“የጨረታ መስፈርቱ ተወዳድረን እንዳናሸንፍ አድርጎናል”
– ስራ ተቋራጮች
አዲስ አበባ፡- የአገር በቀል ስራ ተቋራጮች የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን በሚያወጣቸው ዓለም አቀፍ የመንገድ ግንባታ ጨረታዎች ተወዳድረው ማሸነፍ እንዳልቻሉ ተገለጸ። የፋይናንስ አቅም ውስንነትና የጨረታ መስፈርቱ ከፍተኛ መሆን በዓለም አቀፍ የመንገድ ግንባታዎች ጨረታ ተወዳድረን እንዳናሸንፍ አድርጎናል ሲሉ አገር በቀል ስራ ተቋራጮች አመልክተዋል።
የባለስልጣኑ የኮሙኒኬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት ባለስልጣኑ ከሶስት ቢሊዮን ብር በላይ ለሚገመቱ የመንገድ ግንባታዎች የዓለም አቀፍ ጨረታ ያወጣል። በእነዚህ ጨረታዎች ለውጭም ሆነ አገር በቀል የስራ ተቋራጮችን የሚጋብዙ ቢሆኑም የአገር በቀል ስራ ተቋራጮች ዓለም አቀፍ የጨረታ መስፈርቶችን የሚያሟሉ ባለመሆኑ ተወዳድረው ማሸነፍ አልቻሉም።
መንገዶቹ በዓለም ባንክ፣ በአውሮፓ ህብረትና በአረብ ባንክ ድጋፍና ብድር የሚሰሩ ከሆነ እነዚህ ተቋማትን የሚያስቀምጧቸውን መስፈርቶች ማሟላት እንዳለባቸው የገለጹት አቶ ሳምሶን በጨረታው በፋይናንስ፣ በልምድና በፕሮጀክት አስተዳደር ከፍተኛ አቅም ያላቸው የሌሎች አገራት ስራ ተቋራጮች ጭምር ስለሚሳተፉ አገር በቀል ስራ ተቋራጮች ተወዳድረው ማሸነፍ ይሳናቸዋል ብለዋል።
ቀደም ሲል በዓለም አቀፍ የመንገድ ግንባታ ጨረታዎች ተወዳድረው ያሸነፉ አገር በቀል ስራ ተቋራጮች ከሁለትና ከሶስት የማይበልጡ መሆናቸውን አመልክተው እነዚህ አገር በቀል ስራ ተቋራጮቹ በዓለም አቀፍ የመንገድ ጨረታዎች ተወዳድረው አሸንፈው ሳይሆን የኢትዮጵያ መንግስት ብድሩን ከሚሸፍኑት የውጭ ባንኮችና አገራት ጋር ድርድር አድርጎ መስፈርቶቹ ዝቅ እንዲሉ ተደርገው መሆኑን ተናግረዋል።
በአገር ውስጥ በሚወጡ ጨረታዎች ተወዳድረው ያሸነፉት አገር በቀል ስራ ተቋራጮች በአዳዲስ የመንገድ ግንባታዎች እየተሳተፉ መሆኑን አውስተው በቀጣይ የካፒታል፣የልምድና የፕሮጀክት አስተዳደር ብቃታቸውን እያዳበሩ ሲመጡ ዓለም አቀፍ የመንገድ ጨረታዎች ተወዳዳሪነታቸው እየጎለበተ ይመጣል ብለዋል።
አገር በቀል ስራ ተቋራጮች የፕሮጀክት የአስተዳደር ፣ የልምድና የፋይናንስ አቅማቸውን በማሻሻል በዓለም አቀፍ የመንገድ ጨረታዎች ማሸነፍ የሚጠበቅባቸው መሆኑን ገልጸዋል። በቀጣይ የሚሰሩ 87 የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ስለሚኖሩ የአገር በቀል ስራ ተቋራጮች ይሳተፋሉ ብለን እንጠብቃለን ብለዋል።
ድርጅታቸው በመንገድ ግንባታ ከ20 ዓመት በላይ ልምድ ያለውና አሁንም ሶስት የመንገድ ፕሮጀክቶችን እየሰራ እንደሚገኝ የሚገልጹት የዮቴክ ኮንስትራክሽን ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሀብታሙ ደሳለኝ በበኩላቸው ለአገር በቀል ስራ ተቋራጮች ተብለው ከወጡ ጨረታዎች በስተቀር በዓለም አቀፍ የመንገድ ግንባታ ጨረታዎች ቢሳተፉም አሸንፈው እንደማያውቁ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ለዓለም አቀፍ የመንገድ ጨረታዎች የሚያወጣቸው መስፈርቶች ከ300 ኪሎ ሜትር በላይ ሲሆን ከዚህ በፊት በተመሳሳይ ፕሮጀክት ላይ የተሳተፈ የሚል የጨረታ መስፈርት ስለሚኖረው አገር በቀል ስራ ተቋራጮች መስፈርቱን ማሟላት ይቸገራሉ ብለዋል።
ከአንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በላይ በሆኑ የመንገድ ግንባታ ጨረታዎች አብዛኛው አገር በቀል ስራ ተቋራጮች እንደማይሳተፉ የሚገልጹት አቶ ሀብታሙ በተለይ የአገር በቀል ስራ ተቋራጮች የካፒታል አቅማቸው ውስን መሆኑና የኮንስትራክሽን ዕቃዎች ዋጋ መናር በዓለም አቀፍ የመንገድ ጨረታዎች ተወዳድረው ማሸነፍ እንዳይችሉ አድርጓቸዋል ሲሉ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን በሚያወጣቸው የመንገድ ግንባታ የጨረታ ሂደቶች ግልጽ የሆነ አሰራር መኖሩን አመልክተው አገር በቀል ስራ ተቋራጮች በዓለም አቀፍ የመንገድ ጨረታዎች ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያደረጓቸው የፋይናንስና የፕሮጀክት አስተዳደር የአቅም ውስንነቶች ሊፈቱ ይገባል ብለዋል።
ስራ ተቋራጮቹ በራሳቸው ሁለተናዊ አቅማቸውን ለማሳደግ የሚያደርጉት ጥረት እንደተጠበቀ ሆኖ መንግስት ተቋራጮች ከባንኮች በቀላሉ ብድር የሚያገኙበት ሁኔታ በማመቻቸት፣የፕሮጀክቶች ኮንትራት አስተዳደር አቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎችን መስጠትና የጨረታ መስፈርቶቹን ዝቅ በማድረግ ተወዳዳሪነታቸውን በማሳደግ የበኩሉን እገዛ ማድረግ እንደሚጠበቅበት አመልክተዋል።
ስማቸውንና ድርጅታቸውን መናገር ያልፈቀዱ አንድ የአገር በቀል ስራ ተቋራጭ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ እንደገለጹልን፤ ድርጅታቸው በዓለምና በአገር አቀፍ የመንገድ ጨረታዎች እንደሚወዳደርና አንድ ጊዜ ከቻይና ስራ ተቋራጮች ጋር ተወዳድሮ አሸንፏል። ሆኖም ጨረታውን ያሸነፍነው መስፈርቶቹን አሟልተን ሳይሆን መንግስት ገንዘቡን ከሚያበድሩ ባንኮችና አገራት ጋር ባደረገው ድርድር ዝቅ እንዲሉ ተደርጎ መሆኑን ተናግረዋል።
ለአገር በቀል ስራ ተቋራጭ የውጭ ምንዛሬ እጥረትና የፋይናንስ አቅም ውስንነት በዓለም አቀፍ ጨረታ ተወዳድረው እንዳያሸንፉ ማነቆ ሆኗል የሚሉት ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉት ግለሰብ በአንጻሩ የውጭ ኩባንያዎች በሚኖሩበት ሀገር የብድር አቅርቦትና የውጭ ምንዛሬ ስለሚያገኙ በጨረታዎቹ አሸናፊ ይሆናሉ ብለዋል።
በተለይ በመንገድ ግንባታ ላይ የተሻለ አቅም ያለው የሰው ሀይል መኖሩን ጠቅሰው ብረት፣ ማሽነሪና ሬንጅ የመሳሰሉ የመንገድ ግንባታ ከውጭ በዶላር ተገዝተው የሚገቡ መሆናቸው የፋይናንስ ውስንነት ስለሚኖር በመንገድ ግንባታው ጨረታ ለማሸነፍ አስቸጋሪ ያደርገዋል ብለዋል።
አገር በቀል ስራ ተቋራጮች በበኩላቸው የኮንትራት አስተዳደር አቅማቸውን ቢያሻሽሉ፣የፋይናንስ አቅማቸውን ቢያሳድጉና ተገቢውን የሰው ሀይል በተገቢው ቦታ ቢመድቡ፣ በመንግስት በኩል ደግሞ አገር በቀል የስራ ተቋራጮች ከውጭ አገራት ስራ ተቋራጮች በሽርክና እንዲሰሩ ቢደረግና የውጭ ምንዛሬ ችግሩን ቢፈታ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነታቸውን ማሳደግ እንደሚቻል ምክረ ሀሳብ ሰጥተዋል።
በቅርቡ ባለስልጣኑ የስድስት ቢሊዮን ብር በላይ የአራት ዓለም አቀፍ የመንገድ ግንባታ ጨረታዎችን አውጥቶ የነበረ ቢሆንም አራቱንም የመንገድ ግንባታዎች ጨረታውን ያሸነፉት አራት የቻይና ስራ ተቋራጮች መሆናቸው ታውቋል።
አዲስዘመን ጥር 1/2012
ጌትነት ምህረቴ