ሀላባ ቁሊቶ፡- በሀላባ ቁሊቶ ከተማ በአንድ ዓመት ከ50 በላይ አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች መጀመራቸውን የከተማ አስተዳደሩ ገለጸ፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባና የፋይናንስና ኢኮኖሚ ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ አንዋር ሰንዳፋ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ ከዓመት በፊት በከተማዋ ከአስር የማይበልጡ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች የነበሩ ሲሆን አሁን ላይ ከ60 በላይ ፕሮጀክቶች በግንባታ ላይ ናቸው።በአንድ ዓመት ብቻ 50 አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ተጀምረዋል። ይህ የሚያመለክተው ከተማዋ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ መሆኗን ያሳያል።
አቶ አንዋር እንዳሉት ከዚህ በፊት በከተማዋ ኢንቨስት ማድረግ አዋጪ አይሆንም ብለው የኢንቨስትመንት ፍቃድ ወስደው ወደ ግንባታ ያልገቡ ባለሃብቶች መኖራቸውን አስታውሰው ከተማዋ የዞን አስተዳደር ዋና ከተማ ከሆነች በኋላ ግንባታዎች እንደ አዲስ እየተጀመሩ ነው፡፡
በዞን ምስረታው ማግስት ከተማዋ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ እንደምትገኝ የተናገሩት አቶ አንዋር የኢንቨስትመንት ፍሰቱም ጥሩ በሚባልና ተስፋ በሚሰጥ ሁኔታ ላይ እንዳለ ጠቅሰዋል።
ሀላባ ከተማ ሰዎች ለኑሮ የሚመርጧት ለቱሪዝም ኮንፍረንስ ተመራጭ መሆኗንም ገልፀዋል።የትኛውም አዋጭ ኢንቨስትመንት ከመጣ ከተማ አስተዳደሩ ለመቀበል ዝግጁ መሆኑን የገለጹት ምክትል ከንቲባው፤ ከተማ አስተዳደሩ ሀላባ ቁሊቶ ከተማ ላይ ኢንቨስት ለሚያደርጉ ሁሉ በሩ ክፍት ነው ብለዋል።
ሀላባ ቁሊቶ ከተመሰረተች ከ100 ዓመት በላይ ታሪክ ያስቆጠረች ናት፡፡ በኢትዮጵያ በበርበሬ ምርቷ በስፋት የምትታወቅ ስትሆን፤ የተለያዩ ብሄሮችና ሃይማኖቶች ተቻችለው የሚኖሩባት በፈጣን እድገት ውስጥ የምትገኝ ታዳጊ ከተማ መሆኗን ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 30/2012
ዳግማዊት ግርማ