስሐ በላይ ይማም ብዙ መማር ይችል እንደ ነበር ነው ያስታወሰው። «እሱ የተፈጥሮ ፀጋን የታደለ ነበር። እነ ኃይሉ ጸጋዬ፣ ገነት አጥላው፣ ማንያዘዋል እንደሻው ስለ ጉብዝናው የሚያወሩለት ጎበዝ ደራሲና ተዋናይ ነበር። ይህን ባለሙያ የመታሰቡን አስፈላጊነት በፅኑ ይደግፋል። ሌሎችም በርካታ ባለሙያዎች እንዲታሰቡ እና የያዙት አገር በቀል እውቀት ወደ ትውልድ እንዲሻገር ማድረግ አስፈላጊ ነው» በማለት ነበር ቀኑን ያበሰረው።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ጥበባት መምህር አቶ አሰፋ ወርቁ በአንድ ወቅት ስለዚህ አንጋፋ የቲያትር ባለሙያ እንዲህ ብለው ነበር። በህይወት ታሪኩና ስራዎቹ ዙሪያም አጭር ዳሰሳዊ ጥናት አድርገዋል። አጭር በሆነው የህይወት፣ በጥበብ ስራዎቹ ላይ ትኩረት ያደረገም ነበር። ፍስሃ በህይወት እያለ ስሙን እስከ አያቱ እንዲጠራ ይፈልግ ስለ ነበር እስከ አያቱ ነው የሚጠሩት። እኛም ይህን ፅሁፍ ስናዘጋጅ ፍላጎቱን ታሳቢ ለማድረግ ሞክረናል።
ከፍስሐ በላይ ይማም የተውኔት ሥራዎች ውስጥ ቀዳሚዎቹንና በትውፊት ላይ የተመሰረቱትን ሦስት ሥራዎቹን «አልቃሽና ዘፋኝ»፣ «ስመኝ ስንታየሁ» እና «ሆድ ይፍጀውን» በሦስቱ ተውኔት ውስጥ የቀረፃቸውን ገጸ ባህሪያትን ተወዳጅነትን ካተረፉለት መካከል ይጠቀሳሉ። ከድርሰት ውጪ በተመራማሪነቱም የሚታወቅ እንደመሆኑ በምርምር ሥራዎቹም ላይ ትኩረት የሚያደርገው በትውፊታዊ ሥራዎች ነው። «ፋጢማ ቆሪ» የወሎ አካባቢ ትውፊት ሲሆን፤ ሁለተኛው «አንገር» የሚባለውና ሙስሊም ሴቶች ባላቸው ሲሞት የሚያደርጉትን ባህላዊ ትውፊት የሚያስቃኝ ነው።
አቶ አሰፋ በጥናታቸው እንደሚጠቁሙት ፍስሐ በላይ ይማም መምህር ጸሐፊ ተውኔት፣ ድምጻዊ፣ የግጥምና ዜማ ደራሲ፣ ተወዛዋዥ፣ የባህላዊ ሙዚቃ አምራችና ተጫዋች፣ ሽክላ ሰሪ፣ ሸማኔና የአገር ባህል ልብሶች አዘጋጅ፣ የሙዚቃና የተውኔት ቁሳቁስና አልባሳት አዘጋጅና ዲዛይነር፣ የስጋጃ ምንጣፎች አምራችና ሰዓሊም ጭምር እንደነበር ይገልፃሉ። የሕይወት፣ የጥበብና የምርምር ሥራዎቹን የሚዳስሱ ሁሉ በባህሪው እና በጥልቅ እውቀቱ ሳይደነቁ እንደማያልፉም ይናገራሉ።
የዛሬ 61 ዓመት ነሐሴ 15 ቀን 1946 ዓ.ም በደሴ ከተማ ልዩ ስሙ ዳውዶ በሚባል መንደር ከአባቱ ከአቶ በላይ ይማምና ከእናቱ ከወይዘሮ ጣይቱ አመዴ ነው የተወለደው። ዕድሜው ለትምህርት ሲደርስ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በእቴጌ መነን፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በወይዘሮ ስሂን የቀለም፣ የሙያና የቴክኒክ ትምህርት ቤት በንግድ የትምህርት ዘርፍ ተከታትሎ አጠናቋል። ከ1963 ዓ.ም ጀምሮ የላሊበላ ወሎ ባህል አምባ ኪነት እስከተመሰረተበት እስከ ታኀሣሥ 5 ቀን 1972 ዓ.ም ድረስ በቀድሞው በወሎ ክፍለ አገር ትምህርት ቤቶች ጽህፈት ቤት በቢሮ ሠራተኝነት ከዛም በቀድሞው የቃሉ አውራጃ ክችሮ ትምህርት ቤት በመምህርነትና በርዕሰ መምህርነት ለዘጠኝ ዓመታት አገልግሏል።
በ1974 ዓ.ም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመግባት በታሪክ ክፍለ ትምህርት ቢመደብም ፍላጎቱና ተሰጥኦው ቴአትር በመሆኑ ከታሪክ ትምህርት ክፍል ወደ ቴአትር ተቀይሮ 1977 ዓ.ም በቴአትር ጥበባት ትምህርት ተመርቋል። ዩኒቨርሲቲ ከተመረቀ በኋላም ከ1978 ዓ.ም ጀምሮ በቴአትር ጥበባት ትምህርት ክፍል ተቀጥሮ እስከ 1985 ዓ.ም ድረስ በመምህርነት አገልግሏል።
ከኪነ ጥበብ ጋር የተዋወቀው ገና 13 ዓመቱ ነበር። ወይዘሮ ሲሂን ትምህርት ቤት ተማሪ ሳለም በትምህርት ቤቱ የሙዚቃና ድራማ ክበብ ለቴአትር ያለውን ፍላጎት አዳብራል። መምህርና ርዕሰ መምህር በሆነባቸው ዘጠኝ ዓመታትም የወሎን ህዝብ ትውፊት፣ ያኗኗር ዘይቤ፣ ወግና ባህል በሩቁ ሳይሆን በቅርቡ፣ በጠባቡ ሳይሆን በሰፊው፣ በረግረጉና በገፈቱ ሳይሆን በጥልቀትና በብስለት ለመተዋወቅ፣ ለማወቅ ለማጥናትና ለመመራመር ዕድሉን ፈጥሮለታል። የወሎ ላሊበላ ኪነት ቡድን ሲቋቋም የዩኒቨርሲቲ መምህርነት ሥራውን ሙሉ በሙሉ ተሰናብቶ ከኪነት ጋር በቁሳዊና ትውን ፎክሎር ተመራማሪነት በተወዛዋዥነት ተቀጥሮ ሠርቷል።
ብዙዎች «ፍስሐ በላይ ይማም አስተዋዮችንና የአዛዦችን ትኩረትና ንሸጣ አላገኘም እንጂ በኪነ ጥበብ ስብዕናው፣ በፎክሎሪስትነቱ፣ በተለይም በትውፊት ተመራማሪነቱ ላቅ ያለና ልዩ ስፍራ የሚሰጠው ከፍ ያለ ቦታ ላይ የሚሰየም ታላቅ ህያው ሰብዓዊና ትውፊታዊ ቅርስ ነው» በማለት ይገልፁታል።
የወሎ ባህል አምባ ላሊበላ ኪነት ቡድን ከተቀላቀለበት ከ1972 ዓ.ም ጀምሮ ህይወቱ ከአፀደ ስጋው ተለይታ የቀብር ሥነ ሥርዓቱ በደሴ ከተማ ደብረ መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን እስከ ተፈጸመበት ሐምሌ 26 ቀን 1992 ዓ.ም ድረስ ፍስሐ ይማም በውል የሚታወቁ 20 ተውኔቶችን የፃፈ ሲሆን፤ 17ቱ በተለያዩ የቴአትር ቤቶችና መድረኮች ላይ አቅርቦ በአገራችን የተለያዩ ክፍለ አገሮች በቀድሞ አጠራር የጦር ካምፖችና የማሠልጠኛ ተቋሞች አሳይቷል። ቀሪዎቹ ሦስት ቴአትሮች በሳንሱርና በልዩ ምክንያቶች ለብርሀነ መድረክ አልበቁም።
አልቃሽና ዘፋኝ፣ ስመኝ ስንታየሁ፣ ሆድ ይፍጀው፣ ጅራት ይዞ ሙግት፣ ከያኒያን፣ መካሻ፣ የሁለት እናት ልጅ (በሳንሱር ምክንያት የታገደ) ገዛች፣ የትግል ሰንሰለት፣ ደመላሽ፣ ምን ይሻላል፣ ጠኔ ሲሞርድ፣ አዲስ ሕይወት፣ የቤተሰብ ችሎት፣ አሻግሬ መሰረት፣ የወፍ ጎጆ፣ የጨረቃ ቤት፣ ኡማና ጉማ፣ ለምኖ ለለማኝ፣ የሚሉት ቴአትሮቹ የሕይወት ዘመን ቱሩፋቶቹ ሲሆኑ፤ ከእነዚህ ውስጥ ሁለቱ ያልታዩ ናቸው። ፍሰሐ በላይ ይማም በሰፊው የገጠሩን፤ በጠባቡ ደግሞ የከተማውን ማኅበረሰብ ታሪክ አንጸባርቋል። በመንግስቱ ለማ ያላቻ ጋብቻ፣ በጸጋዬ ገብረመድህን «ሀሁ በስድስት ወር»፣ «እናት አለም ጠኑ»፣ በኬንያዊው ጸሐፊ ተውኔት በኒጊምቢ ዋቴንቦ ዲዳን ኬማቲ፣ በራሽያዊው ጸሐፊ ተውኔት አንቶን ቼኮቭ ድራማዎች ውስጥ በአዘጋጂነትና በተዋናይነት ተጫውቷል።
በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚስተዋሉትን ያለዕድሜና የግዳጅ ጋብቻ ጠለፋን፣ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ የአካላዊ፣ ሥነልቦናዊና ማህበራዊ ጥቃቶችን፤ የሴቶችን ሥነ ሕይወታዊ፣ ሰብዓዊና ጾታዊ፣ መብቶችንና ነፃነቶችን፣ ስርቆትን፣ ሙስናን ስካርን፣ ዝሙትን ልመናን፣ ሠርግንና ሞትን፣ ክህደትን፣ በቀልን፣ የቤት ችግርን በቀድሞውና በአሁኑ ትውልዶች መካከል የሚታዩትን የስሜትና ፍላጎት፣ የአስተሳሰብ አዕምሮና የዓላማ ልዩነቶችን ስራዎቹ ይዳስስ ነበር።
መቋጫ
በአገራችን ኢትዮጵያ የብሔረሰቦችን ሥርጭት መሰረት ያደረጉ በርካታ የአገር በቀል ዕውቀቶች አሉ። በኢትዮጵያ የሚኖሩ ከ86 በላይ ብሔረሰቦች የሚጋሯቸውና አንዱ ከሌላው የሚለዩባቸው የአገር በቀል ዕውቀቶች አሏቸው። ይሁን እንጂ የዘመናት ተጨባጭ ሁኔታ በፈጠረው ዕድል በባህል ውርርስና ልውውጥ ምክንያት የአገራችን ብሔረሰቦች የበርካታ አገር በቀል ዕውቀቶች የጋራ ባለቤቶች ሆነዋል። በዚህ የተነሳም በአገራችን ይህ ዕውቀት የዚያኛው ብሔረሰብ ልዩ ዕውቀት ነው፣ ያኛው የዚያኛው ብሔረሰብ ነው ብሎ በውል ለመለየት አያስደፍርም። በመሆኑም እኛ ኢትዮጵያውያን የጋራ አገር በቀል ዕውቀት ባለቤት ሆነናል ማለት ይቻላል። ይህን ደግሞ እንደ ፍሰሀ በላይ ይማም አይነት ጸሐፊ ተውኔት፣ ድምጻዊ፣ የግጥምና ዜማ ደራሲዎች በሕይወት፣ በጥበብና በምርምር ስራዎቻቸው እየዳሰሱ ለትውልድ ያሻግሩታል። አገርም እንዲህ ባለው መንገድ ትሰራለች። ሰላም!
አዲስ ዘመን ጥር 3/2012
ዳግም ከበደ