አዲስ አበባ፡- ‹‹ለታሪክ ያለን ግንዛቤ የተዛባው ታሪክንና ፕሮፖጋንዳን ባለመለየታችን ነው፣ ዋናው መረዳት የሚገባው የአገር ታሪክና የታሪክ ትምህርት የተለያዩ መሆናቸውን ነው›› ሲሉ የቀድሞ የትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ጥላዬ ጌቴ አስታወቁ።
ሚኒስትሩ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት፤ ታሪክ ያለፈ ጉዳይን የሚነግር፤ መጥፎም ጥሩም ሳይሸሽግ የሚገልጥ ነው። በዚህም ታሪክ የሚሰናዳበት የራሱ አግባብና የአጻጻፍ ስልትን ተከትሎ ስለሚሆን ማንንም ሊያጋጭ አይችልም። ሆኖም ዛሬ ብዙዎች እየተነታረኩበት ያሉት ታሪክንና ፕሮፖጋንዳን ሳይለዩ በመንቀሳቀሳቸው ነው ብለዋል።
“የአገር ታሪክ ሁሉም ወጥቶ በአደባባይ በፈለገው መንገድ የሚተረክ አይደለም። ለትምህርት ሲሆን ደግሞ ከዚህ የበረታ ልዩና ጥልቀት ያለው ጥናትን ይፈልጋል” የሚሉት ዶክተር ጥላዬ፤ ታሪክን መጻፍም ሆነ መተንተን ያለበት የታሪክ ምሁር ብቻ ነው። ይህ ደግሞ የሚሆነው ምሁራኑ ሁሉም በሚባል ደረጃ በትክክል የአገራቸውን ታሪክም ሆነ ለትምህርት የሚሆነውን ታሪክ ተስማምተውበት ሲያጸድቁት እንደሆነ አስታውቀዋል።
‹‹የአፍሪካ፣ የአለምና የአውሮፓ ታሪክ ምንም ስለማያከራክር ዩኔስኮ አጥንቶ ያስቀመጠው መረጃ ስላለ ከዚያ ወስዶ ለትምህርት ማቅረብ ቀላል ነው›› የሚሉት ዶክተር ጥላዬ፤ ችግሩ እየተፈጠረ ያለው የአገር ታሪክ ላይ በመሆኑ ይህ ሲሰናዳ መሰረታዊ ምርምርና ጥናት ተደርጎ እንደሆነ አስታውሰው አሁንም ተዘጋጅቶ ለውይይት የቀረበው በዚህ መልኩ የተዘጋጀ እንደሆነ አመልክተዋል።
እንደ ዶክተር ጥላዬ ገለጻ፤ መቼም ቢሆን ፕሮፓጋንዳ ትምህርት ቤት ተወስዶ ትውልድን መቅረጫ ሊሆን አይችልም። ለትውልድ ማስተማሪያ መወሰድ ያለበት እውነታውን የሚያሳይ ብቻ ነው። ስለሆነም ግለሰቦች የራሳቸውን ስሜት እንዳያንጸባርቁበት ጥንቃቄ ተደርጎ ተሰርቷል ብለዋል።
ሆኖም አንዳንድ ክፍተቶች ስለነበሩ ቅሬታ ቀርቦባቸው እንደገና እንዲታዩ መደረጋቸውን ጠቁመዋል።
የታሪክ ባለሙያዎች ሚዛናዊ፣ ሀቁን የሚያስቀምጡ፣ ከስሜት ነጻ የሆኑ መሆን እንዳለባቸው የሚናገሩት ዶክተር ጥላዬ፤ የሚያዘጋጁት የታሪክ መማሪያ መጽሐፍ የእነርሱን ደረጃ እንኳን መናገር የለበትም። ታሪክ የሚሰራ እንጂ የሚሰረዝ ባለመሆኑም ትውልዱ ፈልፍሎ ያወጠዋልና ጥንቃቄ የሚፈልግ ስራ መሆኑን አስገንዝበዋል። በዚህ መመዘኛም የታሪክ ምሁራኑ ተመርጠዋል ብለዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ለአጠቃላይ ትምህርቱ እየተጻፈ የነበረው የታሪክ መማሪያ ሙሉ ለሙሉ በተግባር ላይ የዋለ እንዳልነበረ የገለጹት ዶክተር ጥላዬ፤ በዚህም ወደትምህርት ተቋማት የሚወሰዱ የማስተማሪያ መጸሐፍት አንድን ብሔር ከአንዱ የሚያጋጩ ሊሆኑ አይገባም።
አሁንም ለሙከራ የቀረበው መማሪያ ለጊዜው ማሻሻያ እየተደረገበት ነው። የአገሪቱ ታሪክ ብዙው የሚያስማማን እንጂ የሚያጋጭ ባለመሆኑ በአግባቡ አይቶ ለማስተማሪያ ብቁ እንዲሆን ማድረግ ላይም መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
ይህንን የሙከራ መማሪያ ጽሁፍ እንዲዘጋጅና ወደ ትግበራ እንዲገባበት ያደረገው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስቴር ሲሆን፤ አሁንም ክትትል እያደረገበት ይገኛል። ገና ትምህርቱ በአግባቡ ሳይሰጥ ጭቅጭቅ በማስነሳቱም ማስተካከያ እንዲደረግበት ተወስዷል። ስለዚህም ታሪኩ አሁን ሲጻፍ እውነታውን እንጂ ምስል ከስቶ የሚፃፍበት እድል እንደማይሰጠው አስረድተዋል።
አሁን ስምምነት ላይ የደረሰ የአገር ታሪክ ለትምህርት እንዲሆን ለማስቻል አገር ውስጥ የሌሉትን በአውሮፓ አይጠፉምና የመማሪያ መጸሐፍ ዝግጅቱ ላይ የሚሳተፈው የታሪክ ምሁር መርምሮ በማግኘት ለአገርና ለወገን ኩራት በሚሆን መልኩ ማዘጋጀት እንደሚጠበቅበትም አሳስበዋል። ታሪክን ለመጻፍ ከታማኝ ምንጮችና ኃላፊነት ከሚወስዱ እንዲሁም በአዋጅ ስልጣን ካላቸው አካላት መረጃው መወሰድ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
አዲስዘመን ጥር 1/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው