አዲስ አበባ፡- በቆዳ ንዑስ ዘርፍ ባሉ በዌት ብሉና ፕክል የበግ፣ የፍየልና የበሬ ቆዳ ላይ ተጥሎ የነበረው የኤክስፖርት ቀረጥ ሙሉ በሙሉ መነሳቱን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ተካ ገብረየሱስ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት በፒክልና በዌትብሉ የበግ፣ የፍየል እና የበሬ ቆዳ ላይ ተጥሎ የነበረው 50 በመቶ ታክስ ተነስቷል።ታክሱን ለመቀነስ ምክንያት የሆነው በዋናነት በአሁኑ ወቅት በዓለም ገበያ ያለቀለት ቆዳ ፍላጎት በመቀነሱ በቆዳ ዘርፍ የኤክስፖርት ንግድ በመዳከሙ መሆኑን ጠቁመዋል።በዚህም በሀገር ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የዌት ብሉና ፕክል ቆዳ ክምችትና ብክነት መከሰቱ አቶ ተካ አስታውቀዋል፡፡
የቆዳ እና ሌጦ አቅራቢዎች 30 በመቶ የሚሆነውን ቆዳ ለሃገር ውስጥ አምራቾች የሚያቀርቡበት እና 70 በመቶ የሚሆነውን ቆዳ በፒክል፣ በዌት ብሉ እና በክረስት መልኩ ለውጭ ገበያ እንዲልኩ የሚያስችል መመሪያ መውጣቱንም ነው ሚኒስትር ዲኤታው የተናገሩት።
ይህም የቆዳ ኢንዱስትሪውን ለማነቃቃት፣ የሀገር ውስጥ የዌት ብሉና ፕክል ከብክነት ለመታደግ እና ከዘርፉ መንግሥት ማግኘት የሚገባውን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ለማሳደግ ነው። በተጨማሪም የዘርፉን ባለሀብቶች የፋይናንስ አቅም ለማሳደግ የሚያስችል መሆኑ ተመላክቷል።
በቆዳ ኢንዱስትሪ ዘርፉ እየተመዘገበ ያለው ዕድገት በሚፈለገው ደረጃ ላይ አለመድረስ፣ የውጭ ምንዛሬ ግኝት አለመሻሻል፣ ለዘርፉ ልማት በመንግሥት የሚቀርበው የውጭ ምንዛሬ መጠን ማነስ የዘርፉ ዋና ዋና ተግዳሮቶች ሆነው መቆየታቸውን ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ተካ ገብረኢየሱስ ገልጸዋል።
የቆዳ እና ቆዳ ውጤቶች አምራቾች ማህበር በበኩሉ መመሪያው እየወደቀ ያለውን የቆዳ ኢንዱስትሪ የሚታደግ መሆኑን ገልጿል። የግሉ ዘርፉ እና መንግሥት ተቀራርቦ መስራታቸው ለውጥ ማምጣት እንደሚያስችል ማሳያ ነው ያለው ማህበሩ 80 በመቶ የሚሆኑ የቆዳ እና ሌጦ አቅራቢዎች ከዘርፉ መውጣታቸውን አስታውሷል። መመሪያው ወደ ዘርፉ እንዲመለሱ እድል የሚሰጥ መሆኑንም ማህበሩ አመልክቷል።
ይህ ውሳኔ እስከተላለፈበት ጊዜ ድረስ ካለቀለት ወይም እሴት ከተጨመረበት ማለትም በአግባቡ የተለፋ፣ የለሰለሰና የተቀለመ ለምርት ዝግጁ የሆነ ቆዳ በቀር ከፊል ያለቀለትና ጥሬ ቆዳ ወደ ውጭ መላክ በታክስ አማካይነት ክልከላ ተደርጎበት ቆይቷል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 30/2012
ፍሬህይወት አወቀ