አዳማ፡- መገናኛ ብዙኃን በመንገድ ደህንነት አጠባበቅና ከፍተኛ ጥፋት እያስከተለ ባለው የትራፊክ አደጋ ዙሪያ አበክረው ሊሰሩ እንደሚገባ ትራንስፖርት ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ፡፡
የመንገድ ትራንስፖርት ባለስልጣን በመንገድ ደህንነት አጠባበቅና በትራፊክ አደጋ ዙሪያ ሰሞኑን በአዳማ ከተማ ባደረገው ምክክር በትራንስፖርት ሚኒስቴር ከፍተኛ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅ አቶ ታጠቅ ነጋሽ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ መረጃን መሰረት በማድረግ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ እንዳመለከቱት ከችግሩ አሳሳቢነት አኳያ የመገናኛ ብዙኃን በትራፊክ አደጋ ዙሪያ ግንዛቤ የማስጨበጥና የማንቃት ሥራ ሊሰሩ ይገባል።
በትራፊክ አደጋ ባለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት ከ20 ሺህ ያላነሱ ዜጎች ሕይወታቸው አልፏል ያሉት ጥናት አቅራቢው በአንድ ዓመት ብቻ 4ሺ 500 ዜጎች በመኪና አደጋ፤ ከ7 ሺ ያላነሱ ሰዎች ቀላልና ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን በንብረትም ላይ ከፍተኛ ውድመት ደርሷል ብለዋል።አደጋውን ለመቀነስም መገናኛ ብዙኃን በሚፈለገው ደረጃ ግንዛቤ የማስረጽ ሥራ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
በመንገድ ትራንስፖርት ዘርፍ የመንገድ ትምህርትና ግንዛቤ ዳይሬክቶሬት የስልጠና ኤክስፐርት አቶ ሳሙኤል ይገዙ ባቀረቡት የመወያያ ጽሁፍ አንድ አሽከርካሪ የደህንነት ቀበቶ በማሰሩ ብቻ ከ45 እስከ 50 በመቶ ሕይወቱን ማዳን እንደሚችል ጥናቶች ዋቢ አድርገው ጠቁመዋል። የአገራችን አሽከርካሪዎች የደህንነት ቀበቶን የሚያደርጉት ቅጣትን በመፍራት እንጂ አደጋን እንደሚቀንስና እንደሚከላከል፤ ህይወታቸውንም ከአደጋ እንደሚታደግ በቂ ግንዛቤ በመውሰድ አይደለም ብለዋል።
በሀገሪቱ የደህንነት ቀበቶው መመሪያ የወጣው በርካታ የዓለም ሀገራትን ልምድ መሰረት አድርጎ መሆኑን የተናገሩት አቶ ሳሙኤል ግቡም አደጋን መቀነስ ብሎም ዜሮ ደረጃ ማውረድ መሆኑን ገልጸዋል። አሽከርካሪዎችም ሆኑ ተገልጋዮች የትራፊክ መመሪያና ደንቦችን ተረድተው በተገቢው መንገድ እንዲጠቀሙ መገናኛ ብዙኃን የማስተማር ማህበራዊ ኃላፊነት እንዳለባቸው ገልፀዋል።
ሌላው ጥናታዊ ጽሁፍ አቅራቢ አቶ ታጠቅ ነጋሽ እንደገለጹት የትራንስፖርቱ ዘርፍ ለሀገር ኢኮኖሚ ትልቅ አቅም ያለውና 95 በመቶ የገቢና ወጪ ንግዱ እንቅስቃሴም በዚሁ ዘርፍ የተመሰረተ ነው። በሀገሪቱ የሚገኙት መኪኖች በ2011 ዓ.ም በፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ተመዝግበው ይፋ የሆኑ 1 ሚሊዮን 71 ሺህ 345 መድረሳቸውን ገልጸዋል። የትራንስፖርት ሚኒስቴር አደጋን ለመቀነስ ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ ሰፊ ሥራ እየሰራ መሆኑን ገልጸው አሁንም ይህንን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል።
የገቢዎች ሚኒስቴር መረጃን ዋቢ አድርገው እንደገለጹት በ2011 ወደ ኢትዮጵያ ከገቡት ተሽከርካሪዎች ውስጥ 88 በመቶ የሚሆኑት ያገለገሉ ሲሆኑ አብዛኞቹ የቴክኒክ ችግር እንዳለባቸው በጥናት መረጋገጡን አስረድተዋል። በአመዛኙ የሞት አደጋ አድራሾቹም እነዚሁ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች መሆናቸውን ጥናቱ እንደሚያሳይ በጽሁፋቸው ገልጸዋል።
አሁን ባለው መረጃ የትራፊክ አደጋ ከኤች አይ ቪና ከወባ ወረርሽኝ ቀጥሎ በሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ዓለም አቀፍ ገዳይ ሆኖ መቀመጡን ገልጸዋል። በመሆኑም መገናኛ ብዙኃን በችግሩ ልክ ሽፋን ሰጥተው ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ በማስጨበጥ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
በምክክር መድረኩ ላይ ጋዜጠኞችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ የመጣውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ ተቋማቱ ግንባር ቀደም ሚና መጫወት እንደሚገባው ተመልክቷል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 30/2012
ወንድወሰን መኮንን