አዲስ አበባ፡-የትራፊክ አደጋን ለመከላከል በስድስት ሺህ 535 ኪሎ ሜትር መንገዶች ላይ በ306 ሚሊዮን ብር ወጪ የመንገድ ምልክት፣ ቀለም የመቀባትና አስፈላጊ የመንገድ ደህንነት ማሻሻያዎችን እየተሰሩ መሆናቸውን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ።
የመንገድ ደኅንነትና ዳታቤዝ ማኔጅመንት ዳይሬክተር ኢንጅነር አብረሃም አብደላ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት በአገሪቱ እየተበራከተ የመጣውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ በ2012 በጀት ዓመት 6535 ኪሜ መንገዶች ላይ በ306 ሚሊዮን ብር ወጪ የተጓደሉ የመንገድ ምልክት የማሟላትና ቀለም የመቀባት ስራዎች በሶዶ፣ በድሬዳዋ፣ በሻሸመኔ፣ በደብረማርቆስና ነቀምት ዲስትሪክቶች እየተካሄዱ ይገኛሉ። ለሚከናወኑ የመንገድ ደኅንነት ማሻሻያ ሥራዎችም ሶስት ተቋራጮች የሁለት ዓመት የሥራ ውል ፈርመው ስራ ጀምረዋል።
በቀሩት የዓለምገና፣ ጎንደር፣ አዲግራት፣ ኮምቦልቻና ጅማ ዲስትሪክቶችም ተቋራጮችን ለማስገባት በጨረታ ሂደት ላይ እንደሚገኙ ኢንጅነር አብርሃም ገልጸው በጨረታ ሂደት ላይ ያሉትን የመንገድ ዳር ምልክትና ቀለም የመቀባት ፕሮጀክቶች በፍጥነት ወደ ሥራ ማስገባት ስራም እንደሚሰሩ አመልክተዋል።እነዚህ የመንገድ ደህንነት ማሻሻያ ስራዎች መከናወንም የትራፊክ አደጋን በመከላከል ረገድ የራሳቸው ድርሻ እንዳላቸው ተናግረዋል።
ባላስልጣኑ የፍጥነት መቀነሻ ማንቂያዎች እና ኅዳጎች እንዲሁም በአደጋ ምክንያት ጉዳት የሚደርስባቸውን የመንገድ ዳር ምልክቶች ድጋፍ ብረቶች በፍጥነት ለመትከል በራስ ኃይል ለመስራት ዕቅድ እንዳለው የገለጹት ዳይሬክተሩ ከመንገዱ ዲዛይን እና ቅርጽ የተነሳ መታጠፊያ ኮርባዎች እና ዳገት-ቁልቁለት የሆኑ አደጋ ሊያጋልጡ የሚችሉ ቦታዎችን መለየት በዘላቂነት የመንገድ ዲዛይን ማሻሻያዎችን ለማድረግም ግብ ይዞ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የመንገድ ዳር ምልክቶች በአካባቢው ማኅበረሰብ መሰረቅ ፤ መጎዳት ደረጃቸውን ያልጠበቁ የፍጥነት መቀነሻ ኅዳጎች በተለያዩ አካላት መሠራታቸውና ለትራፊክ ፍሰት እንቅፋት መሆናቸው የገለፁት ኢንጂነር አብረሃም ለአብነትም በደብረማርቆስ፣ በዓለምገናና በኮምቦልቻ ተሰርተው የነበሩ ደረጃቸውን ያልጠበቁ የፍጥነት መቀነሻ ኅዳጎች እንዲነሱ መደረጋቸውን ጠቁመዋል።
አዲስዘመን ጥር 1/2012
ጌትነት ምህረቴ