ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹምና የዘመቻ መምሪያ ኃላፊ ናቸው፡፡ በወቅታዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከእርሳቸው ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡ የፈረሰው የኢትዮጵያን ባሕር ኃይል መልሶ በማቋቋሙ ዙሪያ፤ በቅርቡ በቤተመንግሥት አካባቢ ስለተከሰተው ሁኔታ፤ በምዕራብ ወለጋ ኦነግ ህጋዊ ያልሆነ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው ስለመባሉ ትኩረት የሰጠናቸው ነጥቦች ናቸው፤ ይከታተሉት፡፡
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ ቀደም ሲል የነበረው ጠንካራ ባህር ኃይል መፍረሱ ይታወሳል፤ ለምን ፈረሰ? አሁን ደግሞ እንደ አዲስ ይቋቋማል ተብሏል፤ ለምን አስፈለገ ?
ጄኔራል ብርሃኑ፡- ቀደም ሲል የነበረን ባሕር ኃይል ፈርሷል፡፡ 27 ዓመታት ሙሉ ያለ ባሕር ኃይል ኖረናል፡፡ ይህ የሆነው የባሕር በር የለንም የሚል አስተሳሰብ ስለነበር ነው፡፡ የነበረን ባሕር ኤርትራ ስትገነጠል አብሮ ሄዷል፡፡ ዙሪያውን በመሬት ተቆልፈን ነው ያለነው፡፡ አሁን ወደ ስልጣን የመጣው የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አመራር የቀደመውን ሃሳብ ውድቅ አድርጎታል፡፡ ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር ስለሆነች ባሕር ኃይል እንደሚያስፈልጋት ተወስኗል፡፡ ሃሳቡም ተገቢና ትክክል ነው፡፡ እኛ ባሕር በር ወይንም ወደብ ባይኖረንም ለቀይ ባሕርና ለሕንድ ውቅያኖስ በጣም ቅርብ ነን፡፡ በባሕሩና በእኛ መካከል ያሉ አንዳንድ አገሮች እጅግ በጣም ትናንሽ ናቸው፡፡ በአንዳንድ ስፍራዎች እኛ ድንበር ላይ ሆነን መድፍ ብንተኩስ ወደ ባሕሩ መጣል እንችላለን፡፡ ቅርበቱ ይህን ያህል ነው፡፡
አሁን የተለያዩ የውጭ ሀገራት ከሩቅ እየመጡ በሶማሊያ፣ በጅቡቲ፣ በፑንት ላንድ፣ በኤርትራም ጭምር የባሕር ኃይል ጦር ሰፈር እየመሰረቱ ባሉበት ሁኔታ፤ እኛ ከባሕሩ 60 ኪሎ ሜትር ርቀን ለምን ባሕር ኃይል አይኖረንም? ባሕሩ የእኛ መተላለፊያ ነው፡፡ ወጪና ገቢ ንግዳችን በእዚያ ያልፋል፡፡ በዚያ ላይ ትልቅ ሕዝብና ታላቅ ሀገር ነንና ባሕር ኃይል ሊኖረን ይገባል ተብሎ ተወስኗል፡፡ በዚህ የመንግሥት ውሳኔ መሰረት አዲስ ባሕር ኃይል የማቋቋም እቅድ አለ፡፡ ለዚህም ከሚያግዙን ሀገሮች ጋር እየተነጋገርን ነው፡፡ ምን ያህል አደረጃጀት፤ ምን ያህል አቅም ይኑረው ? የሚል እንደገና የማዋቀር ሥራ እየሠራን እንገኛለን፡፡
ይሄን የምናደርግበት መሰረታዊ ምክንያት ስትራቴጂካዊ ውሳኔ ስለሆነ ነው፡፡ ለህንድ ውቅያኖስና ለቀይ ባሕር ቅርብ ነን፡፡ በዚያ ላይ የሚመላለስ የእኛ ጥቅም አለ፡፡ በዚያ ያሉ ሀገራት ለተለያዩ ሀገራት የጦር ሰፈር እየሰጡ ስለሆነ እኛም የጦር ሰፈር እንወስዳለን፡፡ በባሕሩ ላይ እንንሳፈፋለን፡፡ በባሕሩ ላይ ያለንን ጥቅም እናስከብራለን፡፡ አያድርገውና ቀጣናዊ ቀውስ ቢፈጠር ባሕር ላይ ምንም ጉልበት ከሌለ እንጎዳለን፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህን ሁሉ አስበውና መርምረው ነው የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል መፍረሱ አግባብ አይደለም እንደገና ተመልሶ መደራጀት አለበት ያሉት፡፡ ተጽእኗችን በባሕሩ ላይ መኖር አለበት፡፡ ከሩቅ መጥተው የተለያዩ ሀገራት ተጽእኖ እየፈጠሩ ነው፡፡ እኛ ትልቅ ሀገር ነን፡፡ የ100 ሚሊዮን ሕዝብ ሀገር ነን፡፡ በ60 ኪሎ ሜትር ባሕር አስቀምጠን የብስ ላይ ብቻ ተገድበን የምንቀመጥበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ በሰፊው አስበን መሥራት አለብን ተብሎ እየተሠራ ነው፡፡ ስለዚህም እጅግ ብርቱና ጠንካራ ዘመናዊ ቴክኖሎጂና መሳሪያ የታጠቀ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል እንገነባለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- ሽሮ ሜዳ አካባቢ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ጠቅላይ መምሪያ ቢሮ ነበር፡፡ አሁን ሌላ አገልግሎት እየሰጠ ነው፡፡ በእዚያ የባህር ኃይሉን አደረጃጀት፣ አወቃቀርና ሌላም ጉዳይ የሚገልጹ መረጃዎች ነበሩ፤ እንዲሁም የባሕር ኃይል አካዳሚም ነበረን፡፡ መረጃዎቹን አሁን ለተጀመረው ባሕር ኃይሉን መልሶ የማደራጀት እንቅስቃሴ በመነሻነት መጠቀም አይቻልም ? የጦር መርከቦቻችንና ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎቻችንስ የት ደረሱ ?
ጄኔራል ብርሃኑ፡- እውነቱን ለመናገር አሁን ሰነዶቹ የት ደረሱ የሚለው መረጃ የለኝም፡፡ የሰማሁት ጥቅል መረጃ ግን ያን ጊዜ ድል ያደረገው ኃይል ወስዶታል የሚል ነው፡፡ ከአሁን በኋላ ባሕር ኃይል ምንም አያደርግልንም ስለተባለ የተሸጠና ወደ መርከብ ድርጅት የገባም ይኖራል፡፡ ትናንሽ ጀልባዎች ደግሞ በወቅቱ አባል የነበሩ ባሕር ኃይሎች ይዘው የሄዱት እንዳለም ሰምቻለሁ፡፡ ለሁሉም በአሳዛኝ ሁኔታ ልክ በጦርነት እንደተሸነፈ ሀገር ባሕር ኃይል ፍርክስክሱ ነው የወጣው፡፡ ባለቤት ስላልነበረው ፈራርሷል፡፡ እንደ ሀገር እጅግ ያሳዝናል፤ ይጸጽታል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በተለያየ ሙያ ተሰማርተው የነበሩና አሁን በሕይወት የሚገኙ ባሕረኞችን መንግሥት ክፍሉን መልሶ ለማቋቋም በሚያደርገው ጥረት ለመጠቀም አስቧል ?
ጄኔራል ብርሃኑ፡- አሁን የሚጠቅሙን ካሉ ተነጋግረን እንዲሠሩ እናደርጋለን፡፡ በአዲስ መልክ ባሕር ኃይሉን እናደራጅ ስንል በሀገር ውስጥም በውጭም ያለውን ኃይል መጠቀማችን አይቀርም፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሰዎች ካሉ እንጠራቸዋለን፡፡ ዞሮ ዞሮ ኢትዮጵያ ሀገራቸው ናት፡፡ አሁን የሚያስፈልገን ትልቁ ነገር ያለፈውን ረስተን በአዲስ መንፈስ፣ ትጋትና ቁርጠኝነት ሀገራችንን ለመለወጥ ለማሳደግ ተባብረን፣ ተጋግዘንና ተደምረን መሥራት ነው፡፡ ጥሪ እናደርግላቸዋለን፤ ተሳተፉ እንላቸዋለን፡፡ ግን ያኔ ባሕር ኃይል የነበሩ ሰዎች ዛሬ ከሃያ ሰባት ዓመት በኋላ የሚኖራቸውን ዕድሜ ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ዕድሜ ሳይሆን እውቀ ታቸውና ሰፊ ልምዳቸው ይጠቅማል ከሚል ነው?
ጄኔራል ብርሃኑ፡- ችግር የለብንም፡፡ አቅሙ ያላቸውን እናሳትፋቸዋለን፡፡ አሁን ብዙዎቹ በሀገር ውስጥ ያሉ አይመስለኝም፡፡ በብዛት በውጭ ነው ያሉት፡፡ ሀገር ቤትም በውጭ ያሉትም እኛን ለማገዝ ፈቃደኛ የሆኑ ካሉ አብረን እንሠራለን፡፡ እንኳን የራሳችንን ወገኖች ቀርቶ ሩቅ ሄደን የውጭ ዜጎችን እየጋበዝን አይደለም እንዴ?
አዲስ ዘመን፡- ሰሞኑን በተለያየ መንገድ የሚሰራጩ መረጃዎች እንደሚያመ ለክቱት በምዕራብ ወለጋ በኩል በኦነግ ሥም ታጣቂዎች ከሠራዊታችን ጋር ግጭት ውስጥ ገብተዋል፡፡ አዲስ አበባ ያሉት የኦነግ ከፍተኛ አመራሮች ሲጠየቁ እኛ በሰላም ለመሥራት ነው እንጂ የመጣነው የጦርነት ፍላጎትና ዓላማ የለንም ብለዋል፡፡ በዚህ ረገድ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?
ጄኔራል ብርሃኑ ፡- ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ያለው ነገር መሬት ላይ ካለው እውነት ጋር አይገናኛም፡፡ ወሬን መነሻ አድርጎ ሚዛናዊነቱን ሳይጠብቁ ማቅረብ አስቸጋሪ ነው፡፡ ማህበራዊ ሚዲያው ትንሽ መነሻ ነው የሚፈልገው፡፡ ማጣራት ሚዛናዊ ማድረግ ብዙ ይቀረዋል፡፡ ትንሽ መነሻ ካገኘ ከራሱ አመለካከት ጋር አያይዞ ነው የሚያሰራጨው፡፡ ይሄ ደግሞ ሀገርም ሕዝብም ይጎዳል፡፡ ሰከን ብሎ ማሰብ ማጣራት ሚዛናዊ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
የኦነግ ሰዎች በሰላም እንታገላለን ብለው ገብተዋል፡፡ የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ አዲስ አበባ ነው ያለው፡፡ ይሄ ድርጅት ተስማምቶ የመጣው በሰላም ለመታገል ነው፡፡ አሁንም በሰላም ነው የምንታገለው የሚል አቋም አለው፡፡ ትጥቅ ይዞ የመቀጠል ዓላማ የለውም፡፡
አቶ ዳውድ ኢብሳ ባለፈው ተናገሩ የተባለውን (ለዋልታ ሚድያና ኮሚኒኬሽን ኮርፖሬት በሰጡት ቃለ መጠይቅ ኦነግ ትጥቅ ለመፍታት ሃሳብ የለውም የሚል መልዕክት ያዘለ እንደነበር ይታወሳል) ሰምቼዋለሁ፡፡ ተናገሩት የተባለውና ድርድር ሲደረግ የነበራቸው አቋም አንድ አይደለም፡፡ ኦነግ ግማሹን የታጠቀ ኃይል አስገብቷል፤ ግማሹ ቀርቷል፡፡ በመካከላቸው አንድ የተፈጠረ አለመግባባት አለ፡፡ ድርጅቱ ወስኖ ሲገባ በከፊል ተወያይቶ በከፊል ሳይወያይ ነው የመጣው፡፡ እነዚያ ያልተወያዩ ሰዎች አኩርፈዋል፡፡ ለምን አይነገረንም? ለምን አናውቅም? ለምን ውሳኔው ከላይ ወደታች ይጫንብናል? የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡ እርስ በራሳቸው እየተነጋገሩ ነው፡፡ አሁን ጦርነት የለም፡፡ አልፎ አልፎ እንደ ዲስፕሊን ጥሰት የሚታዩ ነገሮች ይታያሉ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ ትናንሽ ችግሮች አሉ፡፡ እኛም ድርጅቱም ለመፍታት እየሞከርን ሲሆን፤ በጋራ እየሠራን ነው፡፡ ይፈታል ብዬ አስባለሁ፡፡ እነዚያ ያኮረፉ ሰዎች ያኮረፉበትን ምክንያት ገልጸው እርስ በራሳቸው ተነጋግረው ችግራቸውን እንዲፈቱ እኛ ድጋፍ እያደረግን ሲሆን፤ እነርሱም ለመፍታት እየሞከሩ ይገኛሉ፡፡ ይፈታል ብለን እናምናለን፡፡ ወደ ጦርነትና እርስ በእርስ ግጭት የሚሄድ ነገር ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡
አዲስ ዘመን፡- የሀገር መከላከያ ሠራዊታ ችን በምን ቁመና ላይ ነው ያለው? እየተካሄዱ ያሉት ሪፎርሞችስ በምን ደረጃ ላይ ነው የሚገኙት ?
ጄኔራል ብርሃኑ፡- ሠራዊታችን ጀግና፣ በዲስፕ ሊንም የታነጸ ነው፡፡ ሪፎርሙን ተቀብሏል፡፡ በሪፎርሙ መሰረት የአደረጃጀትና የአሰፋፈር ለውጥ እያደረገ ሲሆን፤ አዳዲስ አመራሮች ወደፊት በመምጣት ላይ ናቸው፡፡ አጠቃላይ ሪፎ ርሙ በስድስት ወር የሚያልቅ አይደለም፤ የዓመታት ሥራ ይሆናል፡፡ ውስጣዊ መረጋጋቱና ለሕገ መንግሥቱ ጥበቃ ያለው ቁርጠኝነት እጅግ በጣም ጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ባለፈው ቤተ መንግሥት አካባቢ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ወታደሮች ከእነሙሉ ትጥቃቸው መሄዳቸው በሕብረተሰቡ ውስጥ ጥሩ ስሜት አልፈጠረም፡፡ የዳበረ ልምድ ስላካበታችሁ ሊፈጠር የነበረውን ችግር በመነጋገር ፈታችሁታል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ድንገተኛ ክስተት እንዴት ነው የታየው ?
ጄኔራል ብርሃኑ፡- ቀደም ብዬ ለመናገር እንደሞከርኩት ሠራዊታችን ጀግናና ዲስፕሊን ያለው፤ የእዝ ተዋረዱን የሚጠብቅ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል በእኛ ሰራዊት የውስጥ ደህንነት የሚባል የለም፡፡ እያንዳንዱ በተዋረድ ያለው አመራር ለስርዓቱና ለሀገሩ ደህንነት ነው ተብሎ ይታሰባል፡፡ ደህንነት ሠራዊቱ ውስጥ ማቋቋም ሠራዊት ይከፋፍላል፤ ጀግንነት ያጠፋል የሚል እሳቤ ስላለ እንደዚያ አይደረግም፡፡ 27 ዓመት በዚህ መንገድ የተሄደ ሲሆን፤ ወደፊትም ይቀጥላል፡፡ አንዱ ወታደር አንዱን ወታደር እንዲሰልል አናደርግም፡፡ እምነት ነው የምንፈጥረው፡፡ ሀገሩን ሕዝቡን እንዲወድ መጥፎ ድርጊት እንዳይፈጽም፤ በዲስፕሊን የታነጸ እንዲሆን ከራሱ በላይ ወገኑን ሕዝቡን እንዲወድ ታማኝ አድርጎ መገንባት ነው እንጂ እርስ በእርሱ ስለላ እንዲያካሂድ ከተደረገ ከባድ ነው፡፡
ደህንነት ሠራዊቱ ውስጥ ማቋቋም ቀደም ሲል በነበረው የደርግ ሠራዊት ውስጥም ችግር ፈጥሮ የነበረ ነው፡፡ ቀድሞ ወታደራዊ ደህንነትና ጥበቃ (ወደጥ) በሚል አዛዦችን ሲሰልል ነበር፡፡ ይህም በአዛዦች በኩል ትልቅ ኩርፊያና ችግር ማስከተሉን ብዙዎች ያነሱታል፡፡ በእኛ አሠራር አዛዡ ይታመናል፡፡ በፊት የነበሩ መኮንኖች እንዴት ለሀገራችን እኛ አንታመንም ወይ እንዴት እንሰለላለን ? በሚል ብዙ ችግሮች እንደነበሩ ይናገራሉ፡፡ ይሄ አሠራር ቀደም ባሉት ዘመናት በግብፅ ሰራዊቱ ውስጥም ከፍተኛ ችግር ፈጥሮ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በሶማሊያም ሆነ በኢትዮጵያ ሰራዊትም ላይ ችግር ፈጥሮ የነበረ ነው፡፡ በእኛ ሁኔታ ሕይወቱን ለመስጠት የተሰለፈን ሰው እንዴት ትሰልላለህ ነው የምንለው፡፡ እምነትና ታማኝነት ነው የምንፈጥረው፡፡ የኢንዶክትሪኔሽን ሥራ ነው የምንሠራው፡፡ እርስ በእርሱ ስለላ እንዲያካሂድ ከተደረገ ሰራዊቱ አጠቃላይ ፈረሰ ማለት ነው፡፡ የእኛ ኢንዶክትሪኔሽን ይሄንን አይፈቅድም፡፡ አንዳንድ ሰዎች ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ‹‹ወታደራዊ ኢንተለጀንስ የለም ወይ፤ ኢንተለጀንሱ እንዴት አይሠራም?›› ብለዋል፡፡ እኛ ከውስጥም ከውጭም ሠራዊታችን ውስጥ ኢንተለጀንስ አንዘረጋም፡፡ አንዱ አንዱን የሚሰልልበት ተቋም አንገነባም፡፡ ይሄ ጀግንነትን ይገድላል፤ታማኝነት ያጎድላል፤በራስ መተማመን ያጠፋል፡፡
ቤተመንግሥት የሄዱትን የሰራዊቱን አባላት በተመለከተ እውነቱን ለመናገር እነዚያ 300 ሰዎች መፈንቅለ መንግሥት እናደርጋለን ብለው ተመካክረውና እቅድ አውጥተው አልሄዱም፡፡ የሠራዊቱን የመብት ጥያቄ በመጠቀም ቁስሉን በመቆስቆስ ጠቅላይ ሚኒስትሩን እንደሚወዱና ጥያቄአቸውን እርሳቸው እንደሚመልሱ አስመስለው ቀስቅሰው ወደ ቤተመንግሥት የወሰዷቸው በጣም ጥቂት ግለሰቦች ናቸው፡፡ ይህ አካሄድ ወታደራዊ ሕግን፣ ስርዓትንና የእዝ ሰንሰለትና ተዋረድን የጣሰ ነው፡፡ ከመጨረሻው ወታደር እስከ ከፍተኛው የሠራዊት አዛዥና ኃላፊዎች ድረስ የእዝ ሰንሰለቱ በሚገባ የተደራጀ ነው፡፡ ይሄን አልፎና ጥሶ መሄድ አይቻልም፡፡ ይሁንና ጥቂቶቹ የሰራዊቱ አባላት ደግሞ ዓላማ አላቸው፡፡ ዓላማቸው ቤተመንግሥቱን መበጥበጥ፣ መረበሽና የተኩስ ቀጣና ማድረግ ነበር፡፡
በውይይትና በማረጋጋት መፍታት ይቻላል ብለን አመንን፡፡ በዚያ መንገድ ሄድንበት፤ ተሳካልን፡፡ ደም ካልፈሰሰ ለምን በዚያ መንገድ ተፈታ አይባልም፡፡ ችግሩን ለመፍታት የሄድንበት መንገድ እጅግ በጣም ሊደነቅ ይገባል፡፡ ደም ማፍሰስ ደረጃ ላይ የሚደረሰው የመጨረሻው አማራጭ ሲጠፋ ነው፡፡ አማራጭ እያለ ለምን ደም ይፈሳል ? ይሄ ሠራዊት ሀገሩን ይወዳል፤ ሕገመንግሥቱን ይጠብቃል፤ታማኝ ነው፤ ጀግና ነው፡፡ በሦስት አራት ግለሰቦች የተሳሳተ ቅስቀሳ የሚጠቀም መስሎት ‹‹ሆ›› ብሎ ሄደ እንጂ የመፈንቅለ መንግሥት ዓላማ የለውም፤ አልነበረውም፡፡ እነዛ ሦስት አራት ግለሰቦች ግን በጠነሰሱት ሴራ ሰራዊቱ ሙሉ ትጥቁን እንደታጠቀ ወደ ቤተመንግሥት ሄዷል፤ በእነርሱ ስሌት እንግባ ሲሉ ቤተመንግሥት ያለው የጥበቃ ኃይል አላስገባም ይላል፡፡ በዚህ መካከል ተኩስ ይከፈታል፤ እንበጠብጣለን፡፡ ካገኘንም ጠቅላይ ሚኒስትሩን እንገድላለን ብለው ያቀዱ ነበሩ፡፡
ይህን ዓይነቱን በሀገርና በሕዝብ ሰላም ላይ የተቃጣ ሰላምና ጸጥታን ለማደፍረስና የሀገር መሪን ለመግደል የተጠነሰሰ ሴራን ለመፈጸም ሌላውን ምንም የማያውቀውን የሰራዊት አባል በማታለልና በማሳሳት በመብት ጥያቄና ሽፋን ስም ከፍተኛ አደጋ ለመፍጠር በዋናነት ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ጥቂት ግለሰቦች የሀገሪቱና የመከላከያው ሕግ በሚፈቅደው መሰረት ጦር ፍርድ ቤት ይቀርባሉ፤ በሕግ ይጠየቃሉ፡፡
መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ ሦስት አራት ሰዎች ብቻ አስበው ሌላው የሰራዊት አባል መረጃም በሌለው ሁኔታ ውስጥ ምንም ሳያውቅ እነርሱ በጠነሰሱት ሴራ ቤተመንግሥቱን ለመበጥበጥና ጦር ሜዳ ለማድረግ፤ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድንም ካገኙ ለመግደል ወጥነው እንጀራ ጠያቂውን ወታደር አሰልፈው ሄደዋል፡፡ እዚያ ከደረሱ በኋላ ወታደሮቹ መጠቀሚያ መሆናቸው ገባቸው፡፡ ከገባቸው በኋላ ትጥቅ ፍቱ ሲባሉ ትጥቅ ፈቱ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትጥቅ የፈቱትን አወያዩ፡፡ እነዚህ ሦስት አራት ሰዎች ይሄን ያደረጉበት ምክንያት አልተሳካላቸውም፡፡ ደም አልፈሰሰም፤ ተኩስ አልተከፈተም እንዲሁም ሰዎች አልተጎዱም፡፡ አደጋ ሊፈጥር የነበረውን ችግር በከፍተኛ ጥንቃቄ በብቃት መፍታት ቻልን፡፡
ይህን በመሰለ ሰላማዊ መንገድ ችግሩ በመፈታቱ ለምንድነው አንዳንድ ሰዎች ያላደነቁት የሚለው ነገር በጣም ገርሞኛል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም መደነቅ የሚገባቸው ናቸው፡፡ እርሳቸው እንዳሉትም ወታደር ስለሆኑም ነው ችግሩ የተፈታው፡፡ ሲቪል ቢሆኑ ኖሮ ላይፈቱት ይችሉ ነበር፡፡
ለምን ቤተ መንግሥቱን ደፈሩ? የሚል ነገር ተነስቷል፡፡ በተለያየ ዘመን ይሄ ዓይነቱ ነገር ተከስቷል – በጃንሆይና በደርግ ጊዜም፡፡ በኢሕአዴግ ጊዜም ቤተመንግሥት አልሄዱም እንጂ እንደዚህ ዓይነት ነገር ነበር፡፡ መንገድ የዘጉ ያመጹ ወታደሮች ነበሩ፡፡ ይሄ በየትኛውም ሀገር ሲከሰት የኖረ ነው፡፡ አሁን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ስለመጡ አዲስ በዓለም ላይ ያልነበረ ነገር እንደተፈጠረ ተደርጎ መነገርም አልነበረበትም፡፡ በዚያ ደረጃ የወሬ ማጋጋያ ይደረጋል ብዬ አላስብም፡፡
ችግሩ እንደተከሰተ የፈታንበት መንገድ በጣም አስተማሪ ነው፡፡ ሀገራችን ላይ የቆየው የተለመደው የችግር መፍቻ ዘዴ ‹‹በለው የትአባቱ ምን ያመጣል?›› የሚለው በእብሪት የተሞላ የኃይል ዕርምጃ ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሄ ዓይነቱ አካሄድ ይቁም እኮ ነው ያሉት፡፡ የቻልነውን በውይይት እንፍታ፤ያልቻልነውን ደግመን እንወያይ ነው እንጂ የተባለው ‹‹በለውማ›› የት ያደርሳል፤ የትም አላደረሰንም፡፡ በለው በወታደሩ ውስጥም አስፈላጊ አይደለም፡፡ በሰላም መፍታት መወያየት እስከተቻለ ድረስ ወታደሮቹም ይወያዩ ነበርና በውይይት ላይ እያሉ ለምን ይመታሉ፤ ይሄ መሆን የለበትም ነበር፡፡ ለመምታት አቅም ስለሌለ ነው ብለው በተሳሳተ መንገድ የሚያስቡም አሉ፡፡ እነርሱ 300 ወታደሮች ናቸው፡፡ ሌላው ሠራዊት እነርሱ ያደረጉትን በሙሉ አይቀበልም፡፡ ከ300 ወታደሮች ውስጥም ጥቂት ዓላማና ግብ የነበራቸው ግለሰቦች ነበሩ፡፡ አብዛኞቹ የመብት ጥያቄ መስሏቸው የተከተሉ እንጂ ምንም የሚያውቁት ነገር አልነበረም፡፡ እነዚህን የማዳንና የመጠበቅ ሥራ ነው የተሠራው፡፡ ጥያቄ የነበራቸውና ዓላማ ይዘው የገቡት ተቀላቅለው እንደነበሩ እኛ እናውቃለን፡፡ ጥያቄ ያላቸውን ዓላማ ከያዙት ለየናቸው፡፡ የሆነውም ይሄ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- እናመሰግናለን !
ጄኔራል ብርሃኑ፡- እኔም አመሰግናለሁ!
ወንድወሰን መኮንን