በሀገሪቱ ከ3000 በላይ የወጣት ማዕከላት ቢኖሩም ከነዚህ ውስጥ የታለመላቸውን ወጣት ተኮር አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙት 1455 ብቻ መሆናቸውን የሴቶች ሕጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ገለፀ።
“ጀርመን ፋውንዴሽን ፎር ወርልድ ፖፑሌሽን” /DSW/ በወጣቶች ሥነተዋልዶ ጤና ዙሪያ ትናንት በቢሾፍቱ ከተማ ባዘጋጀው ፕሮግራም መክፈቻ ላይ ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ ሕይወት ሀይሉ እንዳሉት፤ በመላው ሀገሪቱ ከሶስት ሺህ በላይ የወጣት ማዕከላት ቢገኙም አብዛኞቹ ለታለመላቸው አገልግሎት እየዋሉ አይደሉም።
ማዕከላቱ ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶች በመስጠት ወጣቶች ጤናቸው ተጠብቆ አምራች ዜጎች እንዲሆኑ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ ለዚህም ወጣት ተኮር የሆኑ ፕሮግራሞች አለመኖር (youth friendly አለመሆን)፣ የተሟላ የተዋልዶ ጤናና ኤች አይቪ ፕሮግራሞችና አገልግሎቶች አለመኖር፣ የእውቀትና ክህሎት ማነስ፣ ለሴት ልጃገረዶችና አካል ጉዳተኞች ምቹ አለመሆን ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው ብለዋል።
በወጣት ማዕከላት ዙሪያ የሚከናወኑ ሥራዎችን በባለቤትነት አለመምራትና ቅንጅታዊ አሰራሮች አለመኖራቸው ተጨማሪ ችግሮች መሆናቸውንም ሚኒስትር ዴኤታዋ አክለው ተናግረዋል።
የሀገሪቱን ወጣቶች የተዋልዶ ጤና ችግሮች በማቅለል ረገድ የተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላት ያከናወኗቸው ተግባራት ሊበረታቱና ሊደገፉ የሚገባቸው ናቸው ያሉት ወይዘሮ መሰረት፤ ‹‹ዲ.ኤስ ደብሊው›› ከመንግስት ጋር በመተባበር ለወጣቶች ማሰልጠኛ ማዕከላት ግብዓት ከማሟላት እስከ ስብዕና ግንባታ ያበረከታቸውን አዎንታዊ ተግባራት ለአብነት ጠቅሰዋል።
ድርጅቱ በየአመቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን አቅም መገንባት መቻሉንና የአመራር ክሕሎት(ሊደርሺፕ)፣ የስራ አመራርና የህይወት ክህሎት እና መሰል ሥልጠናዎች ለወጣቶች ተደራሽ አድርጓል ሲሉም አወድሰዋል።
የ‹‹ዲ.ኤስ ደብሊው›› ኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቶ ፈየራ አሰፋ በበኩላቸው፤ፕሮግራሙ የወጣቶች መሆኑን ገልጸው፣ ላለፉት ሁለት አስርት አመታት አቅማቸውን በማሳደግና በሥነተዋልዶ ጤና ዙሪያ ግንዛቤ በመፍጠር፣ጾታዊ ጥቃትን በመከላከል፣ ወጣት መሪዎች እንዲፈጠሩ በማድረግ፣ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻቸውን ማቃለል እንዲችሉ ብዙ ሰራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ወጣቶች በበጎ ፈቃዳቸው በክበባትና በማህበራት እንዲደራጁ በማገዝ፣ በማዕከሎቻቸው በመሰባሰብ ስለራሳቸው የወደፊት ተስፋ እንዲመካከሩ ምቹ ሁኔታዎች በመፍጠር፣ ራሳቸውን ከሥነተዋልዶ ጤና ችግርና ከኤች አይ ቪ ኤድስ እንዲጠብቁ ግንዛቤ በመፍጠር በኢኮኖሚያዊና በማህበራዊ ልማት በንቃት እየተሳተፉ መንግስት የያዘውን እቅድ በመደገፍ የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ በማድረግ ሲሰራ መቆየቱን አቶ ፈየራ ገልጸዋል።
የፕሮግራሙ ዳይሬክተር እንዳስረዱት፤ በቀጣይ የወጣት ማዕከላትን ከማጠናከር ባለፈ በወጣቶች ተሳትፎ የወጣቶችን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ ፕሮግራም ተግባራዊ ይደረጋል። በመሆኑም የቤት ሰራተኞች፣ጎዳና ተዳዳሪዎች፣ሴተኛ አዳሪዎች፣ የቀን ሰራተኞች፣የአበባ ልማት እና የኢንዱስትሪ ፓርክ ሰራተኞች የበለጠ ተጋላጭነታቸው በጥናት በመለየቱ በነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ዙሪያ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
አዲስዘመን ጥር 1/2012
ሙሐመድ ሁሴን